ትራምፕ ለሕፃናት የሚሰጡ ክትባቶችን ብዛት ለመቀነስ የሚያስችል ትዕዛዝ ፈረሙ

ትራምፕ እና ኬኔዲ ጁኒየር በኦቫል ኦፊስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ለሕፃናት የሚሰጡ ክትባቶችን ብዛት የሚቀንስ እንዲሁም በአንድ ክትባት ይሰጡ የነበሩት የጆሮ ደግፍ፣ የኩፍኝ እና የጉድፍ መከላከያዎች (ኤምኤምአር) ለየብቻ እንዲሰጡ የሚመክር ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ፈርሙ።

"ከአስርተ ዓመታት በፊት [የተወለዱ] ሕፃናት የወሰዱት ክትባት ዛሬ ከሚያስፈልቸጋው በጣም ጥቂት ነው" ያሉ ትራምፕ፣ በዚያን ጊዜ ሰዎች የተሻለ ጤናማ እንደነበሩ እና አሁን የሚታየው ከፍተኛ የኦቲዝም ችግር እንዳልነበር ገልጸዋል።

ፕሬዚደንቱ ኤምኤምአር ክትባቶች ደኅንነት ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ ለረዥም ጊዜ ሲገልጹ ቆይተዋል። በርካታ ጥናቶች ግን ክትባቶቹ እና የአዕምሮ እድገት ውስንነት የሚያገናኛቸው ነገር እንደሌለ አመልክተዋል።

ሆኖም ፕሬዚደንት ትራምፕ ለሕፃናት የሚሰጠው ክትባት ቁጥር ከነበረውና በአሜሪካ ፔዲያትሪክስ አካዳሚ (ኤኤፒ) ከሚመከረው 18 ወደ 11 ዝቅ እንዲል መክረዋል።

ትራምፕ ሰኞ ዕለት በኦቫል ኦፊስ በተናገሩበት ወቅት አስተዳደራቸው "በጣም ከባድ እና አደገኛ የሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ለሚረዱ 11 ዋና ዋና ክትባቶች ብቻ የወርቅ ደረጃ እውቅና መስጠቱን ተናግረዋል።

ክትባቶቹ ጆሮ ደግፍን፣ ቴታነስ፣ ፖሊዮ፣ ሄሞፊለስ ኢንፉሌንዛ ቢ፣ ኩፍኝ፣ ሂውማን ፓፒሎማቫይረስ፣ ፈንጣጣ፣ ሩቤላ፣ ዲፍቴሪያ፣ ፔርቱሲስ እና የሳምባ በሽታን ለመከላከል የሚረዱ ናቸው።

"ክትባቶቹን እየቀነስናቸው ነው" ያሉት ትራምፕ፣ ቁጥሮቹን መቀነስ ብቻ ሳይሆን ክትባቶቹ በተከታታይ በተለያየ ጊዜ እንደሚሰጡም ተናግረዋል።

የኤምኤምአር ክትባት በአንድ ጊዜ ከተሰጠ "በጣም ገዳይ" ሊሆን እንደሚችል የጠቆሙት ፕሬዚደንቱ፣ የክትባቱን አሰጣጥ በሕፃናት አካል ውስጥ አንድ ጠርሙስ የለስላሳ መጠጥ ከማፍሰስ ጋር አነፃፅረውታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ክትባቶቹ እንዴት "ገዳይ" እንደሆኑ ማስረጃ እንዳላቸው በጋዜጠኞች የተጠየቁት ትራምፕ "አንዳንድ ሰዎች እንደዛ እንደሆነ ሲናገሩ ሰምቻለሁ" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

እንደ የአሜሪካ በሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል (ሲዲሲ) መረጃ፣ ኤምኤምአር ክትባት በልጆች ላይ የሚያስከትለው ትኩሳት እንኳ በጣም አነስተኛ ነው።

ከባድ የሆነ አለርጂ ወይም የተዳከመ የበሽታ መከላከያ ሥርዓትን ጨምሮ የጤና ችግሮች ያለባቸውም ክትባቱን ከመውሰዳቸው በፊት የጤና ባለሙያዎችን እንዲያማክሩ ይነገራቸዋል።

