የኡጋንዳ ምርጫ 2021፡ የኡጋንዳ ምርጫን ተከትሎ ቦቢ ዋይን "ለህይወቴ ፈርቻለሁ" አለ

ከሶስት አስርት አመታት በላይ የገዙት የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ከጥቂት ቀናት በፊት በተደረገው ምርጫ ማሸነፋቸውን ተከትሎ ዋነኛ ተቀናቃኛቸው ቦቢ ዋይን ለህይወቱ እንደሚፈራ ገልጿል።
በመድረክ ስሙ ቦቢ ዋይን ተብሎ የሚታወቀው የ38 አመቱ ሮበርት ካያጉላንይ ከቢቢሲ ጋር በስልክ ጋር ባደረገው ቆይታ "ለራሴ እንዲሁም ለባለቤቴ ህይወት ፈርቻለሁ" ብሏል።
ቤቱ በፀጥታ ኃይሎች መከበቡንና ከቤቱም መውጣት እንደተከለከለም ገልጿል።
"ማንም ሰው ወደ ቤት እንዲገባም ሆነ እንዲወጣ ከልክለዋል። ከዚህም በተጨማሪ የአገር ውስጥም ሆነ አለም አቀፍ ጋዜጠኞችም ወደ ቤቴ እንዳይገቡ እንዲሁ ታግደዋል" በማለት ያለውን ሁኔታ አስረድቷል።
ከሙዚቀኝነት ወደ ፖለቲካው አለም የተቀላቀለው ቦቢ ዋይን የምርጫውን ውጤትም እንደማይቀበለው ለቢቢሲ ተናግሯል።
ምርጫው በከፍተኛ ማጭበርበር የተሞላ ነው በማለት ክስ ያቀረበ ሲሆን አሸናፊ የተባሉት ፕሬዚዳንት ሙሴቪኒ በበኩላቸው ከፍተኛ ፍትሃዊነትና ሚዛናዊነት የታየበት ምርጫ ብለውታል።
ሐሙስ ጥር 6፣ 2013 ዓ.ም ከተደረገው ምርጫ በፊት ቅስቀሳዎቹ በሁከትና በግጭቶች የተሞሉ የነበሩ ሲሆን ለበርካታ ሰዎች ህይወት መቀጠፍ ምክንያት ሆኗል።
በምርጫው ዋዜማ መንግሥት ኢንተርኔትን ሙሉ በሙሉ አቋርጧል። ይህም ሁኔታ በምርጫው ታዛቢዎች ትችትንና ውግዘትን አስከትሏል።
በኢንተርኔት መቋረጥ ምክንያትም የድምፅ ቆጠራው በርካቶችን ፍትሃዊ ነበር የሚለውን ማሳመን አልቻሉም።አንድ የመንግሥት ሚኒስትር ለቢቢሲ በትናነትናው ዕለት እንደተናገሩት የኢንተርኔት አገልግሎት በቅርቡ ይመለሳል ብለዋል።
በቅርቡ የተደረገው ምርጫ ከጎሮጎሳውያኑ 1986 ጀምሮ ኡጋንዳን የመሯትን የ76 አመቱን ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒን ተጨማሪ አምስት አመት በስልጣን እንዲቆዩ አስችሏቸዋል።
ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ በአፍሪካ ረዥም ጊዜ በስልጣን ከቆዩ ፕሬዝዳንቶች አንዱ ናቸው፡፡ እርሳቸው እና ናሽናል ሬዚስታንስ ሙቭመንት የተባለው ፓርቲያቸው ለአምስት ዓመት በቆየ ጦርነት ማብቂያ ላይ በጎርጎሮሳዊያኑ 1986 ወደ ስልጣን የመጡ ሲሆን ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ኡጋንዳን እየመሩ ይገኛሉ፡፡
ደጋፊያቸው አንጻራዊ ሰላምን እና ብልጽግናን በሀገሪቱ በማምጣት በተለይም በጤና ላይ በተከተሏቸው ፖሊሲዎች ያወድሷቸዋል፡፡ የኤች አይቪ ስርጭትን በመግታት እና በቅርቡም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቋቋም ሠርተዋል።
በአንድ ወቅት በምዕራቡ ዓለም ከአዳዲሶቹ የአፍሪካ መሪዎች አንዱ ተብለው ቢወደሱም፣ ተቺዎቻቸው ወደ አምባገነን መሪነት ተለውጠዋል ሲሉ ይከሷቸዋል።
ሙሴቬኒ በፓርቲያቸው ውስጥ ተተኪ የሌላቸው ሲሆን በ2017 ደግሞ 75 የነበረውን የፕሬዚዳንቱን የዕድሜ ገደብ በማንሳት እንደገና ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር የሚያስችላቸውን ሕግ ፈርመዋል፡፡
ተቀናቃኛቸው ቦቢ ዋይን "የጌቶ ፕሬዝዳንት" ተብሎ በፍቅር የሚጠራው የ38 ዓመቱ ሙዚቀኛ በ 2000 ዎቹ መጀመሪያ የምስራቅ አፍሪካ የሙዚቃ ኮከብ ለመሆን በቅቶ በ2017 ደግሞ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበር ማግኘት ችሏል፡፡
ቦቢ ዋይን ለሙሴቬኒ አገዛዝ ትልቁ ተግዳሮት ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን ከዚህ ቀደም በፖለቲካ ውስጥ ያልተሳተፉ ብዙ ወጣቶችንም ማስተባበር ችሏል፡፡ ፕሬዚዳንቱን ከዚህ በፊት በከፍተኛ ደረጃ የተቸ ሲሆን "ህዝብን ይፈራሉ" ሲል ይከስሳል፡፡
ቦቢ ዋይንን "የዩጋንዳ መረጋጋትን እና ነፃነትን የማይወዱት" የውጭ ሃይሎች ወኪል እንደሆነ ሲከሱት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ወጣቶች በዘመቻው ወደ ሁከት እንዲገቡ እያሳሳቱ ናቸው ብለዋል፡፡
ቦቢ ዋይን በፖለቲካ ውስጥ ከገባበት ጊዜ አንስቶ ብዙ ጊዜ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ በሙሴቬኒ ላይ "አብዮት" ያስፈልጋል ሲልም ተናግሯል ፡፡ ትዊተር ላይ "WeAreRemovingADictator" የሚል ሃሽታግም ተጠቅሟል፡፡












