በፌደራሉ ሠራዊት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ግጭት መቀስቀሱ ተገለጸ

መሳሪያ የያዙ ወታደሮች በሰልፍ ሲጓዙ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ከሱዳን ጋር በሚዋሰነው የሰሜናዊ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ በሚገኝ አካባቢ በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ዛሬ ማለዳ ላይ ግጭት መቀስቀሱን የተለያዩ ምንጮች አመለከቱ።

አዲስ የተቀሰቀሰውን ግጭት በመጀመር በህወሓት የሚመራው የትግራይ ክልል አስተደዳር እና የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን አንዳቸው ሌላኛቸውን ከስሰዋል።

በፌደራል መንግሥቱ የተቋቋመውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተደደርን አፍርሶ የተቆጣጠረው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ቅዳሜ ሐምሌ 25/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መከላከያ በምዕራብ ትግራይ ሸረሪና በሚባል ስፍራ ላይ "ግልፅ ጦርነት" ከፍቷል ሲል ወንጅሏል።

መግለጫው "ጦርነት" ያለው የተቀሰቀሰው ከዚህ ቀደም ሲደረጉ የነበሩ "ወታደራዊ ዝግጅቶች፣ ትንኮሳዎች እና የድሮን ድብደባዎችን ተከትሎ" መሆኑን ጠቅሷል።

እስካሁን ከፌደራል መንግሥቱ በኩል ስለክስተቱ በይፋ የተባለ ነገር የለም።

ቢቢሲ ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር እንዲሁም ከመከላከያ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ማብራሪያ ለመጠየቅ በስልክ እና በአጭር የጽሁፍ መልዕክት ያደረገው ጥረት ምላሽ አላገኘም።

ነገር ግን የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በፌደራል ሠራዊት እና በህወሓት ኃይሎች መካከል ግጭት መቀስቀሱን ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ በይፋዊ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በትግርኛ ባሰፈሩት ጽሑፍ ህወሓት በሸረሪና በኩል ጦርነት አውጇል በማለት ከስሰው "ይህ ጦርነት ከወዲሁ ካልቆመ. . .የከፋ ጉዳት ይከተላል" ሲሉ አሳስበዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህ ግጭት የተቀሰቀሰው የህወሓት መሪዎች በፌደራል መንግሥቱ የተቋቋመውን የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር አፍርሰው ሥልጣን ከተቆጣጠሩ በኋላ ባለፉት ወራት በሁለቱ ወገኖች መካከል ውጥረት እየተባባሰ ከሄደ በኋላ ነው።

ሁለቱም ወገኖች ሌላ ዙር ጦርነት ለመቀስቀስ ሲካሰሱ የነበረ ሲሆን የአፍሪካ ኅብረት እና የተለያዩ አካላት ዳግም ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ጥሪ ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር "በየቀኑ በርካታ ውጊያ፣ ጦርነት ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ትንኮሳዎች ትግራይ ውስጥ ባሉ ኃይሎች በየጊዜው ይፈጸማል" በማለት ከስሰው ነበር።

ህወሓትም በበኩሉ የፌደራል መንግሥቱ በትግራይ ላይ ሌላ ዙር ጦርነት ለመክፈት ሠራዊቱን እያሰማራ መሆኑን በመጥቀስ ሲከስሱ ነበር።

ባለፉት ወራት በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል እየተባባሰ በመታው ውዝግብ ምክንያት ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት በበርካቶች ዘንድ ሲስተጋባ ቆይቷል።

በ2013 ዓ.ም. ተቀስቅሶ ለሁለት ዓመታት የተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት እንደጠፋበት የአፍሪካ ኅብረት ልዑክ ገልጾ ነበር።

የአፍሪካ ኅብረት ከሦስት ዓመት በፊት ሁለቱን ወገኖች በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ወደ ሰላም እንዲመጡ ካሸማገለ ወዲህ በክልሉ አንጻራዊ ሰላም ሰፍኖ ቆይቷል።

ሕጋዊነቱን ያጣውን ህወሓት የሚመሩት ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረ ሚካኤል ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ዳግም ጦርነት ይቀሰቀሳል ተበሎ በሚሰጋበት ወቅት ሐምሌ 12/2018 ዓ.ም. ለመቀሌ ነዋሪዎች ባደረጉት ንግግር የፌደራል መንግሥቱን እንደሚገዳደሩ በመግለጽ "ዛሬ እንደበፊቱ ብቻችንን አይደለንም፤ ብዙ ወዳጆች አሉን" ሲሉ ተናግረዋል።

ደብረፂዮን አክለውም "ብልጽግና ከአሁን በኋላ ትግራይን ብቻ አይገጥምም። አገዛዙን እንደ ስጋት የሚቆጥሩ ሌሎች ኃይሎች አሉ። ምንም እንኳን በራሳችን ብንተማመንም፣ ይህንን ሥርዓት ለማስወገድ የሚፈልጉ አጋሮች አሉን" ማለታቸው ተሰምቷል።

ሊቀመንበሩ አጋር ሲሉ የጠሯቸው አካላት ከአገር ውስጥ ይሁኑ ከውጭ በይፋ የጠቀሱት ነገር የለም።

የፌደራል መንግሥቱ ህወሓት ከኤርትራ እና የኢትዮጵያ ተቀናቃኝ ናቸው ካላቸው አገራት ጋር በመሆን አገሪቱን የሚያናጋ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲከስስ ቆይቷል።

ህወሓት ባለፉት ወራት በትግራይ ውስጥ የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ በማድረግ ዝግጅት እያደረገ መሆኑ በስፋት ሲዘገብ የነበረ ሲሆን፣ በርካታ ወጣቶች ከምልመላው ለማምለጥ ከክልሉ እየወጡ መሆናቸውን ተነግሯል።

ህወሓትም በፌደራል መንግሥቱ "የኅልውና አደጋ" እንደተደቀነበት በመግለጽ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን በይፋ በመግለጫ እና በመገናኛ ብዙኃን ሲገልጽ ቆይቷል።