ማዕከሉ ኤኤምአር ክትባት የወሰዱ አብዛኞቹ ሰዎች ከክትባቱ ጋር በተያያዘ የገጠማቸው ችግር እንደሌለም ጠቅሶ፣ ክትባቱን መውሰድ በኩፍኝ ፣ በጆሮ ደግፍ ወይም በጉድፍ ከመያዝ የተሻለ እንደሆነ ገልጿል።

በአንድ ላይ ይሰጡ የነበሩትን ክትባቶች ነጣጥሎ በሦስት ክትባት ለየብቻ መስጠቱ የሚያስገኘው ጥቅም እንዳለ የሚያሳይም ምንም ዓይነት ሳይንሳዊ መረጃ እንደሌለም ሲዲሲ አመልክቷል።

ይልቁኑ በክትባቶቹ መሃል የሚፈጠረው የጊዜ ክፍተት ሕፃናቱ በበሽታዎቹ እንዲያዙ ሊያደረግ ወይም በተደጋጋሚ ክትባቶች ምክንያት ቀጠሯቸውን ሊያሳልፉ እንደሚችሉ ባለሙያዎች ተናግረዋል።

የትራምፕ የጤና እና ሰዎች አገልግሎት ሚኒስትር ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ጁኒየር በበኩላቸው የታቀደው ለውጥ በወላጆች ምርጫ የሚሰጥ እንጂ ሕፃናት ክትባት እንዳያገኙ ለማድረግ ያለመ አይደለም ብለዋል።

ሚኒስትሩ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የክትባት ደንቦችን ለመቀየር እና ለማላላት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ባለፈው ሳምንትም ከሲኤንኤን ጋር ባደረጉት የ20 ደቂቃ ቃለ መጠይቅ "የኤምኤምአር ክትባትን ውጤታማነት በፍፁም ጥያቄ ውስጥ አላስገባም" ብለዋል።

የትራምፕ አስተዳደር ባለሥልጣናት እንዳሉት፣ ትዕዛዙ አሜሪካ ውስጥ ያሉ ሕፃናት ከዚህ ቀደም ሲሰጡ ከነበሩት 72 ክትባቶች ያነሰ ቁጥር ያለው የመከላከያ መድኃኒት እንዲወስዱ ያደርጋል። በቀድሞው የክትባት መርሃ ግብር የኮቪድ -19 እና የጉንፋን ክትባቶችን ጭምር ተካትተው ነበር።

የአሜሪካ ፔዲያትሪክስ አካዳሚ ፕሬዚደንት ዶ/ር አንድሪው ሬሲን ግን የትራምፕን ፕሬዚደንታዊ ትዕዛዝ " አደገኛ" እና " በሳይንስ ላይ ያልተመሰረተ" ብለውታል።

" ክትባቶችን መዝለል እና ማዘግየት አደጋ አለው። በተለይ የኩፍኝ በሽታ እየተሰራጨ እና ሕፃናት ወደ ትምህርት ቤት እየተመለሱ ባሉበት በአሁኑ ሰዓት" ብለዋል።

የሪፐብሊካን ሴናተር ቢል ካሲዲም " ትራምፕ ትዕዛዙን ለማስተላለፍ የሚያስችል ሙያው የላቸውም" ሲሉ ትዕዛዛቸውን "ስህተት" ብለውታል።

የጤና ባለሙያ የሆኑት ካሲዲይ በኤክስ ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ፅሑፍ " ክትባቶች ደኅንነታቸው የተጠበቀ ነው፤ ክትባቶች ውጤታማ ናቸው፤ ክትባት ኦቲዝም አያስከትልም።" ብለዋል።

ባለሙያዎችም ለሕፃናት የሚሰጥ ክትባት ኦቲዝም ያስከትላል በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ወላጆች ልጆቻቸውን ከማስከተብ ሊቆጠቡ ይችላሉ የሚል ስጋት ፈጥሮባቸዋል። በርካታ ጥናቶች የኤምኤምአር ክትባት ከኦቲዝም ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው አሳይተዋል።