በተለይ በአፍሪካ እየተስፋፋ ያለው አሳሳቢው አዲስ ዓይነት የስኳር ሕመም ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?

ኖዬላ ሙካምቢ

የፎቶው ባለመብት, BBC World Service

የምስሉ መግለጫ, ኖዬላ ሙካምቢ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ዶክተሮች ኖዬላ ሙካምቢን ኢንሱሊን ሲወጓት ሕይወቷን እንዳዳኑ ተሰምቷቸው ነበር። የ30 ዓመቷ የዴሞክራቲክ ኮንጎ ዜጋ ግን ለሞት የተቃረበች ያህል ተሰማት።

ኖዬላ ፀጉር አስተካከይ ናት። ዓይነት 1 ስኳር እንዳለባት የተነገራት በአውሮፓውያኑ 2023 ነበር። ነገሮች ልክ እንዳልሆኑ ሲሰማት ቆይቷል።

በየቀኑ ኢንሱሊን መውሰድ ከጀመረች በኋላ ይደክማት እንደጀመረ ትናገራለች። የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ኖዬላ ሚዛኗን መሳት እንደጀመረች እና አንድ ቀን ራሷን ስታ እንደወደቀች ታስታውሳለች።

"ለልጆቼ ልብስ እያዘጋጀሁ ሳለ ወደቅኩ። መሬት ላይ ወድቄ እየጮህኩ ባለቤቴ አገኘኝ።"

ከሦስት ዓመት በኋላ ዓይነት 5 ስኳር ሕመም እንዳለባት በባለሙያ ተነገራት።

የስኳር ሕመም በመላው ዓለም 830 ሚሊዮን ሰዎችን ያጠቃል። ሰውነት ኢንሱሊን ተጠቅሞ ስኳር ማብላላት ሳይችል ቀርቶ መጠኑ ከቁጥጥር ሲወጣ የሚገጥም ሕመም ነው።

ዓይነት 5 የስኳር ሕመም የሚከሰተው ዓመታት በዘለቀ የተዛባ አመጋገብ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል። በተለይ ደግሞ ከልጅነት እስከ ወጣትነት የተመጣጠነ ምግብ አለማግኘት ለዚህ ምክንያት ነው።

ይህ ዓይነቱ የስኳር ሕመም እንዳለ በይፋ የተነገረው ግን አምና በዓለም አቀፉ የስኳር ፌደሬሽን ነበር። ተቋሙ 251 ስኳር ላይ የሚሠሩ ማኅበራትን አቅፏል።

የዓለም ጤና ድርጅት ለበሽታው እውቅና አልሰጠም። ከሌሎች በሽታዎች የሚለይበት መንገድ ግልጽ እንዳልሆነም ገልጿል።

አንዳንድ ሳይንቲስቶች ዓይነት 5 የስኳር ሕመም 25 ሚሊዮን የሚጠጉ የስኳር ታማሚዎችን እንደሚያጠቃ ያምናሉ። ከሌሎች የስኳር ዓይነቶች ጋር በሽታውን ማምታታት ለጉዳት እንደሚዳርግም ያስጠነቅቃሉ።

በአልበርት አይንስታይን ኮሌጅ ኦፍ ሜድስን ውስጥ የዓለም አቀፍ የስኳር ተቋም ኃላፊ ዶ/ር ሜሪዴት ሀውኪንስ "በተሳሳተ የኢንሱሊን አሰጣጥ ምክንያት ሞት እያስከተለ ያለ ችግር ነው" ይላሉ።

"አብዛኞቹ ያጋጠሙን ወጣቶች ከእንቅልፋቸው ሳይነሱ በዚያው አሸልበዋል" ሲሉም ያክላሉ።

የስኳር ሕመም ምልክቶች

'የማያቋርጥ ድካም'

ዓይነት 1 የስኳር ሕመም የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም የሚያዳክም ሲሆን፣ ዓይነት 2 ደግሞ ሰውነት ለኢንሱሊን ምላሽ በማይሰጥበት ሁኔታ ውስጥ ይከሰታል።

ዓይነት 5 የስኳር ሕመም የሚከሰተው ከመጠን ያለፈ የተመጣጠነ ምግብ አጥረት የጣፊያ እድገትን ሲጎዳ ነው። ጣፊያ ሲጎዳ ደግሞ ኢንሱሊን የማምረት አቅሙ ይዳከማል።

ሕሙማን ኢንሱሊን ቢያመርቱም በበቂ መጠን አይሆንም። በዚህ ምክንያት መደበኛው የሕክምና መንገድ ብዙም ውጤታማ አይሆንም። አንዳንዴም ጉዳት ያስከትላል።

