ኢትዮጵያ ቡክ ፎረም፡ በማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ላይ ለ17 ዓመታት እየተወያዩ ያሉት የመጽሐፍት ወዳጆች

የፎቶው ባለመብት, ARTS TV
ፋሲካ ሲደልል ከአራት ዓመት በፊት "የሻምላው ትውልድ" የተሰኘውን መጽሐፋቸውን ሲያወጡ፤ 'የተጻፈ ይከርማል' የሚለውን ብሒል በመከተል ነበር።
በዚህ መጽሐፋቸው የኢኮኖሚ ጉዳይ ኃላፊ እስከ መሆን ስለደረሱበት የወታደራዊው የደርግ ሥርዓት ከትበዋል።
የመጽሐፋቸው ታሪካዊ ፋይዳም የሚያጠያይቅ አልነበረም። ፋሲካ የከተቡት፣ የጻፉት ሁሉ ግን ከግድፈት የጸዳ አልነበረም። 'የሻምላው ትውልድ'፣ መጽሐፋቸው በርካታ የፊደል ግድፈቶች ነበሩበት። ኋላ ላይ ሲናገሩ "የፊደል ስሕተቱ ከልክ በላይ ነበር። በአንድ ገጽ ላይ ብቻ ሳይ ከ20 በላይ የፊደል ስሕተት አግኝቻለሁ" ብለዋል።
ይህንን ያህል ድግፈት መኖሩን ጆሯቸው ያደረሰው በአንድ ዲጂታል የመጽሐፍት ክበብ ላይ የተነሳ የመረረ ትችት ነው። ይህ የውይይት ክበብ 'ኢትዮጵያ ቡክ ፎረም' ይሰኛል።
ከዲጂታል ክበቡ መስራቾች አንዱ የሆነው የአርትስ ቴሌቪዥን ዋና ሥራ አስኪያጅ ዳንኤል በላይነህ "ልዩ" ብሎ ከሚጠቅሳቸው ውይይቶች አንዱ የሻምላው ትውልድ ላይ የተደረገውን ነው።
ፋሲካ ምን ትችቱ ቢሰላ አልተቀየሙም። "በጣም፣ በጣም ነው የወደድኩት" ሲሉ ክበቡ ባዘጋጀው የአዳራሽ ውይይት ላይ ተናግረዋል።
ወቀሳውን ተቀብለው ብቻም አልቀሩም፤ የሻምላው ትውልድ ሁለተኛ ዕትም እነዚህን ግድፈቶች አርሟል።
ንባብና መጻሕፍት ባሰባሰቧቸው ሰዎች የተመሰረተው ይህ የንባብ ክበብ፣ እስካሁን ከ200 በላይ መጻሕፍት ላይ ውይይት አካሂዷል።
ኢትዮጵያ ቡክ ፎረምን እነማን ጀመሩት?
የኢትዮጵያ ቡክ ፎረም መሠረቱን የተከለው በ2001 ዓ.ም. ገደማ ነው። ከዛሬ 17 ዓመት በፊት። ከመጻሕፍት ጋር ጥሩ ጉርብትና ከንባብ ጋር ጠንካራ ዝምድና ያላቸው ማኀደር ገ/መድህን እና ዳንኤል በላይነህ የተባሉ ሁለት ሰዎች ናቸው በዋናነት የመሰረቱት።
ማኀደር መደበኛ ሞያው አርክቴክት ሲሆን በሸገር ራዲዮ "ከቤት እስከ ከተማ፤የከተማ ማዕከል" የተሰኘ ፕሮግራም አዘጋጅም ነው።
ስለ ኢትዮጵያ ቡክ ፎረም ጅማሮ ሲያስታውስ፤ ለእረፍት ከኢትዮጵያ ውጭ ወደሚኖሩት ወዳጆቹ ሲሄድ ዳጎስ ያሉ መጻሕፍትን በመሸመት ነበር ። ከአዲስ አበባ የሚሸምታቸው መጽሐፍት ካናዳ ለሚኖረው ወዳጁ ዳንኤል እና ለሌሎች አንባቢያን የሚሰጠው ነው።
እሱም እረፍቱን ጨርሶ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስም በተመሳሳይ መልኩ በርከት ያሉ መጻሕፍትን በመሸከም ነው። በዚህ ሁኔታ ንባባቸውን ሲያሳልጡ፣ ባነበቧቸው መጽሐፍት ላይ ሃሳብ ሲለዋውጡ ዛሬ ላይ በቢሊዮን ሰዎች የሚጠቀሙት ፌስ ቡክ ከች አለ። በንባብ ልምዳቸው ላይም አዲስ ነገርን አከለ።
