በራያ አላማጣ ወረዳ "የትግራይ ኃይሎችን ዒላማ ያደረገ" የድሮን ጥቃት መፈጸሙን ምንጮች ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በትግራይ ክልል ራያ አላማጣ ወረዳ "መረዋ" የተባለ ቀበሌ ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት የሰዎች ሕይወት ማለፉን የአካባቢው ባለሥልጣን እና የትግራይ ኃይሎች ምንጮች ተናገሩ። "ትምህርት ቤት" ላይ ተፈጸመ በተባለው ጥቃት "ሦስት የትግራይ ኃይሎች አባላት ሲገደሉ፤ ሰባቱ መጎዳታቸውን" ምንጮቹ ለቢቢሲ ትግርኛ ገልጸዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሦስት ምንጮች እንደሚስረዱት፣ የድሮን ጥቃቱ የተፈጸመው ትናንት ሰኞ ነሐሴ 4/2018 ዓ.ም. ጠዋት 2፡30 ገደማ ነው። ከአላማጣ ከተማ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው በዚህ ስፍራ ሦስት ጊዜ ጥቃት እንደደረሰ ተገልጿል።
በጥቃቱ ዒላማ የተደረገው "አርሚ 26" የተባለው የትግራይ ኃይሎች አባላት እንደሆኑ ቢቢሲ ትግርኛ ከወታደራዊ አዛዦች እና ከደቡብ ትግራይ ዞን ጽሕፈት ቤት ያገኘው መረጃ አመልክቷል።
የፌደራል መንግሥት ተፈጽሟል ስለተባለው የድሮን ጥቃት አስካሁን በይፋ አስተያየት አልሰጠም። ቢቢሲ ስለ ጥቃቱ ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ኮሎኔል ቢረሳው ሽፈራው ያቀረበው ጥያቄ ወዲያው ምላሽ አላገኘም።
ሁለት ጊዜ ጥቃት የተፈጸመው በመረዋ ቀበሌ በሚገኘው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ እንደሆነ ምንጮቹ ገልጸዋል። ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የትግራይ ኃይሎች አባል፣ "ጥቃቱ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ ነው የተፈጸመው። ክረምት በመሆኑ፣ ትምህርትም ስለሌለ የአርሚ 26 [አባላት] በዚያ ተጠልለው ነበር" ሲሉ "ጉዳት የደረሰባቸው የትግራይ ኃይሎች አባላት" መሆናቸውን አስረድተዋል።
በዚህ ጥቃት ሦስት የትግራይ ኃይሎች አባላት ወዲያውኑ እንደተገደሉ እና ሰባቱ ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው የሲቪል እንዲሁም ወታደራዊ ምንጮች ተናግረዋል። ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውም አክለዋል።
ሦስተኛው ጥቃት የደረሰው ወንዝ የሚገኝበት አካባቢ እንደሆነ ተገልጿል። በትግራይ ክልል የራያ አላማጣ ወረዳ አስተዳዳሪ ዳንኤል ታምራት በበኩላቸው ጥቃቱ "ሲቪሊያን ሰዎች" ላይ ማነጣጠሩን እና ትምህርት ቤት ላይ ጉዳት ማድረሱን በማንሳት ከስሰዋል።
"ድሮኗ ጉዳት ያደረሰችው በሰላማዊ ሰዎች ላይ ነው። ጥቃት ያደረሰችው አንደኛ በትምህርት ቤት፣ ሁለተኛ ደግሞ ነዋሪዎች ውሃ በሚቀዱበት ስፍራ ላይ ነው። በርካቶች ቆስለዋል፤ አንድ ደግሞ ወዲያውኑ ሞቷል" ብለዋል። ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ብዛት አራት መሆኑንም ተናግረዋል።
እንደ ፌደራል መንግሥት ሁሉ፣ የክልሉን ሥልጣን የተቆጣጠረው በዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚመራው አስተዳደርም ስለ ጥቃቱ በይፋ አስተያየት አልሰጠም።
ቢቢሲ ትግርኛ ያነጋገራቸው አንድ የትግራይ ኃይሎች ምንጭ ግን ጥቃቶቹ የተፈጸሙት "ከባሕር ዳር እና ቢሾፍቱ ከተሞች በተነሱ ድሮኖች ነው" የሚል ክስ አቅርበዋል።
"አንዲት ድሮን ጠዋት ከባሕር ዳር ተነስታ እንደሄደች አውቀናል፤ ሳትዞር በቀጥታ ነው የደበደበችው" ብለዋል። ቢቢሲ እነዚህ ክሶች በገለልተኝነት አላረጋገጠም።
ሰኞ ዕለት በትግራይ ኃይሎች ላይ የድሮን ጥቃት መፈጸሙን የሚገልጽ መረጃ የወጣው፣ በፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተፈጠረው ውጥረት በተካረረበት ወቅት ነው።
ሐምሌ 25 ቀን የፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች "ሸረሪና" በተባለ የሱዳን አዋሳኝ ሥፍራ ግጭት ውስጥ ገብተው ነበር።
ግጭቱ "በከባድ መሣሪያ እና ድሮን" የታገዘ እንደነበር እንዲሁም ፍንዳታዎችን፣ የከባድ መሣሪያ ተኩስ እና የአውሮፕላኖችን ድምጽ መሰማቱን የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ ዘግቧል።
በህወሓት ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የክልሉ አስተዳደር በዕለቱ ባወጣው መግለጫ፣ ፌደራል መንግሥት "ግልፅ ጦርነት ከፍቷል" ሲል ከስሷል።
የፌደራል መንግሥት ስለ ክስተቱ ይፋዊ አስተያየት አልሰጠም። የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር እንዲሁም የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት ዶ/ር አብርሃም በላይ ግን የህወሓት ኃይሎች "ጦርነት እንደከፈቱ" በመግለጽ ከስሰዋል።
የህወሓት መሪዎች ባለፉት ሳምንታት በክልሉ ውስጥ ባካሄዷቸው ስብሰባዎች ገዢውን ብልጽግና ፓርቲን ለማስወገድ ሲዝቱ ከመሰማታቸው በተጨማሪ፣ በክልሉ መገናኛ ብዙኃን ላይ ተመሳሳይ ዘገባዎች እየቀረቡ ነው።
እንዲሁም የፌደራል መንግሥቱ በትግራይ ክልል ውስጥ ስለተከሰቱ ጥቃቶች አስካሁን በይፋ ያለው ነገር ባይኖርም በሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙን በኩል የህወሓት መሪዎች ለጦርነት እየተዘጋጁ ነው የሚል ዘገባ እየቀረበ ነው።
በዶ/ር ደብረፅዮን የሚመራው የህወሓት አመራር የክልሉን ጊዜያዊ መንግሥት ከተቆጣጠረ በኋላ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ከፍተኛ ውጥረት ተፈጥሮ ግጭት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።















