እስራኤል ከስምምነቱ በኋላ በደቡባዊ ሊባኖስ አዲስ ጥቃት ፈጸመች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምታካሄደውን ወታደራዊ ዘመቻ ቢተቹም አዲስ ጥቃት በደቡባዊ ሊባኖስ መፈጸሟ ተገለፀ።
እስራኤል ረቡዕ ዕለት አየር ኃይሏ ከክፋር ትብኒት ወጣ ብሎ የሚገኙ አካባቢዎችን ማጥቃቷን የአገሪቱ ብሐራዊ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።
የእስራኤል ጦር ስለጥቃቱ ምንም ዓይነት አስተያት ያልሰጠ ቢሆንም ከዚህ ቀደም የሄዝቦላህ መሠረተ ልማቶችን እንደሚደበድብ መግለጹ ይታወሳል።
ምንም እንኳን በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የተደረሰው ስምምነት ዝርዝር ነጥቦች ይፋ ባይሆኑም አደራዳሪዋ ፓኪስታን ሊባኖስን እንደሚያካትት አስታውቀለች።
ማክሰኞ ዕለት ትራምፕ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ “ሊባኖስን በሚመለከት የበለጠ ኃላፊነት ሊሰማቸው ይገባል” ብለዋል።
ፈረንሳይ በሚካሄደው የቡድን ሰባት ስብሰባ ላይ ትራምፕ እስራኤል ሄዝቦላህን “ለረዥም ጊዜ ተዋግታለች እና በርካታ ሰዎች ተገድለዋል” ብለዋል።
የኢራን ጦርነትን የሚያስቆም ስምምነት ላይ መደረሱን እሁድ ምሽት ይፋ ቢሆንም እስራኤል እና ሄዝቦላህ አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ቀጥለዋል።
ትራምፕ በቡድን ሰባት ስብሰባ ላይ ከኔታንያሁ ጋር “ጥብቅ ወዳጅነት” እንዳላቸው ገልጸው “በርካታ ጥቃት በመፈጸሙ ደስተኛ አይደለሁም” ብለዋል።
አክለውም “ያለ አሜሪካ እስራኤል አትኖርም። ያለ እኔ እስራኤል አትኖርም፤ ምክንያቱም ሌላ ፕሬዚዳንት እኔ ያደረግኩትን ለማድረግ ፈቃደኛ አይሆንም” ሲሉ ተደምጠዋል።
ኔታንያሁ ሰኞ ዕለት ጦራቸው “አስፈላጊ እስከሆነ ድረስ” በሊባኖስ እንደሚቆይ ተናግረዋል።
የኢራኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ፣ እስራኤል ሊባኖስ ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ወይም በግዛቲቱ ጦሩ መገኘትን እንደ ስምምነቱ ጥሰት እንደሚቆጥሩት ተናግረዋል።



