በካናዳ የሚኖረው ዳንኤል በላይነህ ያነበባቸውን መጽሐፍ በተመለከተ ግምገማ (Review) እየፃፈ ማጋራት ጀመረ። ያ ጊዜ ደግሞ እነ ሻማ ቡክስ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ እና ፀሐይ አሳታሚ ድርጅት በርከት ያሉ የአገር ውስጥ መጻሕፍትን ለአንባቢያን ያቀረቡበት ነው።

የፎቶው ባለመብት, Ethiopia Book Forum
በእነዚህ አሳታሚ ድርጅቶች ለአባቢያን ከሚቀርቡ የመጽሐፍ ዓይነቶች ውስጥ ግለ ታሪክ እና በኢትዮጵያ ላይ ያተኮሩ የታሪክ መጻሕፍት የእነ ማህደር ቀዳሚ ምርጫዎች ነበሩ። አብዛኛውን ጊዜ ባነበቧቸው መጻሕፍት ላይ ግምገማ (Review) በመጻፍ በፌስቡክ የሚያጋራው፣ በአሁን ወቅት የአርትስ ቲቪ ሥራ አስፈጻሚው የሆነው ዳንዔል በላይነህ እንደነበር ማኀደር ያስታውሳል። "ከ90 በመቶ በላይ ጽሑፎችን ያጋራው ዳንኤል ነበር" በማለትም ይመሰክራል።
በጊዜ ሒደት በፌስቡክ የሚሰራጨውን የመጻሕፍት ግምገማ የሚከታተል ሰው ቁጥር እየጨመረ መጣ። ዳንኤል ያነበባቸው መጽሐፍት ላይ የተሰማውን ሃሳብ ፌስ ቡክ ላይ ማጋራት የጀመረው "እኔ ያገኘሁትን ደስታ፣ትምሕርት ጓደኞቻችንም ቢያገኙት ከሚል ሃሳብ በመነሳት" መሆኑን ይገልጻል። በኋላም ይህ ሙከራ የኢትዮጵያ ቡክ ፎረም በሚል ስያሜ ራሱን የቻለ ገጽ እንድንከፍት አድርጓል በማለት ተናግሯል። የኢትዮጵያ ቡክ ፎረም የፌስቡክ ገጹ ከተከፈተ በኋላ ባሉት ሁለት ዓመታት 150 የሚሆኑ መጽሐፍቶች መገምገማቸውን (review) ያስታውሳል።
ዳንኤል ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ የኢትዮጵያ ቡክ ፎረም መሥራቾች በአገር ውስጥ በሚዘጋጁ የመጻሕፍት ምረቃ፣ ዐውደ ርዕይ፣ የውይይት መርሃ ግብሮች ላይ መሳተፍ ጀመሩ። ይህ አጋጣሚ እንደ እነ ዓለማየሁ ገላጋይ፣ ሌሊሳ ግርማ፣ አዳም ረታ ያሉ ደራሲያን ጋር በአካል እንዲተዋወቁ በር ከፋች ሆነ።
ወደ 'ክለብ ሃውስ' የተደረገው ሽግግር
በንባብ ወዳጆች ተመስርቶ በፌስቡክ ሲንቀሳቀስ የቆየው "የኢትዮጵያ ቡክ ፎረም"፤ ለሥነ-ጽሑፍ ውይይት ይበልጥ ምቹ ወደሆነው "ክለብ ሃውስ" መተግበሪያ በነሐሴ 2012 ዓ.ም. ሽግግር አደረገ።
መተግበሪያው የውይይት ቡድን ለመመሥረት፣ ድምፅ ለመቅዳት፣ እንዲሁም የጽሑፍ መልዕክቶችን ለመላላክ የሚያስችል በመሆኑ መጻሕፍትን ማዕከል ላደረገው ውይይት እንደመረጡት ማህደር ያስረዳል። የዚህ አዲስ መድረክ ማሟሟሻ ይሆን ዘንድም፣ የመጀመሪያው ውይይት የተካሄደው በደራሲ አዳም ረታ "ግራጫ ቃጭሎች" መጽሐፍ ላይ ነበር።
በኢትዮጵያ ቡክ ፎረም አባላት "በክለብ ሃውስ" ዘወትር እሑድ ከምሽቱ 2፡00 እስከ 4፡00 ሰዓት የሚደረገው ቋሚ የሥነ-ጽሑፍ ውይይት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የሚገኙ በርካታ አንባቢያንን በቀላሉ ለማሳተፍ መንገዱን አቅልሏል።
በበይነ-መረብ በሚካሄደው በዚህ ውይይት ላይ አንጋፋ ደራሲያን ይታደማሉ፤ ለሚነሳላቸው ጥያቄዎችም ምላሽ ይሰጣሉ።
