'ሰሜ ባላገር' - የኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃ ፈርጥ ሰማኸኝ በለው ሲታወስ

በኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃ ስም ጥር ከሆኑ ድምጻውያን መካከል ሰማኸኝ በለው ተጠቃሽ ነው።
'ባላገር' 'ደቦት እንሥራ' 'ነይ ዘመድዬ' 'እንዴት ነሽ' 'ዘና በይ' ታዋቂ ከሆኑ ሥራዎቹ መካከል ይገኙበታል።
ሰኔ 8/2018 ዓ. ም. ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ድምጻዊው 'ሰሜ ባላገር' በሚለው የመድረክ ስሙ ይታወቃል።
የአራት ልጆች አባት የነበረው ሰማኸኝ፤ በትወና ሥራውም ይታወሳል።
የአምባሰሏ ንግሥት ማሪቱ ለገሰ በሰማኸኝ ሞት የተሰማትን ጥልቅ ሐዘን ገልጻ "የባህል ንጉሥ ነበር" ስትል ገልጻዋለች።
ኅልፈቱን ከሰማች በኋላ በሐዘን መዋጧን ለቢቢሲ የተናገረችው ማሪቱ ድምጻዊው "መልካም ሰው" እንደነበር ጠቅሳለች።
ማሪቱ ከሰማኸኝ ጋር አብራ ባትሠራም ይቀራረቡ እንደነበር ጠቅሳ "እናትዬ በጣም ያሳዝናል፤ የሚሞት አይመስልም ነበር" ብላለች።
ድምጻዊው አስቻለ ፈጠነ "በጣም ጎበዝ የባህል አምባሳደራችን ነበር" ሲል ገልጾታል።
አንድ የአገው ሙዚቃን እና 'ኧረ በቃ' የተባሉ ሁለት ዜማዎችን ለሰማኸኝ እንደሰጠው አስቻለ ተናግሯል።
"በጣም ልዩ ሰው ነበር፤ እኔ ስለ ሰማኸኝ ለመመስከር ቃላት ያጥረኛል" ሲልም ለቢቢሲ ስሜቱን ገልጿል።
ሰማኸኝ የሙዚቃ ስቱዲዮ ሲገባ "ሌላ ሰው" እንደሚሆን ሳይናገርም አላለፈም።
ቅኝት መዝለልን ጨምሮ ሌሎችም ስቱዲዮ ውስጥ ሙዚቃ ሲቀርጽ ከሚያደርጋቸው ነገሮች ብዙ ትምህርት መውሰዱንም ድምጻዊው ተናግሯል።
ድምጻዊው አረጋኸኝ ወራሽ እንደሚለው ሰማኸኝ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ "ትልቅ ቦታ" ያለው ድምጻዊ ነው።
በባህል-ዘመናዊ የሙዚቃ ስልት ውስጥ በጉልህ ስሙ እንደሚነሳም ተናግሯል።
"በተለይም አዳዲስ ቃላት በማምጣት፣ ደንበኛውን ቱባ የባህል ጨዋታ በደንብ አድርጎ ይጫወት ነበር።"
ባሕር ዳር ተወልዶ እንዳደገ ድምጻዊ በአካባቢው ያሉ የአማርኛ ባህላዊ ሙዚቃዎችን በመጫወት ስመ ጥር መሆኑን ገልጿል።
"ለረዥም ዓመት ያገለገለ፣ በጣም ተወዳጅ የሆነ፣ ወደ ታች ወደ ላይም ሳይል ደረጃውን ጠብቆ ባህላዊ ሙዚቃን በደንብ የተጫወተ ነው" ሲልም አረጋኸኝ ለቢቢሲ አስተያየቱን ሰጥቷል።
ሰማኸኝ ክብደት ለመቀነስ እያደረገ የነበረውን ጥረት በመጥቀስ "ሕመሙንም ሳንሰማ በሙያው ውስጥ ያለን ሰዎች አስደንጋጭ ዜና ነው የሰማነው" በማለት ሐዘኑን ገልጿል።
"በባህል ጨዋታ ስለ ጎጃም በጥሩ ሁኔታ ዘፍኗል" የምትለው ማሪቱ "ብዙ ታሪክ አለው፤ ስለ አገሩም ዘፍኗል" ስትል ገልጻዋለች።
"ጎበዝ ነበር። 'ኧረ ምኑን ሰጠሽ' እንኳን ይበቃዋል። የሚያስቅ፣ የሚያጫውት፣ የሚያዝናና ዘፈን ነው።"
አስቻለው ልጅ ሳለ በቴሌቭዥን ግሽ አባይ ላይ ሰማኸኝን ያየው እንደነበር ይናገራል። 'ኧረ ባላገሩ' እና 'ደቦት እንሥራ' የሚሉት ሙዚቃዎቹን በተለይ ያስታውሳል።
በአካል የተዋወቀው የአገው ሙዚቃ ለመሥራት ስቱዲዮ ሳለ ነበር። ከተዋወቁ በኋላ አንድ ዜማ ሲሞክር "ወዲያው ብድግ አድርጎ ሠራው" ሲል ክህሎቱን ይገልጻል።
ከዚያም ሙዚቃውን ቻግኒ ለመቅረጽ መሄዳቸውን ያስታውሳል።
"ከአገሬ ከወጣሁ ረዥም ጊዜ ነበር። ያኔ አባቴ በሕይወት ነበር። ሰማኸኝን ቤት ይዤው ስሄድ በግ ታረደልን። የጥቅምት መድኃኔዓለም ነበር። እዚያው ክሊፕ ሠራን።"
ከዚያ በኋላ ዜማ ስጠኝ ብሎ ይጠይቀው እንደነበር፣ ባሕር ዳር ሲሄድ ይጠያየቁ እንደነበርም ይናገራል።
"አንተ ትልቅ ደረጃ እንደምትደርስ አውቅ ነበር ይለኛል። ሥራዎቼ ሲወጡ ብዙ ጊዜ ይደውልልኛል። ሁሌ ሞራል ይሰጠኛል።"
ማሪቱ የሰማኸኝን መድረክ አያያዝ እንደምታደንቅ ትናገራለች። "እስክስታው ደስ ይላል፤ ሰው በጣም ይወደዋል። ወዝ አለው፤ ያስቃል። በጣም ጎበዝ ነው። የሚገመገም አይደለም" ትላለች።
በአገር ውስጥ እና በውጭ አገርም ከሰማኸኝ ጋር አብሮ የሠራው አረጋኸኝ፤ "መድረክ አያያዙ የታወቀ ነው። ከእሱ በኋላ የመጡ የባህል ተጫዋቾች ከእሱ በማየት ነው። ከአለባስ ጀምሮ በደንብ የተካነበት ነው" ሲል ያስታውሰዋል።
የሰማኸኝን የሙያ አጋሮች ተጫዋች እና ጓደኞቹን አክባሪ እና ወግ አዋቂ እንደነበር ይመሰክሩለታል።
ማሪቱ "ባህል ያደምቃል። ባንዲራውን ለብሶ ብዙ ሠርቷል" ብላለች።
አረጋኸኝ ደግሞ "በማኅበራዊ ኑሮ፣ በአካባቢው፣ በጓደኞቹም፣ በሰፈሩም ጥሩ ስም አለው" ይላል።















