ብሪትኒ ስፒርስ ለዓመታት ከቆየችበት የአባቷ ቁጥጥር እንድትወጣ ፍርድ ቤት ወሰነ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ታዋቂዋ ድምጻዊት ብሪትኒ ስፒርስ ለ13 ዓመታት ከዘለቀው የአባቷ የበላይ ጠባቂነት ነጻ ወጥታለች።
ኢንስታግራም ላይ ላሉ 35 ሚሊዮን ተከታዮቿ "የደስታ እምባ ተናንቆኛል" ስትል ስሜቷን ገልጻለች።
የብሪትኒን ገንዘብ ጨምሮ ሌሎችም ውሳኔዎችን አባቷ ጄሚ ላለፉት 13 ዓመታት ተቆጣጥረዋል። ከረዥም የፍርድ ቤት ትግል በኋላ ግን ብሪትኒ በስተመጨረሻ የአባቷ የበላይ ጠባቂነት አብቅቷል።
በአሜሪካ ሕግ አንድ ሰው በጉዳዮቹ ውሳኔ ማሳለፍ የማይችልበት ሁኔታ ውስጥ ሲገባ በፍርድ ቤት ጠባቂ (conservatorship) እንዲመደብለት ይወሰናል።
በዚህ አሠራር መሠረት የብሪትኒ የበላይ ተቆጣጣሪ የነበሩት አባቷ ነበሩ። ከዚህ ቁጥጥር ነጻ የወጣችበትን ቀን "በሕይወቴ እጅግ የተደሰትኩበት" ስትል ብሪትኒ ገልጻዋለች።
የ39 ዓመቷ ድምጻዊት በአባቷ ቁጥጥር ስር የገባችው እአአ በ2008 ነበር። አሁን ግን የሎስ አንጀለስ ዳኛ በሕይወቷ ማንኛውንም ውሳኔ ያለ አባቷ ፍቃድ እንድትወስን ፈቅደውላታል።
የብሪትኒ አድናቂዎች የብሪትኒ አባት ከተቆጣጣሪነት እንዲነሱ ለወራት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ነበር። ነጻ መውጣቷ በተነገራት ቀንም በፍርድ ቤቱ አቅራቢያ ተሰብስበው ደስታቸውን ገልጸዋል።
የብሪትኒ አባት ጄሚ የበላይ ጠባቂነታቸው አስፈላጊ እንደሆነ ቢያምኑም "ብሪትኒ ዳግመኛ ሕይወቷን መምራት የምትጀምርበት ደረጃ ላይ ናት" ብለዋል።
ተቆጣጣሪዋ ሆነው ሲሾሙ ብሪትኒ "አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና የገንዘብ ቀውስ ውስጥ ነበረች" ብለዋል።
አባትየው የብሪትኒን ወጪ እና ገቢ ከመቆጣጠር ባለፈ በሥራ እና በግል ሕይወቷም ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን ነበራቸው።
ልጇን ለመጠየቅ ወይም በድጋሚ ለማግባትም የአባቷ ይሁንታ ያስፈልጋት ነበር።
ድምጻዊቷ ይህ የአባቷ ቁጥጥር እንዲነሳላት ፍድር ቤት ስትመላለስ ቆይታለች።
በፍርድ ቤት ሂደቱ ወቅት የብሪትኒን ገንዘብ የሚያስተዳድር ጊዜያዊ ተቆጣጣሪ ተሹሟል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሎስ አንጀለስ ፍርድ ቤቷ ዳኛ ብሬንዳ ፔኒ፤ ብሪትኒ ነጻ እንድትወጣ ውሳኔ ማሳለፋቸውን ተከትሎ ይህ ጊዜያዊ ተቆጣጣሪ ሥልጣኑ ይገደባል።
የብሪትኒ ጠበቃ ማቲው ሮሰንጋርት ውሳኔው በተሰጠ ቀን "በፍርድ ቤቱ ሂደት ወቅት ብሪትኒ ያሳየችውን ጥንካሬ አደንቃለሁ" ብሏል።
ሰዎች በሕይወታቸው ውሳኔ ለማሳለፍ ሲቸገሩ የበላይ ተቆጣጣሪ የሚመድበው የሕግ አንቀጽ ክፍተት እንዳለበት ጠበቃው ተናግሯል።
የድምጻዊቷ ጉዳይ ከአሜሪካ አልፎ የበርካቶች መነጋጋሪያ ሆኗል። ይህም ሕጉ ላይ የተወሰነ ማሻሻያ እንዲደረግ መንገድ ከፍቷል።
የብሪትኒ ጓደኛ የሆነችው ፓሪስ ሂልተን "እንኳን ለዚህ ቀን አበቃሽ! አሁን ሕይወትሽን በነጻነት መኖር ትጀምሪያለሽ!" ብላለች።
ብሪትኒ በኢንስታግራም ገጿ "በሕይወቴ እንደዚህ ጉዳይ የጸለይኩበት ነገር የለም" ስትል ለተከታዮቿ መልዕክት አስተላልፋለች።
ባለፈው ሰኔ ፍርድ ቤት ስትቀርብ "ይህንን በዝባዥ ሕግ አንሱና ነጻ አውጡኝ" ብላ ነበር።
በአባቷ የበላይ ጠባቂነት የተነሳ ያለ ፍላጎቷ የሙዚቃ መድረክ ላይ ለመዝፈን እንደተገደደች ተናግራለች። በድጋሚ ትዳር መሥርታ ልጆች ለመውለድ እንዳልቻለችም አክላለች።












