የአሜሪካ የጦር አውሮፕላን ተከስክሶ የቦይንግ ሠራተኞችን ጨምሮ ስምንት ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በደቡብ ካሊፎርኒያ የአሜሪካ አየር ኃይል የጦር አውሮፕላን የሆነው ቢ-52 ቦምበር ተከስክሶ ሁለት የቦይንግ ሠራተኞችን ጨምሮ ስምንት ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ።
የጦር አውሮፕላኑ ትናንት ሰኞ መደበኛ ፍተሻ እያደረገ ሳለ ነበር አደጋው የተከሰተው።
ኮለኔል ጄምስ ሄይስ "ዛሬ በኤድዋርስ አየር ኃይል መቀመጫ አሳዛኝ ክስተት ተፈጥሯል። ስምንት ታላቅ አሜሪካውያንን አጥተናል። ወታደሮች፣ ንጹኃን ዜጎች እና መንግሥት ኮንትራት የሰጣቸውም ይገኙበታል" ብለዋል።
የአየር ኃይል መቀመጫው እንዳለው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቶች ከአደጋው "መትረፍ እንደማይቻል" አሳይተዋል።
የሞቱት ሰዎች ዝርዝር ለቤተሰቦቻቸው ከተገለጸ በኋላ ለሕዝብ ይፋ ይሆናል።
የአውሮፕላን አደጋው ያደረሰው ጉዳት በአየር ኃይሉ ብቻ ተወስኖ እንዲቀር ማድረግ መቻሉ ተገልጿል።
ቢ-52 የተባለው የጦር አውሮፕላን ለአየር ኃይሉን መቆጣጠሪያ ሥርዓት ድጋፍ እየሰጠ እንደነበር እና በረራ ጀምሮ ብዙም ሳይቆይ እንደተከሰከሰ ተገልጿል።
የአደጋው መንስዔ ይፋ የሚደረገው ምርመራዎች ከተካሄዱ በኋላ መሆኑ ተገልጿል። ይህም እስከ 30 ቀናት ሊወስድ ይችላል። ተጨማሪ ምርመራ ደግሞ እስከ ስድስት ወራት እንደሚወስድ ኮለኔል ጄምስ ሄይስ ተናግረዋል።
ቦይንግ ባወጣው መግለጫ ሁለት ሠራተኞቹ በጦር አውሮፕላኑ ላይ ከተሳፈሩት ሰዎች መካከል እንደሚገኙበት አስታውቋል።
ቢቢሲ ከቦይንግ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
የካሊፎርኒያ አገረ ገዢ ጋቪን ኑሰም አደጋውን "አሳዛኝ" ብለው ለተጎጂዎች ቤተሰቦች እና የአየር ኃይሉ ሠራተኞች መጽናናትን ተመኝተዋል።
የአሜሪካ አየር ኃይል ቢ-52 የጦር አውሮፕላኖችን ከ1950ዎቹ አንስቶ እየተጠቀመ ይገኛል።
የጦር አውሮፕላኑ የተከሰከሰበት ሥፍራ በጭስ ታፍኖ የሚያሳዩ ምሥሎች ወጥተዋል።
ይህንን የጦር አውሮፕላን አሜሪካ በኢራን ዒላማዎችን ለመምታት ተጠቅማበታለች።
እስከ 50ሺህ ጫማ ከፍታ የሚበር ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ ቦምቦች እና 32 ኒውክሌር ክሩዝ ሚሳዔሎች ይጭናል።
በበረራ ላይ ሳለ ነዳጅ ስለሚሞላ ሰፊ አከባቢን ዒላማ የማድረግ አቅም አለው።















