የታመመች ዶሮውን ሆስፒታል ወስዶ መነጋገሪያ የሆነው ታዳጊ ስጦታ ተበረከተለት

የፎቶው ባለመብት, Umer Chane
የ12 ዓመቱ ታዳጊ ማርቆስ አባዬ እና የሚወዳት ዶሮው ከሰሞኑ የማኅበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ሆነዋል።
ማርቆስ ያደገው ገጠር ነው። አሳዳጊው አቶ ቀለመወርቅ አሞኘ የተሻለ ትምህርት እንዲያገኝ ወደ በምዕራብ ጎጃም ዞን ወደምትገኘው ደንበጫ ከተማ ወሰዱት።
ወደ ከተማ ሲሄድ ቤተሰቦቹ የሰጡትን ዶሮ ይዞ ነበር። ይህች ዶሮ ታዲያ በድንገት ታመመችበት።
ሊያድናት ያደረገው ጥረት አልሳካ ሲለውም በስተመጨረሻ ሆስፒታል ይዟት ሄደ።
"ስታንኳርፍ አድራ ሐኪም ቤት ውሰዳት ስባል ሆስፒታል ወሰድኳት። የሰው ሆስፒታል ነው እዚህ የለም ተባልኩ" ይላል ማርቆስ።
ታዳጊው ታማሚ ዶሮውን አቅፎ ወደ ሆስፒታል ያመራው ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር።
የደንበጫ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ነርስ ዑመር ጫኔ ታዳጊውን ሲመለከቱ ቀድሞ የታያቸው ደግነቱ እንደሆነ ያስታውሳሉ።
ነርስ ዑመር ከሥራ ወደ ቤት ሊሄዱ ሲሉ ነበር ማርቆስን የተመለከቱት።
"ዶሮዋ ታማበት እኛ ሆስፒታል መጣ። ሐኪም ቤት መሆኑን ብቻ ነው የተረዳው። ሆስፒታል ከመጣ በኋላ ብዙ ሰዎች ሊሳለቁበት ሲሞክሩ ነበር" ይላሉ።
ነርስ እንደመሆናቸው "የልጁን ደግነት ከፊቱ ላይ መረዳት እንደቻሉ" ይናገራሉ።
ደግነቱ ደስ ስላላቸው አንዳንድ ጥያቄዎች ስለ ዶሮዋ እየጠየቁት ቪድዮ ቀረጹት እና ቲክቶክ ላይ አጋሩት።
"ሰውም ደግነቱን ሲያይ በጣም ተወዳጅ ሆነ።"
ዶሮዋን በፎጣ አቅፎ በስስት ይዞ ሲመለከቱት ስለ ዶሮዋ መጨነቁን በማስተዋል በትህትና ትኩረት ሰጥተው ለማረጋጋት እንደሞከሩ ይናገራሉ።
"በመታመሟ በጣም አዝኗል። ፊቱ ላይ ጭንቀት አለ። በዚያ ስሜት ውስጥ ሆኖ ነው ያናገረኝ።"
በማኅበራዊ ሚዲያ በተለቀቀው ቪድዮ ላይ ነርሱ ስለ ዶሮዋ ሕመም ማርቆስን ሲጠይቁት "እያንኳረፈች ነው. . . ሂድና እዚያ አሳክማት ብለውኝ ነው. . . ዛሬ ገና ነው እያንኳረፈች ያደረችው. . . እንቅልፍ አትተኛም" ሲል ይመልሳል።
ነርሱ ሆስፒታሉ ለሰዎች ሕክምና የሚሰጥ መሆኑን አስረድተው ወደ እንሰሳት ሐኪም ቤት መሄድ እንዳለበት ነገሩት።
ማርቆስም ዶሮውን ወደ እንሰሳት ሐኪም ቤት እንዲወስድ እንደተነገረው ይገልጻል። አሁን ላይ ዶሮዋ "እንደተሻላት" ተናግሯል።
አሳዳጊው አቶ ቀለመወርቅ "የተፈጠረው ነገር በጣም አስገራሚ ነው። እንደ ሕልም እና እንደ ራዕይ ነው የታየኝ" ይላሉ።
ታዳጊው ይኖርበት ከነበረው ገጠር በቅርቡ ትምህርት እንዲማር ወደ ከተማ ይዘውት እንደመጡ ይናገራሉ። እሱም ዶሮዋን ይዤ ነው የምሄደው አለ።
ዶሮዋ ገጠር ሳለም ታማበት ነበር። አድኗት ይዟት ወደ ከተማ ከመጣ በኋላ በድጋሚ ታመመችበት።
በድጋሚ ስትታመም ትምህርት ሁሉ እየተወ ዶሮዋን መንከባከብ ያዘ።
