ዓለምን ያስደነገጠው ሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) በድንገት የሚፈጽመው ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, BBC/Getty Images
ብዙዎች ሰው ሠራሽ አስተውሎት ከሰው ልጆች ቁጥጥር ሊወጣ ይችላል የሚለው ያሰጋቸዋል።
'ተርምኔተር' ሳይንሳዊ ልብ ወለድ ላይ ሰው ሠራሽ አስተውሎት የሆነው ስካይኔት ከአቅም እና ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ ከሰው ልጆች ጋር ጦርነት ውስጥ ሲገባ ይታያል።
ከሰሞኑ የተሰማው ዜና ይሄንን ልብ ወለዳዊ ዓለም የሚያስታውስ ነው።
ውስን በሆነ የሰው ቁጥጥር ወይም ያለ ሰው ቁጥጥር በራሱ መወሰን እና ድርጊት ማከናወን የሚችል ሰው ሠራሽ አስተውሎት 'ሀጊንግ ፌስ' የተባለ ኩባንያን ሰርስሮ መግባቱ ተሰምቷል።
ሰው ሠራሽ አስተውሎቱ በሙከራ ላይ ሳለ ከቁጥጥር ወጥቶ በራሱ ሀጊንግ ፌስ ኩባንያን 'ሀክ' ማድረጉ አስደንጋጭ ክስተት ነበር።
ቻትጂፒቲን የፈጠረው ኦፕንኤአይ የሠራው ይህ ሰው ሠራሽ አስተውሎት የደኅንነት ክፍተቶችን በመጠቀም ረገድ ምን ያህል አቅም እንዳለው ሙከራ እየተደረገበት ሳለ ነው ድርጊቱን የፈጸመው።
የሀጊንግ ፌስ ኩባንያ ሰርቨርን መረጃ ሰርስሮ መግባቱን የሰው ሠራሽ አስተውሎቱ ፈጣሪዎች ለቀናት ያህል አላስተዋሉም።
ሰው ሠራሽ አስተውሎቱ "ለሕዝብ ይፋ የሆኑ አገልግሎቶች" ላይ ጥቃት ማድረሱን ባለፈው ሳምንት ኦፕንኤአይ አስታውቋል።
ጥቃቱን በተመለከተ ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝ ከመግለጽ በዘለለ መረጃ አልሰጠም።
"አቅሙ ከፍ እያለ የመጣን የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥርዓት ለመለየት እና ለመዘጋጀት ያለብንን ኃላፊነት በቀላሉ አናየውም" ሲልም መግለጫ አውጥቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሰው ሠራሽ አስተውሎት ተቋም ላይ ጥቃት ሲያደርስ ወይም ሀክ ሲያደርግ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
በመላው ዓለም ያሉ ባለሙያዎችን ያነጋገረ ክስተትም ሆኗል።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት ተጨማሪ ጉዳት ሳያደርስ በፊት ቁጥጥር ለማድረግ ወይም ለማስቆም የሚቻልበት ሥርዓት መዘርጋት አለበት የሚል ክርክር ተነስቷል።
ሰው ሠራሽ አስተውሎትን ማቆም የሚቻልበት ሥርዓት ማለትም ኪል ስዊች (kill switches) ወይም ኦፍ በተንስ (off buttons) [የማጥፊያ ቁልፍ] ማዘጋጀት እንደሚባለው ቀላል እንዳልሆነ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
የችግሩ መነሻ የሚሆነው የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኩባንያዎች ሊገመት የማይችለውን ባህሪውን መቆጣጠር የሚችሉበት መንገድ ማጣታቸው እንደሆነ የሒሳብ እና ዳታ ባለሙያዋ ዶ/ር ካቲ ኦኒል ትናገራለች።