ለምሳሌ ኖዬላ ኢንሱሊን ሲሰጣት ደሟ ውስጥ ያለው የስኳር መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ (hypoglycaemia) አጋጥሟታል። ይሄም ሕይወትን ሊያሳጣ የሚችል ነው።

እንደ ሌሎቹ የስኳር ዓይነቶች ዓይነት 5 የስኳር ሕመም ከፍተኛ የጤና ቀውስ የሚያስከትል ነው። የዐይን መጥፋት፣ የኩላሊት ሥራ ማቆም፣ የነርቭ ሥራ ማቆም እንዲሁም አካልን እስከማጣት የሚያደርስ የቁስል በቀላሉ አለመዳን ይገጥማል።

ከመጠን በታች የሰውነት ክብደታቸውን የቀነሱ ወጣቶች በደማቸው ውስጥ ከፍተኛ የስኳር መጠን ስለሚኖራቸው ዓይነት 1 የስኳር ሕመም የያዛቸው ይመስላል። ሕመሞቹ ተመሳሳይ ምልክቶችም ያሳያሉ።

ኡጋንዳ የምትኖረው ኖዬላ እንደምትለው ዕድሜዋን በሙሉ ቀጭን ስትሆን፤ ልጇን ከወለደች በኋላ በጠና ታማለች።

"አፌ ሁሌም ይደርቃል። ውሃ አብዝቼ እጠጣለሁ። ሌሊት ሁለቴ፣ ሦስቴ እነቃለሁ።"

ክብደቷ ከ58 ኪሎግራም ወደ 49 ኪሎግራም የቀነሰው በፍጥነት ነበር። ያለማቋረጥ ይደክማትም ነበር። እነዚህ ሁለቱ ደግሞ የዓይነት 1 የስኳር ሕመም ምልክቶች ናቸው።

ዓይነት 5 የስኳር ሕመም በተለይም በእስያ እና ከሰሀራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት የሚኖሩ ሰዎች ላይ ይስተዋላል። በእነዚህ አካባቢዎች የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ዋነኛ ፈተና ነው።

በሌሎች አካባቢዎች የሰውነት ክብደታቸው አነስተኛ የሆኑ ሰዎች ለስኳር ሕመም እየተጋለጡ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ።

በ2023 የወጣ ጥናት በአሜሪካ 2.6 ሚሊዮን ሰዎች የተሳተፉበት ነው። ጥናቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ "ቀጭን ወይም መካከለኛ ክብደት ያላቸው ሰዎች ለስኳር እየተጋለጡ ነው" የሚል ግኝት አለው።

ይህ ሊን ዳያቤቲስ (lean diabetes) የተባለው የስኳር ሕመም ሥርጭት ዓይነት ከዚህ ቀደም ስኳርን ከሰውነት ክብደት ጋር የሚያስተሳስረውን ዕይታ ለውጧል።

ሶፊያ ሻረር ለንደን ነው የምትኖረው። በ23 ዓመቷ በተደረገላት ምርመራ ለስኳር ተጋላጭ መሆኗ ተነገራት።

አሁን 26 ዓመቷ ሲሆን፣ በታዳጊነቷ ሰውነቷ በከፍተኛ መጠን ቀንሶ እንደነበር ትናገራለች። በአንድ ወቅት በዚሁ ምክንያት ሆስፒታል ገብታለች።

በ19 ዓመቷ የሰውነቷ ክብደት ሲጨምር መታመም ጀመረች።

"በጣም ይርበኝ እና ሰውነቴ ይንዘፈዘፋል። ራሴን የምስት ይመስለኝ ነበር" ስትል ስሜቱን ትገልጻለች።

ዓይነት 1 ስኳር እንደሌለባት እንዲሁም በዘረም ተጋላጭ እንዳልሆነች ከተረጋገጠ በኋላ ምናልባትም ሕመሟ ዓይነት 2 ስኳር ሊሆን እንደሚችል ተገመተ።

ዓይነት 5 የስኳር ሕመም ላይ ምርምር የሚያደርጉት ሳይንቲስት አንዳንዶቹ ሶፊያ ላይ የሚታዩት ምልክቶች የበሽታው ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገልጻሉ።

ነገር ግን ምርመራው በዩናይትድ ኪንግደም ስላልተጀመረ እርግጠኛ መሆን አይቻልም።

ኖዬላ ሙካምቢ

የፎቶው ባለመብት, Noella Mukumbi

የምስሉ መግለጫ, ኖዬላ ሙካምቢ

አዲሱ ግኝት

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዓለም ጤና ድርጅት በአውሮፓውያኑ 1985 በሽታውን "የተመጣጠነ ምግብ ካለማግኘት ጋር የሚገናኝ የስኳር ሕመም" ብሎት ነበር።

