የዩክሬን ውጥረት፡ ባይደን አሜሪካውያን በፍጥነት ዩክሬንን ለቅቀው እንዲወጡ አሳሰቡ

የፎቶው ባለመብት, AFP VIA GETTY IMAGES
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዩክሬን የቀሩ አሜሪካውያን በሙሉ የሩሲያ ወታደራዊ እርምጃ ስጋት በመጨመሩ ምክንያት ሃገሪቱን በአስቸኳይ ለቅቀው እንዲወጡ አሳስበዋል።
ሞስኮ ዩክሬንን ከወረረች አሜሪካውያንን ለመታደግ ጦር አልክም ብለዋል ባይደን።
በአካባቢው "ነገሮች በፍጥነት ሊባባሱ ይችላሉ" ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
ሩሲያ በድንበር አካባቢ ከ100 ሺህ በላይ ወታደሮቿን ብታሰፍርም ዩክሬንን የመውረር እቅድ እንዳሌላት በተደጋጋሚ ገልጻለች።
ሃገሪቱ ከቤላሩስ ጋር ግዙፍ ወታደራዊ ልምምዶችን የጀመረች ሲሆን ሩሲያ የባህር ዳረቻዬን ዘግታዋለች ስትል ዩክሬን ትከስሳለች።
ክሬምሊን ጎረቤቷ ዩክሬን ኔቶን እንደማትቀላቀል ለማረጋገጥ "ቀይ መስመር" ማስመር እፈልጋለሁ ብላለች።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ትናንት ሐሙስ እንደተናገሩት አውሮፓ በአስርት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛውን የፀጥታ ችግር ተደቅኖባታል።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዩክሬን የሚገኙ አሜሪካውያን ሃገሪቱን በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ አሳስቧል።
ባይደን ለኤንቢሲ ኒውስ "አሜሪካውያን ዜጎች አሁኑኑ መልቀቅ አለባቸው" ብለዋል።
"በዓለም ላይ ካሉት ትላልቅ ጦሮች አንዱ ጋር እየተፋጠጥን ነው። በጣም የተለየ ሁኔታ በመሆኑ ነገሮች በፍጥነት ሊባባሱ ይችላሉ።"
አሜሪካውያንን ለማስወጣት ጦር የመላክ ዕድል አለ ወይ ተብለው የተጠየቁት ባይደን፤ "የለም። አሜሪካ እና ሩሲያ እርስ በርስ መታኮስ ሲጀምሩ የዓለም ጦርነት ይሆናል። ከዚህ ቀደሙ በተለየ ሁኔታ ውስጥ ነን" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የዓለም መሪዎች በዩክሬን ላይ የተፈጠረውን ቀውስ ለማርገብ የዲፕሎማሲ ጥረታቸውን ቀጥለዋል።
ሩሲያ እና ዩክሬን ግጭት ለማስቆም ከፈረንሳይ እና ከጀርመን ባለስልጣናት ጋር ባደረጉት ድርድር ምንም አይነት ለውጥ ማምጣት እንዳልቻሉ ሐሙስ ረፋድ ላይ አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ቀደም ብለው "ጠንካራ መከላከያ" እና "ትዕግስት የተሞላበት ዲፕሎማሲ" ቀውሱ እንዲረግብ መንገድ እንደሚያስገኙ ተስፋ አድርገው ነገር ግን ጉዳቱ "በጣም ከፍተኛ" ነው ብለዋል።
ጆንሰን በብራስልስ ከኔቶ ዋና ፀሐፊ ጄንስ ስቶልተንበርግ ጋር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሩሲያ ዩክሬንን ለመውረር ወስናለች ብለው ባያምኑም የእንግሊዝ የስለላ ድርጅት በጉዳዩ "መጨነቁን" ገልጸዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም ሩሲያ ወረራ ከፈጸመች ወታደራዊ ድጋፍን ጨምሮ ለዩክሬን የምታደርገውን ድጋፍ ለማጠናከር ታስብ እንደሆነ የተጠየቁት ጆንሰን "ከዚህ በላይ የምናቀርበውን ነገር ግምት ውስጥ እናስገባለን" ብለዋል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ከብሪታኒያ አቻቸው ሊዝ ትረስ ጋር በሰጡት መግለጫ ውይይቱ "አሳዛኝ" ነበር ብለዋል።
በዩናይትድ ኪንግደም እና በሩሲያ መካከል ያለው ግንኙነት "ባለፉት ጥቂት ዓመታት በዝቅተኛው ደረጃ ላይ ነው" ብለዋል።
ትረስ በበኩላቸው ሩሲያን "በቀዝቃዛ ጦርነት ንግግሮች" ከሰዋታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሩሲያ ለባህር ኃይል ልምምድ የባህር በሬን ዘግታለች ስትል ዩክሬን ከስሳለች።












