ሔኒከን በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ገቤኣው በመቀነሱ 8ሺህ ያህል ሠራተኞችን ሊቀንስ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ግዙፉ ቢራ አምራች ኩባንያ ሔኒከን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምከንያት የቢራ ሽያጩ መቀዛቀዙን ተከትሎ 10 በመቶ ሠራተኞቹን ለመቀነስ መወሰኑን አስታወቀ።
ሔኒከን ዋና መሥሪያ ቤቱ መቀመጫውን ካደረገበት አምስተርዳምን ጨምሮ 8ሺህ ያህል ሠራተኞችን ከሥራ ያሰናብታል ተብሎ ተጠብቋል።
የሔኒከን ኩባንያ የበላይ ሃላፊ ዶልፍ ቫን ዴን ብሪንክ 2020 "ያልተጠበቀ ቀውስ" ያጋጠመበት ዓመት መሆኑን ተናግረዋል።
በመላው ዓለም መጠጥ ቤቶች የተዘጉ ሲሆን እንደ ደቡብ አፍሪካ ያሉ አገራት ደግሞ ለተወሰነ ጊዜ የቆየ የአልኮል መጠጥ ሽያጭ ላይ ገደብ ጥለው ቆይተዋል።
ሔኒከን በመላው ዓለም በግዙፍነቱ ሁለተኛው ቢራ አምራች ሲሆን በአውሮፓ ደግሞ ላጋር ቢራ በመሸጥ ቀዳሚው ነው።
ኩባንያውን ከባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ጀምሮ እያስተዳደሩ የሚገኙት ቫን ዴን ብሪንክ በአውሮፓ፣ ሰሜን አሜሪካ እና በአደጉ የእስያ አገራት የተጀመረው የኮቪድ-19 ክትባት ሽያጭ ቀስ እያለ እንዲያንሰራራ ያደርጋል ብለዋል።
"ነገር ግን ዓለም አቀፍ ኩባንያ ነን. . .መላው ዓለም በተወሰነ ደረጃ ሲከተብ ነው ከዚህ ኪሳራ ውስጥ መውጣት የምንችለው" ሲሉ አክለዋል።
አሁንም በወረርሽኙ ክፉኛ የተጠቁትና ስርጭቱን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ትግል እያደረጉ ያሉት ብራዚል እና ሜክሲኮ የሔኒከን ሁለት ትልቅ ገበያ የሆኑ አገራት ናቸው።
ሔኒከን ዋና መሥሪያ ቤቱ በሚገኝበት አምስተርዳም፣ የክልል ቢሮዎችና የየአገራቱ እንቅስቃሴዎችን ከገመገመ በኋላ ተግባራዊ ማድረግ ይጀምራል ተብሏል።
ግዙፉ ቢራ አምራች ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት እንቅስቃሴውን ለመከለስ አቅዶ የነበረ ቢሆንም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ይህንን እቅዱን እንዲያፈጥነው አድርጎታል።
ሔኒከን ሠራተኞቹን ለመቀነስ ማቀዱን ካስታወቀ በኋላ በ2020 ብቻ 109 ሚሊዮን ዩሮ ኪሳራ እንደገጠመው ይፋ አድርጓል።
በ2019 የ1.15 ቢሊዮን ዩሮ የተጣራ ትርፍ አስመዝግቦ ነበር።
የቢራ ፋብሪካው ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው በአውሮፓ፣ ሜክሲኮ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኤንዶኔዢያ የሽያጭ መጠኑ ቀንሷል።
የቢራ አምራቹ እስከ 2023 ድረስ ባሉት ሶስት ዓመታት ውስጥ 2 ቢሊዮን ዩሮ ለመቆጠብ እና 350 ሚሊዮን ዩሮ የግል ወጪዎችን ለመቀነስ ማቀዱን ገልጿል።
አንዳንድ አገራት አሁንም በኮሮናቫይረስ ዳግም ወረርሽኝ የተነሳ ክልከላ ማድረግ በመጀመራቸው ገቢው በዚህ የፈረንጆች ዓመትም ሊቀንስ እንደሚችል ተንብይዋል።
ይኹን እንጂ ቀስ በቀስ ገበያው መሻሻል አንደሚያሳይ እና በ2022 ደግሞ የበለጠ እንደሚያንሰራራ ተተንብይዋል።












