አሜሪካ በህወሓት መሪዎች እና ቤተሰቦቻቸው ላይ የቪዛ ማዕቀብ ጣለች

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

አሜሪካ በኢትዮጵያ ያለውን ሰላም በማናጋት ውስጥ ተሳታፊ ናቸው ባለቻቸው አክራሪ የህወሓት አባላት እና የቅርብ የቤተሰብ አባሎቻቸው ላይ የቪዛ ክልከላ መጣሏን አስታወቀች።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በአክራሪ ህወሓት አባላት እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት እንዲያገረሽ የሚያደርግ ውጥረት እየተባባሰ መምጣቱን በመግለጽ ይህም "በቀጣናው ያለውን ሰላም እና መረጋጋት የሚያናጋ ነው" ብሏል።

በዚህም ምክንያት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢያ በተሰጣቸው ሥልጣን መሠረት በአክራሪ የህወሓት አባላት እና በቤተሰቦቻቸው ላይ የቪዛ ዕገዳ መጣሉን መሥሪያ ቤታቸው አስታውቋል።

ይህ የቪዛ ክልከላ ውሳኔ ዒላማ የሚያደርገው በትግራይ ያለው ቀውስ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት በሚያደናቅፍ ተጠያቂ የሚሆኑ እና ተባባሪዎቻቸውን መሆኑን አመልክቷል።

የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ጨምሮም ዩናይትድ ስቴትስ የትግራይ ሕዝብን ጨምሮ በሰላም እና በክብር መኖር ከሚፈልገው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን መቆሟን እንደምትቀጥል አስታውቋል።

የቀጣናውን ሰላም እና መረጋጋት ስጋት ላይ የሚጥሉ "የህወሓት ባለሥልጣናትን እና ሌሎች ግለሰቦችን ለማጋለጥ እና ተጠያቂ ለማድረግ [አሜሪካ] ያሏትን ዘዴዎች በሙሉ ትጠቀማለች" ብሏል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ።

በትግራይ ለሁለት ዓመታት ደም አፋሳሽ ጦርነት ከተካሄደ በኋላ በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል ጦነርቱን የሚያበቃ ስምምነት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ መደረሱ ይታወሳል።

በስምምነቱ መሠረት በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ተመሥርቶ ለሁለት ዓመታት ከቆየ በኋላ ሕጋዊ ዕወቅናው የተሰረዘበት ህወሓት ለጦርነቱ ምክንያት ከሆኑት መካከል አንዱ በሆነው የተናጠል ምርጫ ተመሥርቶ እንዲፈርስ የተደረገውን የክልሉን ምክር ቤት በመመለስ ሥልጣን ይዟል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በፌደራል መንግሥቱ የተቋቋመውን ጊዜያዊ አስተዳደርን ያፈረሰው ከአንድ ወር በፊት መልሶ የተቋቋመው የትግራይ ምክር ቤት የህወሓት ሊቀ መንበር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤልን የክልሉ ፕሬዝዳንት አደርጎ ከሾመ በኋላ የፌደራል መንግሥቱ በይፋ ያለው ነገር ባይኖርም በክልሉ ውስጥ ውጥረት ነግሷል።

በዚህም የተነሳ በክልሉ ሌላ ዙር ግጭት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት የተፈጠረ ሲሆን፣ የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ እየተካሄደ መሆኑን ነዋሪዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የመብት ድርጅት በመግለጫቸው እየተቃወሙ ነው።

በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል ግጭት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት ባየለበት በአሁኑ ወቅት የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዲፈረም ሁለቱን ወገኖች ያሸማገሉት የአፍሪካ ኅብረት መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ባለፈው ሳምንት ወደ መቀለ አቅንተው ከደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ጋር መነጋገራቸው ተዘግቦ ነበር።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በህወሓት መሪዎች መካከል መከፋፈል ተፈጥሮ በርካታ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ከህወሓት በመውጣት የራሳቸውን ፓርቲ ያቋቋሙ ሲሆን፣ ቀደምት የድርጅቱ መሪዎች በደብረጽዮን መሪነት ክልሉን ተቆጣጥረውት ይገኛሉ።

አሁን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የጣለው የቪዛ ዕገዳ ቀደምት እና አክራሪ በሆኑት የህወሓት መሪዎች እና ቤተሰቦቻቸው ላይ ያነጣጠረ ሲሆን፣ እነዚህ የፓርቲው መሪዎች የፌደራል መንግሥቱ ሊያጠቃን ነው በማለት ሲከስሱ፣ የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላን እያካሄዱ መሆናቸውን ቢቢሲ ያወጣው ዘገባ አመለክቷል።

ከወራት በፊት በህወሓት የሚመሩት የትግራይ ኃይሎች ከአራት ዓመት በፊት ከተካሄደው ጦርነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአማራ እና በትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ከፌደራል መንግሥቱ ኃይሎች ጋር መጋጨታቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ አስታውሷል።

አሜሪካ ደም አፋሳሹ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንዲያበቃ ጉልህ ሚና የተጫወተች ሲሆን፣ በጦርነቱ ወቅት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ባለሥልጣናት እንዲሁም በህወሓት መሪዎች ላይ የተለያዩ ማዕቀቦችን ጥላ እንደነበር ይታወሳል።