ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የኢትዮጵያ መሪዎች ለግጭቶች ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲፈልጉ ጠየቁ

ዶ/ር ቴድሮስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የኢትዮጵያ መንግሥት እና ክልላዊ መሪዎች በአገሪቱ ላሉት ግጭቶች በንግግር ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲፈልጉ ጥሪ አቀረቡ።

የቀድሞው የኢትዮጵያ የጤና እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ዶክተር ቴድሮስ በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ውስጥ እየተካሄዱ ያሉ ግጭቶች "በዜጎች ላይ መከራ እያመጡ" መሆናቸውን በመጥቀስ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲፈለግላቸው ጠይቀዋል።

ዶክተር ቴድሮስ በይፋዊ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ በአማራ፣ በኦሮሚያ የሚካሄዱ ግጭቶች መቀጠላቸውን፤ በአፋር እና በቤኒሻልጉል ጉሙዝ ክልሎችም ግጭቶች እንዳሉ አመልክተዋል።

"ለሦስት ዓመታት እየተካሄደ ያለው የአማራ ክልል ግጭት የበርካቶችን ሕይወት ቀጥፏል። ኦሮሚያም እየደማች ነው" በማለት በሁለቱ ክልሎች እየተካሄደ ያለው ግጭት እያስከፈለ ያለውን ዋጋ ጠቅሰዋል።

"ትግራይም ወደ ግልጽ ውጊያ ለመግባት እየተንሸራተተች ነው፤ አፋርም ወደዚያው ተስቧል። ቤኒሻንጉል ጉሙዝም በግጭት ውስጥ ነው " ያሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ፣ የአገሪቱ ዋና ዋና ክልሎች በግጭት ውስጥ እና ወደ ግጭት በሚያመራ አቅጣጫ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የግጭት ሁኔታ እንዳሳሰባቸው የገለጹበትን ይህንን መልዕክታቸውን ያጋሩት በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መሪዎች መካከል ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት ባየለበት ወቅት ነው።

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ሐምሌ 25፣ 2018 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር በምትዋሰንበትና ሸረሪና በተባለ ሥፍራ ግጭት መቀስቀሱ የተዘገበ ሲሆን፤ መንግሥት እስካሁን ስለክስተቱ በይፋ ያለው ነገር የለም።

በፌደራል መንግሥቱ የተሾሙትን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በማፍረስ እና "ሕገ ወጥ" በተባለ ምርጫ የተቋቋመውን ምክር ቤት በመመለስ ክልሉን እያስተዳደሩ ያሉት የህወሓት መሪዎች በተለያዩ መድረኮች ላይ ለጦርነት መዘጋጀታቸውን እና በብልጽግና የሚመራውን መንግሥት መጣል ዓላማቸው መሆኑን በይፋ ሲገልጹ ቆይተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የፌደራል መንግሥቱም የህወሓት መሪዎችን ከአገሪቱ ጠላቶች ጋር በመተባበር ለጦርነት እየተዘጋጁ መሆናቸውን በመግለጽ በመገናኛ ብዙኃኑ አማካኝነት ተከታታይ ዘመቻዎችን እያካሄደ ነው።

በአሁኑ ወቅት ያለው የጦርነት ስጋት ያሳሰባቸው የመንግሥታቱ ድርጅት የጤና ተቋም ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ ሁሉም ወገኖች ከግጭት ተቆጥበው ንግግር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የሚካሄደው ግጭት "ይበቃል" ያሉት ዶ/ር ቴድሮስ፣ ጦርነት ሞትን፣ ውድመትን እና ችግርን ብቻ የሚስከትል መሆኑን በመጥቀስ "የፌደራል መንግሥቱ እና ሁሉም የክልል መሪዎች ከጠብመንጃ ይልቅ ንግግርን በመምረጥ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲፈልጉ" ጠይቀዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍሪካ ቀንድ አማካሪ የሆኑት እና የቀድሞው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ ትናንት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ ህወሓት ለወራት ከፌደራል መንግሥቱ ተቃዋሚዎች ጋር የፈጠረውን ወዳጅነት ሲክድ ቆይቶ አሁን በይፋ ከኤርትራ ጋር እየሰራ መሆኑን አምኗል ብለዋል።

