'ምዕራባዊያን ሩሲያን እንዳያስቆጡ እመክራለሁ' በአውሮጳ የሩሲያ አምባሳደር

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአውሮጳ የሩሲያ አምባሳደር ቭላድሚር ቺዞፍ ምዕራባዊያን ሩሲያን እንዳያስቆጡ አሳሰቡ፡፡
አምባሳደሩ አሁን የተፈጠረውን ችግር ለማርገብ የዲፕሎማሲ ዕድል እንዳለም ጠቁመዋል፡፡
አምባሳደር ቭላድሚር ቺዞፍ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት ሁኔታዎችን በጥንቃቄና በብስለት ዲፕሎማሲን ተጠቅሞ ማርገብ እንጂ ሩሲያን ማስቆጣት አደጋው የከፋ እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል።
ሩሲያ ከተቆጣች ደግሞ የዲፕሎማሲ ሐሳቧን እርግፍ አድርጋ ልትተወው ትችላለችም ብለዋል፡፡
ባለፉት ቀናት በሩሲያና በምዕራብ አገራት መካከል ከፍተኛ ውጥረት እንደነበረ አይዘነጋም፡፡
የፈረንሳዩ ኢማኑኤል ማክሮን ሰኞና ማክሰኞ ዕለት ኪያቭና ሞስኮ በመመላለስ ከዚያም ደግሞ ወደ በርሊን በመብረር ሁኔታዎችን ለማርገብ ሲተጉ ሰንብተዋል፡፡
ከቭላድሚር ፑቲን ጋር 6 ሰዓታት የወሰደ ንግግርና ምክክር በማድረግም ወረራ እንደማይደረግ ፑቲን ቃል ገብተውልኛል ሲሉ ተስፋን ለዓለም ማብሰራቸው አይዘነጋም፡፡
አሜሪካ በበኩሏ ሩሲያ ዩክሬንን ለመውረር ድንበር ላይ 100ሺህ ወታደር ማሰለፏን በመጥቀስ ወረራው በማንኛውም ቅጽበት ሊደረግ ይችላል ስትል ማስጠንቀቋ ይታወሳል፡፡
ባለሥልጣናቷም ፑቲን ዩክሬንን ለመውረር ከሚያስፈልጋቸው የወታደር ኃይል 70 በመቶው በድንበር ሰፍሮ እንደሚገኝ ሲናገሩ ነበር፡፡
የደኅንነት ባለሥልጣናት በበኩላቸው ሩሲያ ወረራውን ተአማኒና ቅቡል ለማድረግ ሐሰተኛ ፊልም እየቀረጸች እንደሆነ መረጃ እንደደረሳቸው ለዓለም ይፋ ያደረጉት ባለፈው ሳምንት ነበር፡፡
ጆ ባይደን በበኩላቸው ሰኞ ዕለት አዲሱን የጀርመን መራሒ መንግሥት በዋሺንግተን ተቀብለው ያስተናገዱ ሲሆን ሩሲያ ወረራ ከቃጣት ምን ዓይነት ቅጣቶች ሊጣሉባት እንደሚችሉ መክረዋል፡፡
በተለይም ሩሲያን ክፉኛ ያሽመደምዳታል ብለው የገመቱትን የኖርዲክስ ስትሪም2 የጋዝ ማስተላለፊያ ለመዝጋት እንደማያመነቱ ሁለቱ መሪዎች ቃል ሰጥተው ነበር፡፡
ሩሲያ የዛሬ 8 ዓመት ግድም ነበር የዩክሬንን ደቡባዊ ክፍል፣ የክሬሚያ ባሕረ ገብን በወረራ የያዘቸው፡፡
ከሰኞ ወዲህ የዲፕሎማሲ ጥረቱ ተስፋ ሰጪ እየኾነ የመጣ ቢመስልም ዛሬ ሐሙስ ሩስያ ከሰሜናዊት ጎረቤቷ ቤላሩስ ጋር ወታደራዊ ልምምድ እንደምትጀምር አስታውቃለች፡፡
በዚህ ልምምድ 30ሺህ የሚኾኑ ወታደሮቿ እንደሚሳተፉ ተነግሯል፡፡ ቤላሩስ የፑቲን ቀኝ እጅ ናት፡፡
ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት በአውሮጳ የሩሲያ አምባሳደር ቭላድሚር ቺዞፍ ግን የሩሲያ ወታደሮች ከቤላሩስ ጋር ልምምድ ካደረጉ በኋላ ወደ አገራቸው ቋሚ የጦር ሰፈር እንደሚመለሱ ተናግረዋል፡፡
አሜሪካ ይህ ወታደራዊ ልምምድ ሁኔታዎችን ለማርገብ የሚደረግን ጥረት የማንኳሰስ ያህል ነው ስትል ተችተዋለች፡፡
ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የጀመሩት የዲፕሎማሲ ጥረት ፍሬ ማፍራት እንደሚጀምር እየተጠበቀ ሲሆን በተለይ የሚኒስክ ስምምነት አሁን ለተፈጠረው ውጥረት እንደ መፍትሄ ሊወሰድ እንደሚችል ፍንጮች አሉ፡፡
ይህ ስምምነት በ2014 ሩሲያ ክሪሚያን ከተቆጣጠረች በኋላ የተደረሰ አዲስ ስምምነት ሲሆን የደቡባዊ ዩክሬን አካባቢ በሩሲያ በሚደገፉ አማጺያን እንዲተዳደር ያደረገ ስምምነት ነው፡፡
ይህን ስምምነት ፈረንሳይና ጀርመን ያሸማገሉትና የፈረሙበት ስምምነት ነው፡፡
የአሁኑ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ይህ ስምምነት ለሩሲያ ያደላ ነበር ሲሉ እምብዛምም አይቀበሉትም፡፡
ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት አምባሳደር ቺዞፍ የዲፕሎማሲ ጥረቱ እንዳለ ሆኖ ሩሲያ ግን ለጊዜው ወታደሮቿን ከድንበር ፈቀቅ የማድረግ ፍላጎት እንደሌላት አረጋግጠዋል፡፡
"ሁሉም ሚዲያ የሩሲያ ወታደሮች ወደ ዩክሬን ድንበር ስለመጠጋታቸው ያወራል፡፡ ወደ ሩሲያ ፊታቸውን ስላዞሩ የዩክሬን ወታደሮችስ ለምን አይወራም?" ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ሩሲያ ለምዕራብ አገራት ሰላም እንዲሰፍን በርካታ ቅድመ ሁኔታዎችን ያስቀመጠች ሲሆን ከነዚህ መሀል ዋነኞቹ የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ወደ ምሥራቅ አውሮጳ መስፋፋቱን እንዲያቆም፣ በተለይ ደግሞ በፍጹም ዩክሬንን በአባልነት እንዳይቀበል የሚሉ ይገኙበታል፡፡
ይህን የሩሲያን ጥያቄ ምዕራብ አገራት ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርገውታል፡፡
ከቢቢሲ ጋር ቆየታ የነበራቸው በአውሮጳ የሩሲያ አምባሳደር ይህ ጥያቄ ቁልፍ ጉዳይ ነው፤ ሩሲያ በኔቶ ላይ ያላትን ጥያቄ ከማንሳት አትቦዝንም ብለዋል፡፡












