ተቃዋሚዎች ወደ ድንበሯ የተጠጉት አሜሪካ ካናዳ ሰልፉን እንድታስቆም ጠየቀች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የካናዳ ፌደራል መንግሥት የኮቪድ-19 ክልከላዎችን በመቃወም ሰልፍ የወጡ አሽከርካሪዎችን እንዲያስቆም አሜሪካ ጠየቀች።
የጭነት መኪና አሽከርካሪዎቹ የተቃውሞ ሰልፍ እያካሄዱ ከኦቶዋ ወደ አሜሪካ እና ካናዳ ድንበር ተጠግተዋል።
የካናዳ መኪና አምራቾች እና የካናዳ አመራሮችም ሰልፉን ለማስቆም እየሞከሩ ሲሆን፤ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንም ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉ ይገኛሉ።
የኦንትሪዮ ፍርድ ቤት ሰልፈኞቹ በበይነ መረብ የገንዘብ እርዳታ እንዳያገኙ አግዷል።
ጎፈንድሚ የተባለው የገንዘብ ማሰባሰቢያ ሰልፈኞቹ መርህ ጥሰዋል ብሎ ከገጹ ካባረራቸው በኋላ ጊቭሴንድጎ በተባለው ገንዘብ ማሰባሰቢያ ገጽ 8 ሚሊዮን ዶላር አግኝተዋል።
የኦንታሪዮ አመራር ይህንን የእርዳታ ገንዘብ የመውሰድ መብት እንዳለው ገልጿል።
የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት እና ትራንስፖርት ክፍል በበኩሉ፤ የካናዳ የፌደራል መንግሥት በድንበር አካባቢ የተፈጠረውን ችግር እንዲፈታ አሳስቧል።
"በዋነኛነት አምባሳደር በተባለው ድልድይ ላይ መንገድ የዘጉ ተቃዋሚዎች ድርጊታቸውን እንዲያቆሙ እንፈልጋለን" ተብሏል።
ዊንድሶር እና ኦንታሪዮን ከዲትሮይት እና ሚሽገን ጋር የሚያገናኘው መንገድ ተዘግቷል። ተሽከርካሪዎች ሌላ አማራጭ መንገዶች ለመጠቀምም ተገደዋል።
የዊንድሶር ፖሊስ ከሌሎች የፖሊስ ክፍሎች እገዛ እንደጠየቀና ጉዳዮን በሰላም ለመፍታት እየሞከረ እንደሚገኝ አስታውቋል።
ከንቲባው ድሩ ዲከንስ ለሲኤንኤን "እነዚህን ሰዎች በግድ ማባረር የሚጠበቅብን ከሆነ እናባርራለን" ብለዋል።
ተቃዋሚዎቹን በግድ ማባረር ሌሎች ተቃዋሚዎች በንዴት ሰልፉን እንዲቀላቀሉ ከማነሳሳቱም ባሻገር ወደ ግጭት ሊያመራም ስለሚችል ጥንቃቄ እንደሚደረግ አክለዋል።
ሰልፈኞቹ ወደ ኮውትስ እና አልበርታ የሚወስደውን መንገድም ለሁለት ሳምንታት ዘግተዋል። ተቃውሞው ወደ ኖርዝ ደኮታ ድንበር እየተጠጋም ነው።
የዓለም ግዙፉ መኪና አምራች ቶዮታ በኦንትሪዮ የሚገኙ ሦስት ፋብሪካዎቹ በዚህ ሳምንት መኪና እንደማይገጣጥሙ ገልጿል።
ተቃውሞው የቶዮታን ብቻ ሳይሆን የፎርድ መኪና ምርትንም አስተጓጉሏል።
አሜሪካ የሚሠራው ጄነራል ሞተርስም ሥራው ተደናቅፏል።
የዋይት ሀውስ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት አማካሪ ብራየን ዴስ "የካርጎ ጭነቶች በባቡር፣ በሌላ ድልድይ ወይም በባሕር እንዲያልፉ እናደርጋን" ብለዋል።
ኦቶዋ እስካሁን 25 ሰዎችን ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ አስራለች። 1,775 ሰዎች ደግሞ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።
በከባድ የጭነት መኪና መንገድ በመዝጋት በኦቶዋ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መጨናነቅ እንዲፈጠር ተደርጓል።
መነሻው አሜሪካ የሆነ ሐሰተኛ የስልክ ጥሪ በማድረግ የካናዳ የስልክ መስመሮች እንዲጨናነቁም ሆኗል።
ወደ ካናዳ የሚገቡ የጭነት መኪና አሽከርካሪዎች መከተብ አለባቸውን የሚለውን ሕግ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሮዶ እንዲሰርዙ ተቃዋሚዎቹ ጠይቀዋል።
የትሮዶ ተቃዋሚ የሆኑ ፖለቲከኞች ሰልፈኞቹን ሲያሞግሱ ቆይተዋል።
አሜሪካ በቀጣይ ቀናት ተቃውሞው ወደ ካሊፎርንያ እና ዋሽንግተን ዲሲ ይስፋፋል ብላ ትሰጋለች። ካናዳ ከወዲሁ ሰልፉን እንድታስቆምም ጫና ማሳደሩን ቀጥላለች።












