የኡጋንዳ ምርጫ 2021፡ ዩዌሪ ሙሴቪኒና ቦቢ ዋይን ለፕሬዚደንታዊ ምርጫ ተፋጠዋል

ፖሊሶች በካምፓላ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

በኡጋንዳ አነጋጋሪ በሆነው ምርጫ የ38 ዓመቱ ኡጋንዳዊው የሙዚቃ ኮከብ ቦቢ ዋይን በአፍሪካ ካስተዳደሩ መሪዎች አንዱ የሆኑትን ዩዌሪ ሙሴቬኒ እየተገዳደራቸው ነው።

ሮበርት ክያጉላይ በመድረክ ስሙ ደግሞ ቦቢ ዋይን በመባል የሚታወቀው የሙዚቃ ኮከብ የአገሪቷን ወጣት ትውልድ እንደወከለ የተናገረ ሲሆን፤ የ76 ዓመቱ ዩዌሪ ሙሴቪኒ በበኩላቸው ለአገሪቷ መረጋጋት መቆማቸውን ተናግረዋል።

በምርጫ ቅሰቀሳ ዘመቻ ወቅት ከፍተኛ ተቃውሞ የነበረ ሲሆን በርካታ ሰዎችም ተገድለዋል።

መንግሥት ማህበራዊ ሚዲያዎች እንዲዘጉ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ፕሬዚደንት ሙሴቪኒ ይህ የሆነው ፌስቡክ የፓርቲያቸውን በርካታ ደጋፊዎች ገጽ በማገዱ ነው ብለዋል።

የኡጋንዳ ፖሊስ በምርጫው ዕለት በዋና መዲናዋ ካምፓላ የሕንጻ ጣሪያዎች ላይ ፖሊስ እንደሚያሰማራ ገልጿል።

ሆኖም መሳሪያ የታጠቁ ተሽከርካሪዎች ግን በጎዳናዎች ላይ ቁጥጥር ማድረጋቸውን ጀምረዋል።

ምርጫው አንድ ሰዓት ላይ የተከፈተ ሲሆን የምርጫው ውጤት ከቅዳሜ በፊት ይወጣል ተብሎ አይጠበቅም።

ፕሬዚደንት ሙሴቪኒ 35 ዓመታትን በሥልጣን ካሳለፉ በኋላ ለስድስተኛ ጊዜ ለመመረጥ ይወዳደራሉ።

በዋና መዲናዋ ካምፓላ እና በሌሎች በርካታ አካባቢዎች ዘመቻዎችን ማካሄድ ተከልክሏል።

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይህ የተደረገው ዘመቻ ማካሄድ በተከለከለባቸው ቦታዎች በርካታ ደጋፊዎች ስላላቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

መንግሥት ግን ምክንያቱን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሥርጭትን ለመከላከል ነው ብሏል።

ቦቢ ዋይንን ጨምሮ የተቃዋሚ ተወዳዳሪዎች፣ ደጋፊዎችና የዘመቻ ባልደረቦቻቸው በተለያዩ ጊዜያት ታስረዋል።

ፖሊስ በገበያ ማዕከላትና ሌሎች ትላልቅ ሕንፃዎች ላይ ኃይሉን ለማሰማራት ያሰበው ባለፈው ሕዳር ወር የተቃዋሚ ፓርቲ አንቂዎች ከሕንጻ ጣሪያዎች ላይ ተቃውሞ መጥራታቸውን ተከትሎ ነው።

በዚህ ወቅትም ቦቢ ዋይን ከታሰረ በኋላም ከ50 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

የምርጫ ታዛቢዎች

የምርጫ ታዛቢዎች ከአሜሪካ ሳይሆን ከአፍሪካ መሆናቸው ተገልጿል።

አሜሪካ ረቡዕ ዕለት አብዛኛው ምርጫውን ለመታዘብ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ታዛቢዎቿን ማስወጣቷን ገልጻለች።

በኡጋንዳ የአሜሪካ አምባሳደር ናታሌ ብራውን በመግለጫቸው "ያለ ታዛቢ ፕሬዚደንታዊውም ሆነ የፓርላማ ምርጫው ተጠያቂነት ፣ ግልፅነትና አመኔታ አይኖረውም" ብለዋል።

አምባሳደሯ በርካታ ኡጋንዳዊያንም ምርጫውን ለመታዘብ ፈቃድ እንዳላገኙ አክለዋል።

የአውሮፓ ሕብረት የምርጫ ባለሙያዎችን ለመላክ ያቀረበው ሃሳብም ተቀባይነት አላገኘም።

በምላሹ የፕሬዚደንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ቃል ቃባይ ዶን ዋንያማ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ ከአፍሪካ ሕብረትና ከምስራቅ አፍሪካ ማሕበረሰብ ታዛቢዎች እንዳሉ ገልጸዋል።

አክለውም "ኡጋንዳ ለመጨረሻ ጊዜ የምርጫ ታዛቢዎችን ወደ አሜሪካ መቼ እንደላከች አላስታውስም" ብለዋል።

የአገሪቷ መንግሥት ቀደም ብሎ ምርጫው ነጻና ፍትሐዊ እንደሚሆን ተናግሮ ነበር።

በሌላ በኩል ቦቢ ዋይን መራጮች ሐሙስ ዕለት በምርጫ ጣቢያዎቹ እንዲቆዩና የምርጫ ማጭበርበርን ለመከላከል በስልኮቻቸው ካሜራ እያንዳንዱን ሂደት እንዲቀርጹ ጥሪ አቅርቧል።

የአገሪቷ የቴሌኮም ድርጅቶች የኡጋንዳ ኮሚዩኒኬሽን ኮሚሽን ትዕዛዝን ተከትሎ ሁሉም ማህበራዊ ሚዲያ ዎችንና የጽሁፍ መልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎችን መዝጋቱን ለደንበኞቹ ያስታወቀው ረቡዕ ዕለት ነበር።