ሩሲያ በማንኛውም ቅጽበት ዩክሬንን ልትወር እንደምትችል አሜሪካ አስጠነቀቀች

የፎቶው ባለመብት, EPA
ሩሲያ ዩክሬንን ለመውረር ሁሉን ነገር አጠናቃለች ስትል አሜሪካ አስጠነቀቀች፡፡
እንደ አሜሪካ ባለሥልጣናት ከሆነ ሩሲያ ወታደሮቿን ከዛሬ ጀምሮ በማንኛውም ቅጽበት ልታንቀሳቅስና ወረራውን ልትፈጽምት ትችላለች፡፡
በመሆኑም ዜጎቿ ጨርቄን ማቄን ሳይሉ በሚቀጥሉት 48 ሰዓታት አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ መክራለች፡፡
ወረራው የሚጀምረው በአየር ድብደባ ሊሆን እንደሚችልም የተነበየች ሲሆን ይህም የሚያመላክተው ጦርነቱ አንዴ ከተጀመረ በኋላ ከሩሲያ ምድር መልቀቅ ቀላል እንደማይሆን ነው፡፡
ሞስኮ በአንጻሩ ወረራ የሚባል ነገር በሐሳቤም የለም ትላለች፡፡
ይሁንና ከ100 ሺህ የሚልቁ ወታደሮቿን ወደ ዩክሬን ድንበር ማስጠጋቷን አላስተባበለችም፡፡
ከአሜሪካ ባሻገር ሌሎች የምዕራብ አገራትም ዜጎቻችን እባካችሁ የሩሲያ ምድርን ልቀቁ ሲሉ መክረዋል፡፡
ዩኬ፣ ካናዳ፣ ኔዘርላንድስ፣ ላቲቪያ ለዜጎቻቸው መመሪያን የሰጡ ሲሆን ጃፓንና ደቡብ ኮሪያም ዜጎቻችን ከሩሲያ ብትወጡ ነው የሚሻለው ሲሉ መክረዋል፡፡
የሩሲያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ምዕራብ አገራት ሐሰተኛ ዜና እያሰራጩ ሕዝብ ያሸብራሉ ሲል ከሷል፡፡
የአሜሪካ የብሔራዊ ደኅንነት ከፍተኛ አማካሪ ጄክ ሰሊቫን "በሚቀጥሉት ደቂቃዎች ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ከባድ ነው፤ የሩሲያ ወታደሮች ጥቃት ለመሰንዘር ተጠንቀቅ ላይ ናቸው" ብለዋል፡፡
የደኅንነት አማካሪው ጨምረው፣ ቭላድሚር ፑቲን በወረራው ዙርያ የመጨረሻ ውሳኔ ይስጡ አይስጡ አሜሪካ መረጃ የላትም ያሉ ሲሆን፣ ይሁንና ክሬምሊን ወረራውን ቅቡል ለማድረግ አንድ አሳማኝ ሰበብ እየፈለገች መሆኑን መረጃ እንዳላቸው አብራርተዋል፡፡
የደኅንነት አማካሪው ጄክ ሩሲያ የመጀመርያውን ጥቃት የምትሰነዝረው ከአየር እንደሆነ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊከን የሩሲያ ጠብ አጫሪነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ቀደም ሲል ተናግረው ነበር።
ብሊንከንም በተመሳሳይ የሩሲያ ጥቃት በማንኛውም ቅጽበት ሊጀመር እንደሚችል ጠቁመው በተለይ በፌብሩዋሪ 20 የኦሎምፒክ ፍጻሜ ዕለት ሊሆን እንደሚችል ምልክቶች እንዳሉ አብራርተዋል፡፡
አሜሪካ ለዚህ ጥቃት ምላሽ 3 ሺህ የሠራዊት አባላትን ከኖርዝ ካሮላይና ቀጠና ወደ ፖላንድ አንቀሳቅሳለች፡፡
ይሁንና እነዚህ ወታደሮች ከዩክሬን ወታደሮች ጋር ተሰልፈው አይዋጉም ተብሏል፡፡ ሆኖም ከአጋር አገራት ጋር ኾነው በተጠንቀቅ አካባቢውን ይቃኛሉ የሚል ግምት አለ፡፡
የፈረንሳዩ ማክሮን ከሰኞ ጀምሮ፣ ኪያቭ፣ ሞስኮና በርሊን ሲመላለሱ ነው የሰነበቱት፡፡
የማክሮን ወዲያ ወዲህ ማለት አይቀሬ ነው ለሚባለው ጦርነት የዲፕሎማሲ መፍትሄ ለመሻት ነበር፡፡
አንጌላን የተኩት የጀርመኑ መራሒ መንግሥት ሾልዝ በበኩላቸው ማክሰኞ ዕለት በዋሺንግተን ከባይደን ጋር መክረው ሩሲያ እንደተፈራው ወረራ ከፈጸመች በምን መልኩ ልንቀጣት ይገባል በሚለው ላይ ከመግባባት ደርሰው ነው የተመለሱት፡፡
በሚቀጥሉት ቀናት የፈረንሳዩ ማክሮንና የአሜሪካው ባይደን ከቭላድሚር ፑቲን ጋር የመጨረሻ ሊሆን ይችላል የተባለ ምክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሩሲያ በተለይ የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት በምህጻሩ ኔቶ፣ ወደ ምሥራቅ አውሮጳ አይስፋፋብኝ፣ በተለይ ደግሞ ባላንጣዬን ዩክሬንንም አባል አድርጎ አይመዝግባት ስትል በጥብቅ ስትጠይቅ ኖራለች፡፡
ይህ ቁልፍ የደኅንነት ጥያቄዋ ግን በምዕራብ አገራት ገሸሽ ሲደረግባት ነው የኖረው፡፡