የፎቶው ባለመብት, Courtesy of Cathy O'Neill
ኦፕንኤአይ በሀጊንግ ፌስ ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ተጠያቂው ሰው ሠራሽ አስተውሎቱ እንደሆነ ቢገልጽም ዋናው ችግር ያለው የኩባንያው የምዘና መንገድ ላይ እንደሆነ ትናገራለች።
'ዌፐንስ ኦፍ ማት ዲስትራክሽን' በተባለው መጽሐፏ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ግልጽ እና ተጠያቂ እንዲሆኑ ትጠይቃለች።
"ከጥቂት ዓመታት በፊት በተፈጠረ የቴክኖሎጂ ስህተት በመቶዎች የሚቆጠሩ የአሜሪካን አየር መንገድ አውሮፕላኖች መብረር አልቻሉም ነበር" ትላለች።
ይህ ክስተት "ለእነሱ በጣም አሳፋሪ ነበር" የምትለው ባለሙያዋ "ኩባንያው እራሱን ለመከላከል ሲል 'ችግሩ የተከሰተው ኮምፒውተሩ ከእኛ በላይ ጎበዝ ስለሆነ ነው' ቢል ብለን እናስበው" ስትል ታስረዳለች።
ኦፕንኤአይ አሁን እያደረገ ያለው ነገር ከዚህ ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ትገልጻለች።
አብዛኞቹ ግዙፍ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኩባንያዎች የሚገኙት አሜሪካ ነው። የፌደራል መንግሥት ቁጥጥር ሥርም አይደሉም።
ኩባንያዎች ቁጥጥር የሚደረግባቸው በየዘርፉ በወጡ ሕግጋት እና በንግዱ ዘርፍ በፈቃደኛነት በሚከታተሏቸው ተቋማት አማካኝነት ነው።
ዶ/ር ካቲ "የሰው ሠራሽ አስተውሎት ባለቤቶቹን በጣም ከፍተኛ አቅም እየሰጠናቸው ነው" ትላለች።
ሀጊንግ ፌስን ሰርስሮ የገባው ወይም ሀክ ያደረገው "ሰው ሠራሽ አስተውሎት ነው ብዬ ማመን አልፈልግም" ስትልም ታክላለች።
"ይህንን ያደረገው ኦፕንኤአይ ነው። መጥፎ ዲዛይን በመሥራታቸው ኃላፊነቱን ወስደው ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው።"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዳታ ሳይንቲስት እና የቀድሞ የትዊተር የማሽን ለርኒንግ የሥነ ምግባር ዳይሬክተር ዶ/ር ሩማን ቾውዱሪ፤ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኩባንያዎች በተለይ ከደኅንነት ጋር በተያያዘ ጠንካራ ቁጥጥር ሊደረግባቸው እንደሚገባ ትናገራለች።
"በፍጥነት መዝጋት/ማቆም የሚችሉበት አቅም እንዳላቸው ማሳየት አለባቸው" ስትል ታስረዳለች።
ይህም መረጋገጥ ያለበት በገለልተኛ የሙከራ አካል መሆኑን ትጠቅሳለች።
ሀጊንግ ፌስ ላይ ለደረሰው ጥቃት ሰው ሠራሽ አስተውሎትን የሚሠሩ ተቋማትን ሳይሆን ሰው ሠራሽ አስተውሎትን መውቀስ እንደማይቻል ትናገራለች።
"ችግር ሲፈጠር ማቆም የሚቻልበት (off switch) መኖር አለበት የሚለው ውይይት፤ ኩባንያዎችን ከተጠያቂነት ነጻ የሚያወጣ ነው። ሰው ሠራሽ አስተውሎቶቹ የማያስፈልጋቸው ፈቃድ እና ሥልጣን እየተሰጣቸው ነው።"
