በትግራይ ክልል የተረቀቀው እና ስጋት የፈጠሩት በሞት የሚያስቀጡት አንቀጾች

የህወሓት ሊቀመንበር ደብረፂዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በቅርቡ በማኅበራዊ ሚዲያ እየተሠራጨ ያለው እና ከስድስት ዓመት በፊት በተደረገው እና ለጦርነቱ እንደ አንድ ምክንያት በሚጠቀሰው ምርጫ የተቋቋመው የትግራይ ክልል አስተዳደር እንዳረቀቀው የሚነገርለት አዲሱ ረቂቅ አዋጅ አወዛጋቢ ሆኗል።

"የትግራይ ሕዝብ ኅልውና እና ደኅንነትን ለማረጋገጥ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ያወጣው አዋጅ" በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ይህ ረቂቅ ሰነድ በክልሉ ምክር ቤት እንደሚጸድቅ ቢቢሲ ትግርኛ ከምንጮቹ ያገኘው መረጃ ያሳያል።

በስድስት ምዕራፎች የተከፋፈለው እና በ44 ገጽ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ የያዛቸው አንቀጾች በኢትዮጵያ ውስጥ የተለመዱ አለመሆናቸው እና ከመደበኛው የክልል ወይም የፌደራል ሕገ መንግሥት ውጭ የተተረጎሙ አንዳንድ ድንጋጌዎችን መያዙን ምንጮቹ ጨምረው ገልጸዋል።

በአዋጁ መግቢያ ላይ 'ጠላት' የፕሪቶሪያን ስምምነት በማፍረስ በትግራይ ሕዝብ ላይ ሁሉንም ዓይነት በደል እና ግፍ እየፈጸመ ስለሆነ የትግራይ ሕዝብ እና መንግሥት ራሳቸውን የመከላከል ተፈጥሯዊ እና ሕጋዊ መብት እንዳላቸው ተቀምጧል።

ህወሓት በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት የተቋቋመውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፈርሶ ከጦርነቱ በፊት በተመረጠው ምክር ቤት ተክቷል። ይህ ደግሞ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ያለውን ውጥረት አባብሶታል።

ቢቢሲ ረቂቅ አዋጁን የያዛቸውን ዝርዝር ጉዳዮች ተመልክቷል።

አስገዳጅ ብሔራዊ ጥሪ

በረቂቅ አዋጁ የመጀመሪያ ክፍል አንቀጽ 5 ላይ ዕድሜ እና ጤና የሚፈቅድለት ማንኛውም የትግራይ ተወላጅ የክልሉ መንግሥት የሚያቀርብለትን የክተት ጥሪ ተቀብሎ የመሳተፍ 'ብሔራዊ ግዴታ' እንዳለበት ይገልጻል።

በሦስተኛው ክፍል ደግሞ "የወንጀል ተጠያቂነት" በሚለው የረቂቅ ሕጉ ክፍል ስር፣ በትግራይ ጦር ውስጥ ለመቀላቀል ወይም ለመዋጋት ፈቃደኛ ያልሆነ ማንኛውም ሰው በደጀን ወይም በግንባር ግዴታውን እንዲፈጽም ጥሪ ቀርቦለት ያልተቀበለ ከሆነ ከ10,000 እስከ 50,000 ብር ተቀጥቶ ግዴታውን እንዲፈጽም ይደረጋል ሲል ይደነግጋል።

በዚህ ረገድ፣ የሠራዊቱን ወይም የመንግሥትን እንቅስቃሴ ማጋለጥ፤ ሕገወጥ የጦር መሳሪያዎችን መያዝ፣ ጥይት/ርችት መተኮስ፣ እንዲሁም ለማምለጥ መሞከር እና ከብሔራዊ ጥሪ ጋር አለመተባበር በእስራት እና በገንዘብ ቅጣት ከሚያስቀጡ ድርጊቶች መካከል ናቸው።