ከተማ ወጥቶ ዶሮዋን ባለሙያዎች ጋር ቢወስድም አልድንነት እንዳለችው ይናገራሉ።
"ዶሮዬ አልዳነችም ብሎ አዝኖ ትምህርቱንም ምግቡንም አቋረጠ።"
መፍትሔ አድርጎ ያሰበው ዶሮዋን ሆስፒታል ይዞ መሄድ ነው።
"ሆስፒታል ሲባል እሱ ያሰበው ሰዎችንም እንሰሳትንም የሚያክም አድርጎ ነው። ሁሉንም ማከም፣ ማዳን የሚችሉ ነው የመሰለው" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Umer Chane
ዶሮዬ ልትሞት ስለሆነ ቀጥታ ሆስፒታል ወስጄ ነው ማዳን ያለብኝ ብሎ ሆስፒታል ወሰዳት።
ይሄ ሲሆን ቤተሰቡ አላወቀም ነበር።
"እኛም አልሰማንም ነበር። ሲወስዳትም የት እንደሄደ አናውቅም። ሦስት አራት ቀን ቆይቶ ነው ከሚዲያ የሰማነው" ይላሉ አቶ ቀለመወርቅ።
ዶሮዋ ከቤተሰቡ "እንደ ጎጆ መውጫ" እንደተሰጠችው ይናገራሉ።
"ከሌላ ዶሮ ጋር ስትገናኝ ሁላ የሚበሏት ነው የሚመስለው። በጣም ይወዳታል።"
ገጠር ሳለ ዶሮዋን ብቻ ሳይሆን ሌሎች እንሰሳትም ይንከባከብ ነበር። ሲመሽ ደግሞ የጎረቤት ዶሮም ያስጠጋል።
በአንድ ወቅት የጎረቤት ዶሮ ታማ ወድቃ ቤታቸው ወስዶ እንደሰጣቸው ያስታውሳሉ።
"እነሱ ሞታለች ብለው ቢጥሏትም ነፍስ ስላገኘባት ሰጣቸው።"
የራሱን ዶሮም "ከመጠን በላይ ይወዳታል" ይላሉ።
ከተሰጠው ምግብ ላይ ቀንሶ፣ ፈትፍቶ፣ በእጁ ይዞ ወይም በእቃ ላይ አድርጎ ያበላታል።
ብዙውን ጊዜ አተኩሮ ያያታል። መሄጃዋን ይመለከታል።
እንዳትወድቅ ጉድጓድ ይደፍንላታል። ከተወሰነ ቦታ እንዳታልፍ ይጠብቃታል። ከሌሎች ዶሮዎች ጋር እንዳትገናኝም "እንደሚያቅባት" ይናገራሉ።
"ከዐይኑ አትለይም። ልቡ ያለው ትምህርት እና ዶሮዋ ላይ ነው። ትምህርት ላይ እንዲያተኩር ልብህን ከዶሮይት ላይ አንሳ እለው ነበር።"
ማርቆስ ሆስፒታል ይዟት በሄደው ዶሮ በማኅበራዊ ሚዲያ ታዋቂ ከመሆን አልፎ 100 ዶሮዎች ከነመኖው ሊሰጡት ቃል ተገብቶለታል።
ቪድዮው በማኅበራዊ ሚዲያ ከተጋራ በኋላ በዶሮ እርባታ ዙሪያ የሚሠራው 'ትረስት አግሮ ኮንሰልቲንግ' 100 ዶሮዎች እንደሚሰጠው አስታውቋል።
የተቋሙ መሥራች እና ምክትል ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አቡኑ አንዳርጌ ለሦስት ቀናት የማረፊያ እና ምግብ ወጪ ተሸፍኖ ሥልጠና እንዲያገኝ እና የምስክር ወረቀት እንዲሰጠው ይደረጋል ብለዋል።
የዶሮዎችን አመጋገብ እና ባህሪ ጨምሮ ስለ እንሰሳቱ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
ዶ/ር አቡኑ ዶሮዎች "ከሰው ልጆች ጋር ተስማምተው ለመኖር የተፈጠሩ ናቸው" ሲሉ ይገልጿቸዋል።
"ከቀረብናቸው፣ በሚገርም ሁኔታ ዶሮዎች በጣም መዝናናት ይችላሉ። የሚያወሩትን መስማት ይችላሉ። ምላሽም ሊሰጡ ይችላሉ። ቀርበው በተንከባከቧቸው ቁጥር እንቁላላቸውን፣ ምርታቸውን ይሰጣሉ። እንደ ሰው ልጅ ንክኪ የሚፈልጉ፣ ከሰው ልጆች ጋር ተስማምተው ለመኖር የተፈጠሩ ናቸው" ይላሉ።