ከ12 ዓመታት በኋላ ግን በሽታው ከዓይነት 2 የስኳር ሕመም የተለየ እንዳልሆነ ዶክተሮች አስታወቁ።

ስለ በሽታው ውይይት ማድረግ እና ጥናት ማካሄድ ላይም ክፍተቶች አሉ።

በሽታውን በትክክል ለማወቅ የሚያስችል ምርመራ አለመኖር በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕመሙ እንዳይታወቅ ምክንያት ሆኗል።

በየካቲት 2025 ዓለም አቀፉ የስኳር ፌደሬሽን በይፋ ለበሽታው እውቅና ሰጥቷል።

አምና በላንሴት ማዕከል ከ50 በላይ ሳይንቲስቶች የተሳተፉበት ጥናት ለበሽታው እውቅና እንዲሰጥ ረድቷል።

የዓለም ጤና ድርጅት፤ በአውሮፓውያኑ 1999 እና በ2006 "በቂ ሳይንሳዊ መረጃ ባለማግኘቱ" ሕመሙን ለብቻው ለመፈረጅ እንደማይቻል አስታውቋል።

አሁን በሽታው የተሰጠው ምድብ "ከስኳር ሕመሞች ባህሪያት ጋር የሚስማማ" መሆኑን ግን ጠቅሷል።

በሽታውን የተለየ ምድብ ለመስጠት "ጥሩ ማስረጃ" መኖሩን ግን ሳይጠቅስ አላለፈም።

ዓለም አቀፉ የስኳር ፌደሬሽን ለበሽታው እውቅና መስጠቱ ሕሙማን የተሻለ ሕክምና እንዲያገኙ እንደሚረዳ ገልጿል።

በአልበርት አይንስታይን ኮሌጅ ኦፍ ሜድስን ውስጥ የዓለም አቀፍ የስኳር ተቋም ኃላፊ ዶ/ር ሜሪዴት ሀውኪንስ "ለመጀመሪያ ጊዜ በምርምሩ ምዕራፍ ተከፍቷል" ይላሉ።

የዓለም ጤና ድርጅትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ሳይንቲስቶችን ዓይነት 5 የስኳር ሕመም መኖሩ ላይ ጥያቄ ያነሳሉ።

በሕንድ፤ ዓይነት 5 የሚባለው የስኳር ሕመም ዓይነት 2 የስኳር ሕመም ያለባቸው ሰዎች ሰውነታቸው ከመጠን በታች ሲቀንስ የሚከሰት ወይም የዓይነት 1 ዝርያ እንደሆነ ይታመናል።

በሕንድ የስኳር ሕመም ምርምር ማዕከል ኃላፊ ዶ/ር ቪ ሞሀን "ዓይነት 5 የስኳር ሕመም ከሆነ እንዴት ማከም እንደምችል ንገሩኝ" ይላሉ።

በሽታውን በምርመራ ማግኘት ቀላል ባለመሆኑ ምክንያት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እና የሰውነት ክብደት መቀነስ እንደ ጠቋሚ ምልክት ሲወሰዱ ይታያል።

አመጋገብን በማስተካከል እና የተመጠነ መድኃኒት በመውሰድ መሻሻል ሊታይ እንደሚችል የአንዳንድ ምርምሮች የመጀመሪያ ደረጃ ውጤቶች ያሳያሉ።

ነገር ግን የአሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ዓለም አቀፍ እርዳታ መቀነሱ በዘርፉ የሚደረገውን ምርምር አስተጓጉሏል።

በጦርነት፣ ረሃብ እና የምግብ እጥረት በሚፈተኑ አካባቢዎች ችግሩ ሊባባስ እንደሚችል ይገመታል።

"ዓለም አቀፍ የምግብ ቀውስ ውስጥ ለመግባት ጫፍ ላይ ነን። ለቀጣዩ ትውልድ መጥፎ ዜና ነው" በማለት ዶ/ር ሜሪዴት ሀውኪንስ ይናገራሉ።

ኖዬላ የተሰጣት የሕክምና ውጤት የተሳሳተ እንደሆነ ካወቀች በኋላ ለዓይነት 2 የስኳር ሕመም የሚሰጥ ኢንሱሊን እየወሰደች ነው። ጤናዋ ላይ መሻሻል እንዳየች ትናገራለች። ዐይኗ በተሻለ መመልከት ከመጀመሩ በተጨማሪ የሰውነት ክብደቷ ተስተካክሏል።

"በጣም ይደክመኝ ነበር። አሁን ግን ብርቱ ሆኛለሁ" ትላለች።