በሞት የሚያስቀጡ ሰባት ድንጋጌዎች

በአንቀጽ 29 እስከ 30 በተደነገገው መሠረት በተለይም በጦርነት ጊዜ በመሠረተ ልማት፣ በሕዝብ እና በመንግሥት ተቋማት ላይ የሚደርስ ጉዳት፣ ከጠላት ጋር መተባበር እና የምሥጢር ማሹለክ በእስራት እና በገንዘብ እንደሚያስቀጣ የተገለጸ ሆኖ ነገር ግን ድርጊቱ ሆን ተብሎ ከተፈጸመ በዕድሜ ልክ እስራት ወይም ሞት ሊያስቀጣ ይችላል።

እንዲሁም እንቅስቃሴው በሕዝቡ ላይ አለመረጋጋት የሚፈጥር ከሆነ በሕግ እና በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ ወይም በባለሥልጣናት ወይም በትግራይ ሠራዊት ላይ ጉዳት ማድረስ የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም እስከ ሞት ሊያስቀጣ የሚችል ወንጀል ሆኖ ሰፍሯል።

እንዲሁም ከውጭ መንግሥት ጋር በመተባበር "የትግራይን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት መፈጸም" እንደ ድርጊቱ ዓይነት ከባድ ከሆነ እስከ ሞት ድረስ የሚያስቀጣ እንደሆነ ተገልጿል።

ሌላው በአንቀጽ 44 ላይ የተገለጸው እና እስከ ሞት ቅጣት የሚያደርሰው ወንጀል ከጠላት ጋር የኢኮኖሚ ትብብር ማድረግ ወይም መመካከር የሚል የሚለው ነው።

የጦር እና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች በትግራይ ሕዝብ ወይም በተወሰነ የትግራይ ማኅበረሰብ ላይ ሆን ተብሎ እንዲፈጸም የቀሰቀሰ ትዕዛዝ የሰጠም ሆነ በራሱ ለመፈጸም የተንቀሳቀሰ በዕድሜ ልክ እስራት ወይም እስከ ሞት በሚደርስ ይቀጣል።

ረቂቅ ሕጉ ይህ በተለያዩ መንገዶች ይገለጻል ሲል አስፍሮ ከእነዚህም ውስጥ ረሃብን ወይም መድኃኒትን እንደ ጦርነት መሳሪያ መጠቀም ወይም የጥንት ቅርሶችንና የአምልኮ ቦታዎችን ሆን ተብሎ ማውደም በሞት ከሚያስቀጡ ድርጊቶች መካከል ተካትቷል።

የመገናኛ ብዙኃንን የሚመለከቱ አንቀጾች

የመስዋዕትነትን ክብር ማሳነስ፣ የተዋጊዎችንን እና ቤተሰቦቻቸውን ክብር መንካት በተለይም የተደራጀ የሚዲያ ቅስቀሳ ከሆነ እስከ አስራ አምስት ዓመት የሚደርስ እስራት ያስቀጣል።

በተጨማሪም በትግራይም ሆነ ከትግራይ ውጭ ትግሉን የሚተች፣ ሰዎች ወደ ትግል እንዳይገቡ የሚያበረታታ እና ትግሉን የሚቃወም ማንኛውም ሰው እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ እስራት እንደሚቀጣ ይገልጻል።

የቢቢሲ ምንጮች ይህ ከፕሬስ ነፃነት ጋር የተያያዘ እና በክልሉ [በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያ] የመናገር ነፃነትን ለማፈን ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።

በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ሌላ የ'ወንጀሎች' ዝርዝር ተካትተዋል። በተለይም ከሦስት እስከ አስር ዓመት የሚደርስ ቅጣት የሚጣልበት በማኅበረሰቡ ውስጥ ሽብር ሊያስከትሉ የሚችሉ ወሬዎችንና ሐሰተኛ መረጃዎችን መንዛት ይገኙበታል።

ሌላ አነጋጋሪ ድንጋጌ

አንቀጽ 48 በትግራይ ሠራዊት ላይ በማንኛውም መንገድ ፕሮፓጋንዳ ማካሄድ ወይም ሆን ተብሎ ከጠላት ጋር በመተባበር፣ ሆን ተብሎ እንዲጠቃ ማድረግ፤ የትግራይ ተወላጆችን ለጠላት መመልመል እና የትግራይ ጦር እንዲከዳ ማነሳሳት እና ማበረታታት የዕድሜ ልክ እስራት ወይም ሞት የሚያስቀጣ ወንጀል ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ሌላው ሞት የሚያስቀጣው ወንጀል ተቀጣጣይ ፈንጂ ያፈነዳ እና በአደጋው ሰው ከሞተ በሕዝብ እና በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ውድመት ካደረሰ እና ከተዛመተ የሚል ይገኝበታል።