"መደበኛ አንባቢዎች ነን የ ሂስም ሆነ ሥነ-ጽሑፍ ልምድ የለንም"
በክለብ ሃውስ መተግበሪያ ላይ አምስት ዓመታትን ያሳለፈው የኢትዮጵያ ቡክ ፎረም በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ከ5,300 በላይ አባላትን ያፈራ ሲሆን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ መጸሐፍት ተዳስሰው ጠንካራ ትችቶችና አስተያየቶች ተንጸባርቆባቸዋል።
በዚህ የበይነ መረብ ውይይት ጥሩ የንባብ ልምድ ያላቸውና በውይይቶቹ ላይ ያለማቋረጥ ሲሳተፉ የነበሩ አባላት ቋሚ አሰናኞች ሆነው ዛሬ ድረስ ቀጥለዋል።
በየሳምንቱ የሚደረገውን የመጽሐፍ ውይይት የሚመሩት ማህደርን ጨምሮ ምሕረት ታየ፣ ስለሺ ይልማ ዳዊት ብርሃኑ የተባሉ አራት አሰናኞች ሲሆኑ፣ በመደበኛ ሥራቸው አርክቴክት፣ የግራፊክስ ባለሞያ፣ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሞያ፣ እንዲሁም ባንክር ናቸው።
ይህንን የመጻሕፍት ውይይት ከዋና ሥራቸው ጎን በትርፍ ጊዜያቸው እንደሚያከናውኑት የሚናገረው ማህደር፤ "እኛ መደበኛ አንባቢዎች ነን እንጂ የሒስም ሆነ የሥነ-ጽሑፍ ሙያዊ ልምድ የለንም፤ ነገር ግን ሀሳባችንን እናጋራለን›› በማለት የክበቡን መሰረታዊ መንፈስ ያስረዳል።
"አንዳንድ መጽሐፍት አርትኦት ሥሩልን የሚል [ጥያቄ]" እንደሚመጣላቸው የሚያስረዳው ማህደር የሙሉ ጊዜ ሥራችን ስላልሆነ ጥያቄውን አርትኦት ለመሥራት ፍላጎት ላላቸው እንደሚያስተላልፉ አስረድቶናል።

የፎቶው ባለመብት, Ethiopia Book Forum
ከበይነ-መረብ ውይይት እስከ "ቆይታ ከደራሲያን ጋር"
የኢትዮጵያ ቡክ ፎረም አባላት አሁን ላይ ለውይይታቸው የቴሌግራም መተግበሪያ እየተጠቀሙ ይገኛሉ። ሰዎች ውይይቱ ላይ መታደም ባይችሉ እንኳን መተግበሪያው ድምጽን ቀድቶ የሚያስቀምጥ በመሆኑ በተመቻቸው ሰዓት እና ቀን ማድመጥ የሚያስችላቸው ነው።
በዘጠኝ ምዕራፍ ባደረጉት ውይይት እስካሁን በ204 መጻሕፍትን ዳሰሰዋል። ለምርጫ የሚቀርቡት ሁሉም መጽሐፍት በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያውያን ዙሪያ ያተኮሩ በአማርኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች የተፃፉ ናቸው። ውይይት ከተደረገባቸው መጽሐፍት ውስጥ በስፋት የሚገኙት የግለ ታሪክ እና የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያተኮሩ ናቸው። ዳንኤል እነዚህ መጽሐፍት ላይ ትኩረት የተደረገበትን ምክያት ሲያስረዳ "የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ" እንደሚባለው።
