የብሪትኒ ስፒርስን ሃብት የሚያስተዳድረው ባለ አደራ የገንዘብ ተቋም 'በቃኝ' አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዝነኛዋ አሜሪካዊት ሞዛቂ ብሪትኒ ስፒርስ ለዓመታት ራሷንና ንብረቷን ለመቆጣጠር አስተማማኝ የአእምሮ ዝግጁነት የላትም በሚል በገዛ ንብረቷ ማዘዝ ሳትችል ቆይታለች።
ሀብት ንብረቷም አባቷና ሌላ የፋይናንስ ተቋም በጋራ በባለ አደራነት እንዲያስተዳድሩት ነበር ሲደረግ የነበረው።
ትናንት ግን ይህ በአደራ ሲያስተዳድር የነበረውና 'ዘ ቤስመር ትረስት' የተሰኘው የገንዘብ ተቋም የብሪትኒ ነገር በቃኝ ብሏል።
አባቷ ጄሚ ስፒርስ እና 'ዘ ቤስመር ትረስት' ኩባንያ በጥምረት ባለ አደራ ሆነው የመቆየታቸው ነገርም እያበቃለት ይመስላል።
ኩባንያው ለዚህ ውሳኔ የበቃው ባለፈው ሳምንት ብሪትኒ ስፒርስ ለፍርድ ቤት አምርራ በባለ አደራ መተዳደር ምንኛ ስሜቷን እንደጎዳው ከተናገረች በኋላ ነው።
ብሪትኒ ስፒርስ ለዓመታት የአባቷን ባለአደራነት ስትቃወም የቆየች መሆኑ ቢታወቅም እንደ ባለፈው ሳምንት ስሜታዊ ንግግር አድርጋ አታውቅም።
"በገዛ አባቴ፣ በገዛ ንብረቴ እንዲህ መንገላታትና ለገዛ ነፍሴ ባዳ መሆን ነበረብኝን?" ስትል ለፍርድ ቤት ያሰማችው ዘለግ ያለ ንግግር የብዙዎችን ስሜት የነካ እንደነበር ተዘግቧል።
ብሪትኒ ስፒርስ ይህን ምርር ያለ የፍርድ ቤት ንግግሯን የቋጨችው "ክቡር ዳኛ! እባክዎ የተቀማሁትን ሕይወቴን ይመልሱልኝ" በሚል ነበር።
'ቤሰመር ትረስት' ይህን ተከትሎ ትናንት ሐሙስ 'የበቃኝ' ማመልከቻ አስገብቷል።
ለምን በባለ አደራነት የብሪትኒ ስፒርስን ሀብት ማስተዳደር በቃኝ እንዳለ ሲጠየቅም የሞዛቂዋን ስሜታዊ ንግግር እንደ ምክንያት ጠቅሷል።
የእርሷ ፍላጎት ካልሆንን መቀጠል አንሻልም ብሏል የገንዘብ ድርጅቱ።
ብሪትኒ ስፒርስ ላለፉት 10 ዓመታት በባለ አደራ ስትተዳደር ቆይታለች። ይህም የኾነው የአእምሮ ጤናዋ አሳሳቢ ነው ተብሎ በመታመኑ ነበር።
ብሪትኒ ይህን ስሜታዊ የፍርድ ቤት ንግግር ካደረገች በኋላ አድናቂዎቿ በመላው ዓለም የበይነ መረብ ዘመቻ ከፍተዋል።
'ብሪትኒን ነጻ እናውጣ' የሚለው ዘመቻ አሁንም እንደቀጠለ ነው።
23 ደቂቃ በዘለቀው የብሪትኒ የሰሞኑ የፍርድ ቤት ንግግር ምን ያህል አባቷን በፍርሃት እንደምታያቸው፣ የማትፈልገውን እንድታደርግ እንደምትገደድ፣ ልጅ መውለድ ፈልጋ እንደተከለከለችና በአጠቃላይ በነፍሷ ማዘዝ እንኳ እንዳልቻለች የሚያትት ነበር።












