አፕል በሰው ሠራሽ አስተውሎት መስፋፋት የተነሳ ምርቶቹ ላይ ዋጋ ሊጨምር ነው

የአፕል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቲም ኩክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአፕል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቲም ኩክ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የሰው ሠራሽ አስተውሎት ተፈላጊነት እየጨመረ በምጣቱ የተነሳ አፕል የሚጠቀማቸው የሚሞሪ ቺፕሶች በመወደዳቸው በምርቶቹ ላይ የዋጋ ጭማሪ ሊያደርግ መሆኑን የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተናገሩ።

ቲም ኩክ ለዎል ስትሪት ጆርናል እንደተናገሩት የሚሞሪ ቺፕስ ዋጋ "የምንቋቋመው ባለመሆኑ" የዋጋ ጭማሪው "ልናስቀረው የምንችለው አይደለም" ብለዋል።

ሚሞሪ ቺፕስ እንደ ሞባይል ስልኮች ላሉ ምርቶች ዋነኛ ግብዓት ነው። ነገር ግን የሰው ሠራሽ አስተውሎት መስፋፋት ከቅርብ ወራት ወዲህ ዋጋቸውን አንሮታል።

ኩክ "ወደ እኛ የመጣውን ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ለመቀነስ የተቻለንን ሁሉ እያደረግን ነው፣ እናም ደንበኞቻችንን ከጭማሪው ለመጠበቅ እየሞከርን ነበር፣ ነገር ግን ሁኔታው ​​ዘላቂነት የሌለው ሆኗል" ሲሉ ለዎል ስትሪት ጆርናል ተናግረዋል።

"ሸማቾች መሣሪያዎቹን በሚፈልጉበት እና የሚሞሪ ቺፕስ አቅራቢዎች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እያደረጉ ባለበት በዚህ ወቅት የአቅርቦት መጠኑ አነስተኛ ነው" ሲሉ ኩክ ጨምረው ተናግረዋል።

ኩክ ለ15 ዓመታት የአፕል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው ከሰሩ በኋላ ከመስከረም ወር ጀምሮ በጆን ተርነስ ይተካሉ።

"በእርግጥ ለሸማቾች ምርቶቻችንን ወደ ተመጣጣኝ ዋጋ ለማውረድ ዝቅተኛ ዋጋ የተቆረጠለት የሚሞሪ ቺፕስ እና በቂ አቅርቦት ያስፈልገናል። ዋናው ነጥብ ይህ ነው።"

የኩክ አስተያየት የተሰማው ሌሎች የቴክኖሎጂ ግዙፍ ኩባንያዎች በቺፕስ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያለውን ጫና ይፋ ካደረጉ በኋላ ነው።

ታይዋን ሴሚኮንዳክተር ማኑፋክቸሪንግ ኩባንያ (ቲኤስኤምሲ) በዚህ ወር ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ልዩ ቃለ ምልልስ የዋጋ ግሽበት ወጪ እየጨመረ በመምጣቱ የዋጋ ጭማሪን ሊያንር እንደሚችል ተናግረዋል።

ቲኤስኤምሲ እንደ አፕል፣ ናቪዲያ እና ኤኤምዲ ባሉ ኩባንያዎች የተነደፉ እጅግ የላቁ ቺፖችን ያመርታል።

በዚህ ዓመት አጋማሽ ላይ ሳምሰንግ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ዋጋ እንደሚጨምር የሚጠብቅ መሆኑን ገልጿል።

የሰው ሠራሽ አስተውሎት ፍላጎት ከመጨመሩ ባሻገር የኢራን ጦርነት ሴሚኮንዳክተሮችን ለማምረት ወሳኝ የሆነውን ጋዝ ሂሊየም አቅርቦት ሰንሰለቱን በማስተጓጎሉ የኮምፒውተር ቺፕሶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል።

አይፎን 17 ባለፈው መስከረም ወር ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ተወዳጅ ሆኗል። የአፕል ምርቶች ሽያጭ ከዓመት በፊት ከነበረው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ2026 የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ብቻ በ17 በመቶ አድጓል፣ ይህም በቻይና በታየው ከፍተኛ ፍላጎት ምክንያት መሆኑ ተገልጿል።

ኩባንያው በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የማክ ሚኒ ኮምፒውተሮችን ዋጋ በ200 ዶላር ጨምሯል።