"አዲስ አበባ እንደ እንግዳ ካልሆነ ከዚህ በኋላ ለመኖር የምመጣ አይመስለኝም"

ዮናስ መኳንንት

የፎቶው ባለመብት, Yonas

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

የሥዕል እና የቅርጻ ቅርጽ ባለሙያ የሆነው ዮናስ መኳንንት፤ ተወልዶ ያደገባትን፣ የእንጀራ ገመዱ የነበረችውን አዲስ አበባን ጥሎ ገጠር ከገባ ከጥቂት ወራት በኋላ ሁለት ዓመት ይሞላዋል።

ዮናስ ከተማን እርግፍ አድርጎ ጥሎ ገጠር እንዲገባ ያደረገው፤ በአዲስ አበባ ተጀምሮ በሌሎች የክልል ከተሞች የተተገበረው የኮሪደር ልማት መሆኑን ይናገራል።

የካቲት 2016 ዓ.ም. በአራት ኪሎ፣ ፒያሳ እና በሌሎችም የከተማዋ ቦታዎች የተጀመረው የኮሪደር ልማት ዮናስ እና ቤተሰቡ ወደሚኖሩበት ዑራኤል አካባቢ የደረሰው ብዙም ሳይቆይ ነበር።

ዋና ዋና መንገዶችን በማስዋብ፣ የእግረኛ መንገድን በማስፋት እንዲሁም የመዝናኛ ቦታዎችን በመገንባት ላይ በሚያተኩረው በዚህ ፕሮጀክት ሳቢያ፣ "ከቤተሰቤ ጋር የምኖርበት ቤት ፈረሰ" ይላል ዮናስ።

ይህ አጋጣሚ ታዲያ ብዙ ጊዜ ሲያስበው የነበረውን፣ ግን ደግሞ ሊሳካ ያልቻለውን ከተማን ጥሎ የመውጣት ምኞቱን ዕውን አደረገለት።

ለማረፊያነትና ለኑሮ የመረጣት አካባቢ ደግሞ በአማራ ክልል ከጣና ሐይቅ ዳር የምትገኘውን ጎርጎራን ነበር።

ዮናስ በወቅቱ "እጄ ላይ ሁለት ምርጫዎች ነበሩኝ፤ ገጠር መግባት አሊያም ከአገር መውጣት" ይላል።

ምንም እንኳን ከአገር የመሰደዱን ምርጫ ማድረግ የሚችለው ቢሆንም፣ አላደረገውም። "እውነቱን ለመናገር እኔ ከአገር መውጣት አልፈልግም።

ኬንያ እና ኡጋንዳ ውስጥ የማውቃቸው የአርት ጋለሪዎች ነበሩ። 'መምጣት ትችላላችሁ፣ አብረን እንስራ' እያሉ ከድሮም ይጋብዙን ነበር። ብድግ ብለን መሄድ እንችል ነበር፤ በደስታ ነው የሚቀበሉን" ሲል ይናገራል።

ዮናስ መኳንንት

የፎቶው ባለመብት, Yonas

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዮናስ ከአገር መውጣት ያልፈለገበትን ዋነኛ ምክንያት ሲያስረዳ፣ እንደ አንድ የሥነ ጥበብ ባለሙያ አገርን ጥሎ አለመሄድንና አለመሸሽን ማስተማር ስለሚፈልግ መሆኑን ይገልጻል።

"አገር ደስ ሲልህና ሲደላህ የምትኖርበት፣ ከፋኝ ብለህ ጥለህ የምትሄደው አይደለም። በክፉ ሰዓት ነው ለአገርህ መገኘት ያለብህ፤ በደላው ሰዓትማ ሁሉም ሰው የሚሰበሰብበት ነው" በማለት ወደ ገጠር መግባት የመረጠበትን ምክንያት ያስረዳል።

በዚህ ውሳኔው መሠረት ጥር 6/2017 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ወደ ጎንደር የመጀመሪያ ጉዞውን አደረገ። የአማራ ክልል ላለፉት ዓመታት በግጭት ውስጥ መቆየቱ፣ ጉዞው ሦስት ቀናትን እንዲወስድበት አስገድዶታል።

በጉዞው ላይ ጓዝ አላበዛም፤ ለሥዕል ሥራ የሚሆኑ ግብዓቶችን፣ ጎን ማሳረፊያ አልጋንና ዛሬ ድረስ አብረውት ያሉትን ውሾቹን ብቻ ይዞ ተጓዘ።

ጎንደር ከደረሰ በኋላ የተወሰኑ እቃዎችን ጨምሮ ወደ ጎርጎራ በማቅናት፣ ለጎረቤት አደራ ተሰጥቶና ለ11 ዓመታት ተዘግቶ የቆየውን የአያቶቹን ቤት ከፍቶ ገባ። ከለመደው የከተማ ጫጫታ ተነጥሎ ጸጥታ ባረበበት መንደር መኖር ጀመረ።

"እኔ እዚህ ከመጣሁ ትልቅ እረፍት ነው የሚሰማኝ። በጣም ሰላማዊ ቦታ ነው፤ ምንም ዓይነት የመኪና ድምጽ የለም፣ የምትሰማው የእንስሳት ድምጽ ብቻ ነው። የስቱዲዮ አርቲስት መሆኔ ደግሞ ብዙ ነገር አቅልሎልኛል" ይላል ዮናስ ከቤተሰብ እና ከቀዬ ተነጥሎ መኖር አልከበደህም ወይ? ሲል ቢቢሲ ለጠየቀው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጥ።

