ሙዚቃ፡ ብሪትኒ ስፒርስ አባቴ እየተቆጣጠረ አስቸገረኝ አለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ታዋቂዋ አሜሪካዊት ሙዚቀኛ ብሪትኒ ስፒርስ አባቴ እየተቆጣጠረኝ መንፈሴን ስለሚያስጨንቃት ወደኔ ድርሽ እንዳይል ስትል ፍርድ ቤቱን ተማጸነች፡፡
በሕይወቴም በሥራዬም ውስጥ እንዲገባ አልፈልግም የምትለው ብሪትኒ አቶ ጄሚ ስፒርስ በፍርድ ቤት የሷ ጉዳዮች ተቆጣጣሪ ሆነው ለ12 ዓመታት አገልግለዋል፡፡
በ2019 ለተወሰነ ጊዜ እሷንና የሷን ጉዳይ መከታተል ትተው ነበር አቶ ጄሚ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የራሳቸው ጤና መልካም ስላልነበረ ነው፡፡
የብሪትኒ ስፒርስ አድናቂዎች እሷ ከዚህ ከአባቷ ከለላና ጥበቃ ነጻ እንድትሆን በሚል የትዊተር ዘመቻ ከፍተዋል፡፡
የካሊፎርኒያ፣ ሎስአንጀለስ አካባቢ ፍርድ ቤት ሰነድ እንደሚለው ብሪትኒ የአቶ ጄሚን ውክልና በጽኑ ተቃውማለች፡፡
.አሁን እሷ ከአባቷ ይልቅ ሥራ አስኪያጇ ጆዲ መንገመሪ ይህንን ኃላፊነት እንዲወስድ ትፈልጋለች፡፡ መንገመሪ አባቷ ባልነበረ ሰዓት የሷን ጉዳዮች እንደ ወኪል በመሆን ሲያስተዳድር ነበር፡፡
አባቷ ጄምስ የብሪትኒን ነዋይ ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል፡፡ አሁን ግን ብሪትኒ የነዋይ ጉዳዮችን የሚከታተልላት ሁነኛ ድርጅት መቅጠር ትፈልጋለች፡፡
የብሪትኒ ጠበቃ እንደሚለው አባቷ ጄሚ ገሸሽ ሲደረጉ ውሳኔዋን በጸኑ እንደሚቃወሙ ይጠበቃል፡፡
ብሪትኒ ለመጨረሻ ጊዜ መድረክ ላይ ሥራዋን ያቀረበችው በጥቅምት 2018 ሲሆን በ2019 በሎስ አንጀለስ አቅዳው የነበረው ኮንሰርቷ አባቷ በመታመማቸው ለመሰረዝ መገደዷ ይታወሳል፡፡
ብሪትኒ ስፒርስ አሁን 38 ዓመቷ ሲሆን ከ2018 ጀምሮ ገንዘብ ነክ ጉዳዮቿን ተቆጣጥራ አታውቅም፡፡ ይህም በፍርድ ቤት በገዛ ሕይወቷ ጉዳዮች ራሷ እንዳትወስን ስለታዘዘች ነው፡፡
'ኮንሰርቫቶርሺፕ' በሚል የሚታወቀው ይህ የፍርድ ቤት አሰራር ሰዎች በአእምሮ ጤና ጉዳይ ችግር ውስጥ ሲገቡ በገዛ ነዋያቸው እንኳ እንዳይወስኑ ያግዳል፡፡ ምክንያቱም ውሳኔያቸው ጥፋትን ስለሚያስከትል ነው፡፡
ላለፉት ሁለት ዐሥርታት ብሪትኒ አባቷና ጠበቃዋ እንጂ ራሷ ገንዘብ ነክ ጉዳዮቿን ሆነ ስለገዛ ሕይወቷ መወሰን አትችልም፡፡ የሚጎበኟትንም ሰዎች የሚወስኑላት ወኪሎቿ ናቸው፡፡
ከሐኪሟ ሳይቀር የምትማከራቸውን ነገሮች እሷን ወክለው የሚነጋገሩላት አባቷና ጠበቃዋ ናቸው፡፡
ብሪትኒ የአእምሮ ጤና እክል የገጠማት ከኬቨን ፈድርላይን ጋር ከተፋታች ወዲህ ነው፤ ከ2007 ዓ.ም፡፡ ያፈሯቸውን ሁለት ልጆችም እሷ ዘንድ እንዳይሆኑ ፍርድ ቤት ወስኗል፡፡
ከዚያ ወዲያ ብሪትኒ ጤና ርቋት ነው ያለችው፡፡