እነሱን በደንብ ካልተረዳን የበፊቱን መገመት አንችልም የሚል ነገር ስላለኝ በአብዛኛው በጽሑፍ ሪቪው የተደረጉት መጽሐፎች ግለ ታሪክ በኢትዮጵያውን የተጻፉ የታሪክመጽሐፎች ላይ ነበር" ብሏል። ሆኖም አሁን ላይ ሁሉም አባላት ለውይይት እንዲቀርቡ የሚፈልጓቸውን መጽሐፍት እንደሚመርጡ ገልጿል። "በዚህ ምክንያት ነው ከግለታሪክ እና የኢትዮጵያ ታሪክ ተሻግሮ ልብ ወለድ ትርጉም መጽሐፍት ላይ መወያየት የተጀመረው" ሲል የመጽሐፍት ዘውግ የሚመረጥበትን መንገድ አብራርቷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በበይነ መረብ ውይይቱ አንጋፋ ወጣት ደራሲያንም እየተሳተፉ ይገኛሉ።
"የጭድ እሳት ቆሳስለው የተረፉ ትዝታዎች" መጽሐፍ ደራሲ ፕሮፌሰር ጴጥሮስ ቶጃ መጽሐፋቸው በኢትዮጵያ ቡክ ፎረም አባላት ውይይት ከተደረገበት በኋላ የክበቡ ቤተኛ መሆናቸውን ነግረውናል።
ኑሮአቸውን በአሜሪካ ካደረጉ 46 ዓመት የሆናቸው ፕሮፌሰር ጴጥሮስ "ኩትዝታውን ዩኒቨርስቲ ኦፍ ፔንሲልቬንያ" ውስጥ በ "ክሪሚናል ጀስቲስ" ትምሕርት ክፍል ውስጥ 27 ዓመታት በመምሕርነት አገልግለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Seleshi Yilma FB
ከአራት ዓመት በፊት ባሳተሙት መጽሐፋቸው ላይ የተደረገውን ውይይት "ግሩም እና አርኪ ነበር። በጣም ጠቅሞኛል" በማለት ይገልጹታል። በውይይቱ "በጣም ገንቢ እና ጠቃሚ" አስተያየቶች ተሰጥቶኛል ይላሉ ፕሮፌሰር ጴጥሮስ። ከሆሄያት ግድፈት አንስቶ የመጽሐፉ ድህረ ቃል ላይ የተሰጡ ትችቶችን በመቀበል ሁለተኛ እትም እያዘጋጁ መሆኑን ነግረናል።
ፕሮፌሰር ከልጅነት ዕድሜያቸው አንስቶ ያላችው መጽሐፍት ፍቅር እና የኢትዮጵያ ቡክ ፎረም ላይ የሚደረገው የመጽሐፍት ውይይቱ በበይነ መረብ መካሄዱ በተሳትፏቸው እንዲቀጥሉ አድርጓቸዋል። እንደ እርሳቸው ሁሉ ሌሎች ጸሐፍቶች ኢትዮጵያ ቡክ ፎረምን ተዛምደዋል።
በዚህ ረገድ "ደራሲያን የጻፏቸውን መጽሐፍት የሚያነቡ ጥልቅ አንባቢያን እንዳሉ በግልጽ እንዲያዩ" አድርጓል የሚል እምነት አለው ዳንኤል።
ከዚህ ባለፈ ግን "መጽሐፌን እንዳትተቹ" የሚሉ ደራሲያንም አልጠፉም። በኢትዮጵያ ቡክ ፎረም አባላት የተነሱ ትችቶች ያስቆጣቸው እና ቅር ያሰኛቸው ጸሐፊዎች ስለመኖራቸው መስማቱን ማኅደር ይናገራል።
"አንዳንዶች እናንተ ጋ እንዳትናገሩን [ይላሉ]" ሲል መጽሐፋቸው ላይ ውይይት እንዳይደረግ ቀድመው ስለሚጠይቁ ጸሐፊዎችም ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ አንስቷል።
ኢትዮጵያ ቡክ ፎረም ላይ የሚሳተፉ ደራሲዎች እያደገ መምጣቱ "ቆይታ ከደራሲያን ጋር" የተሰኘ መርሃ ግብር እንዲጀመር ምክንያት ሆናል።
ዝግጅቱ ደራሲያን እና ተደራሲያን በአካል ተገናኝተው ውይይት የሚያደርጉበት፣ የሚጠያየቁበት እና እውቀት እና ልምድ የሚቀስሙበት መድረክ ነው።
በስድስት መድረኮች በተካሔደው ፕሮግራም 20 አንጋፋ እና ወጣት ደራሲያን በዚህ ፕሮግራም ተጋብዘው ከአንባቢያን ጋር ቆይታ አድርገዋል።