አቶ ጌታቸው ህወሓት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የገባውን አለመግባባት ለመፍታት "ምንም ሰላማዊ መንገድ የለም" በማለት ግጭት ለመቀስቀስ ተዘጋጅቷል ሲሉም ከስሰዋል።

"ህወሓት ዓላማው ዳግም ምዕራብ ትግራይን መቆጣጠር አይደለም፤ የብልጽግና መንግሥትን መጣል መሆኑን አመራሮች በግልጽ ተናግረዋል" ሲሉም ወንጅለዋቸዋል።

አቶ ጌታቸው በዚህ የማኅበራዊ ድረ ገጽ ልጥፋቸው የፌደራል መንግሥቱ ለፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ ተግባራዊነት በቁርጠኝነት እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።

አክለውም የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ ትንኮሳዎች ቢፈጸሙበትም ሁሉንም የሰላም አማራጮች ክፍት አድርጎ በመታቀብ እንዲቆይ ጠይቀዋል።

አቶ ጌታቸው ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ባስተላለፉት መልዕክት በድንበር አካባቢ የሚከናወኑ እንቅስቃሴዎችን ሳተላይት በመጠቀም እንዲከታተል፣ ግጭት የሚቀሰቅሱ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮችን ተጠያቂነት እንዲያሰፍን እንዲሁም በቀጣናው ያሉ ሁሉም ወታደራዊ አካላት ሰላማዊ ሰዎችን መጠበቅ ቅድሚያ እንዲሰጡ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ለሁለት ዓመት በህወሓት እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ሲካሄድ የቆየው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተደረሰው የሰላም ስምምነት ሊቋጭ ችሏል።

የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመ አራት ዓመት ሊሞላው በቀረበበት በአሁኑ ወቅት በሱዳን ድንበር አቅራቢያ በሸረሪና የተከሰተው ግጭት ዳግም ጦርነት ይከሰታል የሚለውን ስጋት ከፍ አድርጎታል።

የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት ሌላ ዙር ጦርነት በመቀስቀስ እርስ በእርሳቸው ሲካሰሱ የአፍሪካ ኅብረት እና የተለያዩ አካላት ዳግም ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር "በየቀኑ በርካታ ውጊያ፣ ጦርነት ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ትንኮሳዎች ትግራይ ውስጥ ባሉ ኃይሎች በየጊዜው ይፈጸማል" በማለት ህወሓትን ወንጅለው ነበር።

ሕጋዊነቱን ያጣውን ህወሓት የሚመሩት ደብረፂዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) በቅርቡ ለመቀሌ ነዋሪዎች ባደረጉት ንግግር የፌደራል መንግሥቱን እንደሚገዳደሩ በመግለጽ "ዛሬ እንደበፊቱ ብቻችንን አይደለንም፤ ብዙ ወዳጆች አሉን" ሲሉ ተናግረዋል።

ይህም በህወሓት እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ዳግም ግጭት ከተቀሰቀሰ በጦርነቱ የሌሎች አገራት ቀጥተኛ ተሳትፎ ሊኖር ይችላል የሚል ስጋት እንዲጨምር አድርጓል።

በ2013 ዓ.ም. ተቀስቅሶ ለሁለት ዓመታት በተካሄደው ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሞቱ ሲሆን በሺህዎች የሚቆጠሩ ከቀያቸው ተፈናቅለው በየመጠለያ ጣቢያው ይገኛሉ።

ይህ ጦርነት ካደረሰው ውድመት ያላገገመችው ትግራይ አዲስ ግጭት የሚቀሰቀስ ከሆነ የበለጠ ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ታስተናግዳለች ተብሎም ተሰግቷል።