አብዛኛውን ጊዜ ሥራዎቹን የሚያከናውነው ለረጅም ሰዓት ከስቱዲዮ ሳይወጣ በመሆኑ፣ አያቶቹ ቤት ውስጥ ብቻውን መኖር ከጀመረ በኋላ ብዙ ጊዜውን ከቤት ሳይወጣ ያሳልፍ ነበር። ይሁን እንጂ የቤተሰቦቹ እና የባልንጀራዎቹ ናፍቆት፣ እንዲሁም የብቸኝነት ስሜት ፈታኝ ሆኖበት ነበር።

ዮናስ መኳንንት

የፎቶው ባለመብት, Yonas

ይህንን የብቸኝነት ስሜትና ናፍቆት ያስረሳው ግን "የቲክቶክ ማኅበረሰብ" መሆኑን ይናገራል። በማኅበራዊ ሚዲያ ከተዋወቃቸው ወዳጆቹ ጋር በመመካከር ሕይወቱ በፍጥነት መስመር መያዝ እንደቻለ ያስታውሳል።

በተለይ የየዕለት ኑሮውን፣ አዲሱን ቀዬ ለመልመድ የሚያደርገውን ጥረት እየቀረጸ በማኅበራዊ ሚዲያ ማጋራት ከጀመረ በኋላ በርካታ ወዳጆችን አፍርቷል።

ኑሮውን ማጠናከር ችሏል። ከእነዚህ ወዳጆቹ ጋር በመመካከር በአያቶቹ ግቢ እንስሳቶችን ማርባት ጀመረ። በሥነ ጥበብ ሙያው ይታወቅ የነበረው ዮናስ ሁለቱን እጆቹን ወደ ግብርናው አስገባ።

ከዶሮ አንስቶ በግ፣ ፍየል፣ አህያ፣ ፈረስ እና ከብት የመሳሰሉ የቤት እንስሳትን ማርባት ጀመረ።

በጎችና ፍየሎቹ ከ20 በላይ ደርሰው የነበረ ቢሆንም፣ በገጠማቸው ወረርሽኝ ምክንያት በአንድ ሳምንት ውስጥ ሁሉም አለቁበት።

በተመሳሳይ ከ50 ዶሮዎች ሦስት ብቻ ቀሩት። ይህ አጋጣሚ የገበሬን ሕይወትና ፈተና በደንብ እንድረዳው አድርጎኛል የሚለው ዮናስ፣ "ገበሬ ሁሌም የሚኖረው እንዲህ ነው፤ ወረርሽኝ ይመጣል እንስሳትን ይገልብሃል፣ በሚቀጥለው ደግሞ ታረባለህ መልሰው ይበዛሉ። አሁን ለምጄዋለሁ፣ መደንገጥ አቁሚያለሁ፤ የገበሬ ፈተና ነው" በማለት ገጠመኙን በጸጋ መቀበሉን ይገልጻል።

ከዚህም ባሻገር ዮናስ በማኅበራዊ ሚዲያ ከተዋወቃቸው ጓደኞቹ ጋር በመሆን ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው ማኅበረሰብም ጠቃሚ ሥራዎችን መሥራት ችሏል።

ከ500 ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ የመለዋወጫ እቃ በመግዛት ተበላሽቶ የነበረውን የአካባቢውን የመጠጥ ውኃ ማውጫ ፓምፕ እንዲሰራ አድርገዋል።

ለተማሪዎች ደብተርና የንጽህና መጠበቂያዎችን ለግሰዋል፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የአቅመ ደካማ ሰዎችን ቤት በማደስ ላይ ይገኛሉ።

ይህንን በጎ አድራጎት አብረውት የሚያከናውኑት የማኅበራዊ ሚዲያ ወዳጆቹ ጎርጎራ ድረስ በመሄድ በአካል አግኝተውታል።

እሱ በሠራው ጀልባ ጣና ሐይቅ ላይ በመንሸራሸር፣ እርጋታና ጸጥታ ካረበበት የገጠር ኑሮም ተቋድሰዋል።

ባለፈው ዓመት ብቻ ከ50 በላይ ሰዎች ጎርጎራ ድረስ በመሄድ ከዮናስ ጋር ተገናኝተዋል። በመኖሪያ ቤቱ ተስተናግደዋል።

በመጨረሻም ዮናስ ዳግም ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ የመኖር ዕቅድ እንደሌለው ሲናገር፣ "አዲስ አበባን እንደ እንግዳ ካልሆነ ከዚህ በኋላ ለመኖር የምመጣ አይመስለኝም። ምን አለኝ? ከዜሮ ለመጀመር ካልሆነ በስተቀር ምን ቀርቶኛል?" ይላል።

አሁን ላይ ትልቁ ዕቅዱ በሚኖርባት በጣና ዳር ባለችው ጎርጎራ፣ ግዙፍ የሥነ ጥበብ ስቱዲዮ መክፈትና ማስተማር፣ እንዲሁም አካባቢውን ሰፊ የቱሪዝም መዳረሻ ማድረግ መሆኑን ገልጿል።