ከቤቱ ውጭ ዓይነ ምድር የሰበሰበ ናይጄሪያዊ በእስራት ተቀጣ

ከተሰባሰበ ከረጢት ጎን የቆመ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Mahmud Bashir

የምስሉ መግለጫ, Mahmud Bashir
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በሰሜን ናይጄሪያ አንድ ግለሰብ ጎረቤቶቹ ከቤቱ ውጭ ዓይነ ምድር በከረጢት እያከማቸ ሕይወታችንን አከበደው የሚል ቅሬታ ካቀረቡበት በኋላ የሁለት ሳምንት እስራት ተፈረደበት።

መሐመድ ሳይዱ ጎረቤቶቹ መጥፎ ሽታ እንደሚሸታቸው ለአካባቢ ባለሥልጣናት ካመለከቱ በኋላ በካኖ ከተማ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ተደርጓል።

ዳኛዋ ግለሰቡ በ14 ቀን እስር እና በ100 ሺህ ናይራ (74 ዶላር) እንዲቀጣ በይነውበታል። ዳኛዋ የግለሰቡን እርምጃ ሰዎችን ቸል ያለ እና ለጎረቤቶቹ ጤና አደጋ ሲሉ ገልፀውታል።

የውሃ ታንከሮችን ማፅዳት ሥራው የሆነው መሐመድ ሳይዱ ዓይነ ምድሩን ለአርሶ አደሮች ለማዳበሪነያት እየሸጠ ነበር ተብሎ ይታመናል።

በአካባቢው የሰው ዓይነ ምድር የተለመደ ማዳበሪያ ቢሆንም በይፋ ግን እምብዛም እውቅና አይሰጠውም።

የአካባቢው የሽማግሌ አዛዥ የሆኑት ሙሳ አብዱላሂ ለቢቢሲ "ለመጀመሪያ ጊዜ ቅሬታው ሲደርሰኝ 50 የሚሆን የአይነ ምድር ከረጢት የነበረው ይመስለኛል" ብለዋል።

ጎረቤቶች ከቤቱ የሚወጣው ሽታ ቤታቸው ለመቀመጥ እንኳ የሚያስችል እንዳልነበር ተናግረዋል።

ከቅሬታ አቅራቢዎች መካከል የሆነችው ሳሚላ ኢኑዋ ለቢቢሲ በቅድሚያ ችግሩን በግል ለመፍታት ሞክረው እንደነበር ገልፃለች።

"ስለ ሁኔታው አነጋግረነው ነበር፤ ነገር ግን አላቆመም" ብላለች።

በፍርድ ቤት ችሎት መሐመድ ሳይዱ የኅብረተሰብ ጤናን አደጋ ላይ በመጣል በቀረበበት ክስ ጥፋተኝነቱን አምኗል።

ዳኛዋ ብያኔያቸውን ከመስጠቸታው በፊት ወደ ቤቱ አቅንተው በከረጢት የተሰበሰበውን ዓይነ ምድር ተመልክተዋል።

ግለሰቡ ዓይነ ምድሩን እንዲያፀዳ እና ጥፋቱን እንዳይደግም ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ካመራ በኋላ ለነዋሪዎች በሰፈራቸው የተሻለ ሁኔታ መፈጠሩን ሳሚላ ኢኑዋ ተናግራለች።

"በመጨረሻም ሰፈራችን ያለ መጥፎ ሽታ አስደሳች ሆኗል" ብላለች።

የአካባቢው የሽማግሌ አዛዥ ግለሰቡ ቆሻሻውን መሰብሰብ ሲጀምር ጣልቃ ለመግባት ሞክረው እንደነበር ተናግረዋል።

ዓይነ ምድሩን ዳግም መሰብሰቡን ተከትሎ ጎረቤቶች አዛዡን አልፈው ወደ አካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት አምርተዋል።