በተጨማሪም የትግራይ የፀጥታ ኃይሎች የሚጠቀሙበትን ምግብ ወይም ውሃ መመረዝ እስከ 15 ዓመት በሚደርስ እስራት የሚያስቀጣ መሆኑ ተጠቅሷል።

ድርጊቱ በሰዎች ላይ የሞት አደጋ የሚያስከትል ከሆነ የዕድሜ ልክ እስራት ወይም የሞት ቅጣት ሊጣልበት እንደሚችል ተገልጿል።

የኢኮኖሚ አሻጥር

በተጨማሪም በአራጣ እና ተዛማጅ የኢኮኖሚ ሴራ፣ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር እና መድኃኒት የደበቀ ወይም በተጋነነ ዋጋ የሸጠ እስከ 300 000 ብር ቅጣት ሊጣልበት እንደሚችል ይደነግጋል።

ከዚህ በተጨማሪም በአዋጁ አንቀጽ 58 ላይ ሰፊ ስፍራ የተሰጠው ጉዳይ ነዳጅን ይመለከታል። ነዳጅን የደበቀ ከውሃ ጋር ቀላቅሎ የሸጠ ወይም ደግሞ ለፀጥታ ኃይሎች የተቀመጠ ነዳጅ ላይ ጉዳት ያደረሰ፣ ያታለለ የ25 ዓመት እስራት እንዲሁም ከ50,000 እስከ 100,000 ብር ቅጣት ሊደርስበት ይችላል።

የተፈጻሚነት ወሰን

ረቂቅ ሕጉ ላይ የተጠቀሱት ወንጀሎች እንደየ ክብደታቸው ከማኅበራዊ ፍርድ ቤት እስከ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ሊታዩ እንደሚችሉ አዋጁ ላይ ሰፍሯል።

በዚህ መሠረት የትግራይ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝን እና ሰበርን ብቻ የሚመለከት ሆኖ ውሳኔው የመጨረሻ እና ይግባኝ የማይቀርብበት ይሆናል ይላል።

በኢትዮጵያ የመጨረሻው ይግባኝ የማየት መብት ያለው 'ሰበር ሰሚ ችሎት' እንዳለው የተቀመጠ ሲሆን ይህ ረቂቅ ሕግ ግን ይህንን ይጣረሳል።

የአዋጁ አንቀጽ 62(5) ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን እርስ በርሱ የሚጋጭ ትርጓሜ በሚሰጥበት ጊዜ የክልል ምክር ቤቱ የሚሰጠው ትርጓሜ የመጨረሻ እንደሚሆን ይገልጻል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የመጨረሻው የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ሰጪ ሥልጣን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው።

አንቀጽ 75፣ ቁጥር 2፣ በትግራይ ሕዝብ ኅልውና እና ደኅንነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች፣ ከባድ የሙስና ጥፋቶች ሲፈጸሙ በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ [እጅ ከፍንጅ ባይያያዙም] ካለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መያዝ እንዲሁም ፍተሻ ማከናወን ይቻላል።

ይህ የአዋጁ ክፍል ለብዙዎች ስጋት የፈጠረ ሲሆን ታጣቂዎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማንኛውንም ዜጋ ለማሰር እና ለማዋከብ ይጠቀሙበት ይችላሉ የሚል ስጋት ፈጥሯል።

የአዋጁን ተፈጻሚነት በሚመለከት የተቀመጠው ሌላው ክፍል ደግሞ "ተፈጻሚነት፡ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 35 እስከ 48 በተደነገጉት ወንጀሎች ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናሉ" ብሏል።

እነዚህ አንቀጾች ወደ ኋላ ሄደው የሚፈጸሙ ሲሆን እጅግ ከባድ እና የሞት ቅጣትን ያዙ ናቸው።