ኡጋንዳን ለ35 ዓመታት የመሩት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በምርጫ ማሸነፋቸው ይፋ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኡጋንዳው የረጅም ዘመን ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ በድጋሚ መመረጣቸውን የአገሪቱ የምርጫ ባለሥልጣናት አስታወቁ። ተቀናቃኛቸው ቦቢ ዋይን ግን የድምጽ ማጭበርበር እንደነበር ክስ እያቀረበ ነው።
አገሪቱን ለ35 ዓመታት በፕሬዝዳንትነት የመሩት ዩዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒ ሐሙስ ዕለት ጥር 06/2013 ዓ.ም በተካሄደው ብሔራዊ 59 በመቶ የሚጠጋ ድምጽ አግኝተው ማሸነፋቸው ነው በአገሪቱ ምርጫ ኮሚሽኑ የተገለጸው።
በምርጫው ከተሰጠው ድምጽ ውስጥ ሙሴቬኒ 58.64 በመቶውን በማግኘት የሥልጣን ዘመናቸውን አራት አስርታት ለመድፈን የሚያስችላቸውን ውጤት ያገኙት ሲሆን፤ ዋነኛው ተፎካካሪ የነበረው ሙዚቀኛውና ፖለቲከኛው ሮበርት ኪያጉላኒ ወይም ቦቢ ዋይን የ34.83 በመቶ መራጮችን ድምጽ በማግኘት ሁለተኛ መሆኑ ተገልጿል።
በምርጫው ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገቡት መራጮች መካከል አጠቃላይ ድምጽ የሰጡት ሰዎች 57.22 በመቶ ብቻ እንደሆኑ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የድምጽ መስጠቱ ሂደት ሐሙስ ምሽት ላይ ተጠናቆ የተጀመረው የድምጽ ቆጠራ አርብ ዕለትም የቀጠለ ሲሆን አርብ ከሰዓት በኋላ ድረስ የነበረውን አሃዝ መሠረት አድርጎ በወጣው የመጀመሪያ ደረጃ ውጤት ሙሴቬኒ ተቀናቃኛቸውን ቦቢ ዋይንን በሰፊ የድምጽ ብልጫ እየመሩት እንደሆነ ተገልጾ ነበር።

ተቃዋሚው ዕጩ ቦቢ ዋይን በምርጫው ላይ የድምጽ ማጭበርበር ነበር በማለት አቅርቦት የነበረውን ክስ የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ውድቅ ቢያደርግበትም ማጭበርበር መከሰቱን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን እንደሚያቀርብ ገልጿል።
የምርጫ ታዛቢዎች እንዳሉት የድምጽ ቆጠራው ላይ የነበረው ዕምነት ለሦስት ቀናት በተቋረጠው የኢንተርኔት አገልግሎት ሳቢያ ክፉኛ ጥያቄ ውስጥ መግባቱን ገልጸው ነበር።
ምርጫው ሊካሄድ በተቃረበበት ጊዜ በተከሰተ ግጭት ከ50 በላይ ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች የተገደሉ ሲሆን፤ የተቃዋሚ ፖለቲከኞችም መንግሥትን በሚፈጸሙ ማጉላላቶች ሲከሱ ቆይተዋል።
ለ35 ዓመታት በሥልጣን ላይ የነበሩት ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ለስድስተኛ ጊዜ ነው አሁን ምርጫውን ያሸነፉት።
የ76 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ለአገሪቱ መረጋጋትን እንደሚያመጡ በመግለጽ ለምርጫ ሲቀሰቅሱ ነበር። ተቀናቃኛቸው የ38 ዓመቱ ጎልማሳ ቦቢ ዋይን ወጣቶችን በመወከል ወደ መሪነት መንበሩ ለመውጣት ቀስቅሷል።
የምርጫው ውጤት እየታወቀ ሲመጣ አርብ ዕለት የኡጋንዳ መንግሥት ወታደሮች ቤቱን በመክበብ ጥሰው መግባታቸውን ቦቢ ዋይን ተናግሮ ነበር።
"ወታደሮቹ ምንም ነገር አላሉንም" ሲል በትዊተር ገጹ ላይ ያሰፈረው ቦቢ ዋይን፤ "በከባድ ችግር ውስጥ ነን" ሲል ጽፎ ነበር።
ነገር ግን የመንግሥት ቃል አቀባይ ለቀረበው ክስ በሰጡት ምላሽ "ሃዘኔታን ፍለጋ ድራማ መፍጠር ነው" ሲሉ የተቀናቃኙን ፖለቲከኛ ክስ አጣጥለውታል።
"በዚህ ጊዜ ቦቢ ዋይን በጣም አስፈላጊ ሰው ነው። ስለዚህም ደኅንነቱን መጠበቅ የኡጋንዳ መንግሥት ኃላፊነት ነው" ሲሉ ቃል አቀባዩ ዶን ዋንያማ ተናግረዋል።
