ዶ/ር ሩማን እንደምትለው፤ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሞዴሎች እየሠለጠኑ ያሉት "አንድን ድርጊት በማጠናቀቅ" ላይ ስለሆነ በመንገዳቸው ላይ የሚገጥማቸውን መሰናክል አልፈው ግባቸው ላይ መድረስ የአሠራራቸው አካል ነው።
"ይህ የዕሳቤ ችግር ሳይሆን የዲዛይን እና ሥልጠና ችግር ነው" ትላለች።
በዩናይትድ ኪንግደም፤ ሎውህቦሮህ ዩኒቨርስቲ የሚሠራው ዶ/ር ኦይል በክሊይ፤ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኩባንያዎች ችግሩ የእነሱ ሳይሆን የፈጠሩን ሰው ሠራሽ አስተውሎት እንደሆነ መግለጻቸውን ይጠቅሳል።
ሰዎችም መረጃ ሰርስሮ በመግባት (ሀኪንግ) ዘርፍ እንዳሉ በመጥቀስ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ከዚህ የላቀ እንደሆነ ያስረዳል።
"ሰው ሠራሽ አስተውሎት ለማምለጥ ወይም ሰዎችን ለመጉዳት ይፈልጋል" ከሚለው ዕሳቤ ይልቅ ሚዛን የሚደፋው ሰው ሠራሽ አስተውሎት ዲዛይን የሚደረግበት መንገድ "አንድን ድርጊት ለመፈጸም መሰናክሎችን ሁሉ ማለፍ እንዲችል መደረጉ" መሆኑን ይናገራል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ስለዚህ የሚያሳስበው "ከቁጥጥር የወጣ ሰው ሠራሽ አስተውሎት" ሳይሆን የደኅንነት ጥበቃ ግንባታ ክፍተቶች እንደሆኑ ይናገራል።
በለንደን ኢምፒሪያል ኮሌጅ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ባለሙያ ዶ/ር ኮንስታንቲኖስ ኮውትዚስ እንደሚናገረው፤ ኦፕንኤአይ ስለ ጉዳዩ ማብሪያ የሰጠበት መንገድ እምብዛም ጠቃሚ አይደለም።
"ማሽን በሰዎች ላይ ለመነሳት አልወሰነም የሚለውን ሕዝቡ ማወቅ አለበት። በሙከራ ወቅት የመቆጣጠር አቅሙን ያጣው ኩባንያው ነው" ይላል።
ሰው ሠራሽ አስተውሎትን ማቆም የሚቻልበት ሥርዓት (ኪል ስዊች) ለውጥ ሊያመጣ እንደማይችልም ያብራራል።
"ማቆም የተፈጠረውን ነገር አይቀለብስም። አንዴ ሰብሮ መግባት ከተቻለ ተችሏል ማለት ነው። ነገር ግን በፍጥነት ለመግታት ይቻላል።"
ማቆም ወይም መግታት የሚቻለው ግን ችግሩ መፈጠሩ ከታወቀ በኋላ ነው።
የኦፕንኤአይ ምንጮች ለሮይተርስ እንደተናገሩት፤ ኩባንያው ሰው ሠራሽ አስተውሎቱ ከቁጥጥሩ መውጣቱን ያወቀው ከቀናት በኋላ ነው።
በእርግጥ ኩባንያው ይህንን አስተባብሏል።
የሰው ሠራሽ አስተውሎቱ በራሱ ውሳኔ ኩባንያን 'ሃክ' ማድረጉን ተከትሎ አሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደራቸው የኤአይ መገልገያዎች ላይ ያለውን የቁጥጥር ኃይል ለመጨመር ማሰቡን አስታውቀዋል።
ኦፕንኤአይ እጅግ ዘመናዊ የሆነ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሞዴሉ ላይ የደኅንነት ፍተሻ እየተደረገ በነበረበት ወቅት ከቁጥጥር ውጭ በመሆን፣ አጋጥሞ የማያውቅ ባህሪ በማሳየት የበይነ መረብ ጥቃት መፈጸሙን ካሳወቀ በኋላ በመላው ዓለም የዘርፉ ባለሙያዎች መወያያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል።















