የብሪትኒ ስፒርስ አባት 'የልጄ የበላይ ጠባቂ መሆን በቅቶኛል፤ ራሷን ታስተዳድር' አሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የብሪትኒ ስፒርስ አባት ከዚህ በኋላ እሷን አልቆጣጠርም ሲሉ ሎስ አንጀለስ ውስጥ ለሚገኝ አንድ ፍርድ ቤት ማመልከቻ አስገብተዋል።
ይህ ማለት ለ13 ዓመታት ሕይወቷንና ገንዘቧን ሲቆጣጠሩ የነበሩት የታዋቂዋ ሙዚቀኛ አባት ከዚህ በኋላ በብሪትኒ ጉዳይ አያገባቸውም ማለት ነው።
ብሪትኒ ስፒርስ አባቷን ከበላይ ጠባቂ ኃላፊነት ለማስነሳት ባለፉት ሁሉት ዓመታት ሁለት ጊዜ ብትሞክርም ፍርድ ቤት ጥያቄዋን ሳይቀበል ቀርቶ ነበር።
የፖፕ ሙዚቃ ኮከቧ ከአባቷ ጋር ያላትን ግንኙነት "በዝባዥ" ስትል ትገልፀዋለች፤ በሱ ጥላ ሥር እያለሁ አላቀነቅንምም ብላለች።
ብሪትኒ ከሁለት ወራት በፊት አባቷን በተመለከተ ፍርድ ቤት ቀርባ ውስጧ ያለውን መዘርገፏን የሚዘነጋ የለም። ይህን ተከትሎ ነው አባት የበላይ ጠባቂነቴ ይብቃኝ ያሉት ተብሏል።
"በቅርቡ የተከሰቱ ጉዳዮች ናቸው ይህ የበላይ ጠባቂነት አስፈላጊ ነው ወይ ብዬ እንድጠይቅ ያስገደደኝ። ምናልባት አሁን ባለው ሁኔታ የበላይ ጠባቂዋ ሆኜ መዝለቄ አዋጭ አይደለም" ይላል አባት ማክሰኞ ዕለት ለፍርድ ቤት ያስገቡት ወረቀት።
"ብርቲኒ ስፒርስ ለዚህ ፍርድ ቤት በግልፅ እንደተናገረችው ሕይወቷን ያለ በላይ ጠባቂ መምራት ትሻለች" የሚለው ማመልከቻ ብሪትኒ ስፒርስ ገንዘቧን እንዲሁም የጤናዋን ሁኔታ ራሷ መቆጣጠር እንደምትፈልግ ያትታል።
ደብዳቤው "የብሪትኒ አባት ጄሚ ስፒርስ ለልጃቸው እንደሁልጊዜው በጎ በጎውን ነው የሚመኙት" ይላል።
እናም "ብሪትኒ የበላይ ጠባቂነቱ እንዲነሳ ከጠየቀችና የራሷን ሕይወት መምራት እንደምትችል ካመነች ስፒርስ ይህ ዕድል እንዲሰጣት ይጠይቃሉ።"
ብሪትኒ ከዚህ በፊት የአባቷ የባለይ ጠባቂነት "ጭካኔ" የታከለበት እንደሆነና፤ እሱ የሚላትን ካልፈፀመች ልጆቿን ማየት እንደማትችል እንደዛተባት መናገሯ ይታወሳል።
ባለፈው ሐምሌ ወር ፍርድ ቤት ቀርባ የ69 ዓመቱ አባቷ የበላይ ጠባቂነቱን ተጠቅሞ "በዝብዞኛል" ስትል መክሰስ እንደምትሻ ተናግራ ነበር።
የበላይ ጠባቂነት ምንድነው?
አባቷ የበላይ ጠባቂ ሆነው ገንዘቧን እንዲሁም ወሳኝ ጉዳዮችን እንዲቆጣጠሩ በፍርድ ቤት ኃላፊነት የተሰጣቸው በፈረንጆቹ 2008 ነበር።
በወቅቱ ዘፋኟ የአእምሮ ጤናዋ ተቃውሶ ነበር በሚል ነው ይህ ኃላፊነት ለአባቷ የተሰጣቸው።
ፍርድ ቤት አባቷ ጄሚ ቤት ንብረቷንና ገንዘቧን እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን እንዲቆጣጠሩ ኃላፊነት ሰጣቸው።
የበላይ ጠባቂነቱ ሁሉት ክፍሎች አሉት። አንደኛው ገንዘቧንና ንብረቷን የሚመለከት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እሷን እንደ ሰው መቆጣጠር የሚል ነው።
ነገር ግን አባቷ በጤና ምክንያት ከሶስት ዓመት በፊት ግላዊ ጎዳዮቿኝ ከመቆጣጠር ኃላፊነት ራሳቸውን አግልለዋል፤ በገንዘቡ ጉዳይ ግን ፀንተዋል።
አሁን ያስገቡት ማመልከቻ ብሪትኒ ስፒርስ ሙሉ በሙሉ ከአባቷ ጥላ ሥር እንድትወጣ የሚያደርግ ነው።












