በኡጋንዳ ለሳምንታት ተቋርጦ ቆየው የኢንተርኔት አገልግሎት ተመለሰ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የኡጋንዳ መንግሥት ተቋርጦ የነበረውን ኢንተርኔት በመመለስ ማህበራዊ ሚዲያዎች ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እንዲሰጡ አደረገ።
በኡጋንዳ ኢንተርኔት ተቋርጦ የነበረው ብሔራዊ ምርጫን ተከትሎ ነው።
በኢንተርኔት እና ማሕበራዊ ሚዲያዎች መቋረጥ ይቅርታ የጠየቀው የኡጋንዳ መንግሥት "ለአገር ደህንነት ነው" የሚል ማስተባበያ ሰጥቷል።
የኢንፎርሜሽን ኮሙኑኬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት ፒተር ኦግዋንግ በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ " በማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ/ደንበኛ የሆንን ከአፍራሽ ይልቅ ገንቢ እንሁን" ሲሉ መልዕክት አስፍረዋል።
ኡጋንዳ ከሳምንታት በፊት በመላ አገሪቱ ባካሄደችው ብሔራዊ ምርጫ ዋዜማ ጀምሮ ኢንተርኔት ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚባል ደረጃ አቋርጣ የነበረ ሲሆን የትኛውንም የማህበራዊ ሚዲያምም መጠቀም አዳጋች ሆኖ ቆይቷል።
በወቅቱ ፕሬዝዳንት ዮዌሪ ሙሴቭኒ ማህበራዊ ሚዲያዎችን ሥርዓት አልበኞችና አድሏዊ ሲሉ ተችተዋቸው ነበር።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉት ፌስቡክ ከገዢው ፓርቲ ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸውን 200 የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች መዝጋቱን ካስታወቀ በኋላ ነው።
በወቅቱ ማህበራዊ ሚዲያዎቹ የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨት በሚካሄደው ምርጫ ላይ የሚካሄዱ ክርክሮች ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር እየሰሩ ነው ሲል አስታውቋል።
ፌስቡክ የማህበራዊ ሚዲያዎቹ ተቀማጭነታቸውን በኡጋንዳ ያደረጉ እና በአገር ውስጥ የሚገኙ ተጠቃሚዎችን ዒላማ ያደረጉ መሆናቸው አስታውቆ ሀሰተኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩ እና መልዕክታቸው በብዙ ተጠቃሚዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ለማስመሰል በተመሳሳይ መልኩ የተባዙ ገፆች ነበሩ ብሏል።
የፌስቡክ ግሎባል ትሬት ዲስራፕሽን ኃላፊ የሆኑት ዴቪድ አግራኖቪች እነዚህ ሐሰተኛ መረጃን የሚያሰራጩ ገጾች በቀጥታ ግንኙነት ያላቸው ከኡጋንዳ የማስታወቂያና ኮሙኑኬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ጋር መሆኑን በምርመራ ድርጅታቸው እንደደረሱበት ገልጿል።
ፌስቡክ 139 የኢንስታግራም ገጾችንም ጨምሮ ሰርዟል።
እነዚህ የተሰረዙ ማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒን እና ፓርቲያቸውን በመደገፍ የሚንቀሳቀሱ ነበር።
ፕሬዝዳንቱን ይፎካከር ከነበሩት መካከል አንዱ የሆነው ሮበርት ክያጉላንዪና ወይንም ቦቢ ዋይን ነበር።
ቦቢ ዋይን ፕሬዝዳነት ሙሴቪኒ ወደ ሥልጣን ሲመጡ የአራት አመት ታዳጊ ነበር።
ኡጋንዳ ባካሄደችው ብሔራዊ ምርጫ ሙሴቪኒ ለስድስተኛ ጊዜ ማሸነፋቸው የተገለፀ ሲሆን ቦቢ ዋይን ይህንን የምርጫ ውጤት ተቃውሞ ፍርድ ቤት ሰፊ ማጭበርበር ተካሂዷል በሚል ክስ መስርቷል።















