የኤምኤስኤፍ ሠራተኞች ለምግብ ድጋፍ ወሲብ በመጠየቅ በሱዳናውያን ስደተኞች ላይ ጥቃት መፈጸማቸው ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በፈረንሳይኛ ምህጻሩ ኤምኤስኤፍ በመባል የሚታወቀው ዓለም አቀፉ የድንበር የለሽ ሀኪሞች ድርጅት፣ ሠራተኞቹ የእርስ በርስ ጦርነትን በመሸሽ ደህንነትን ፍለጋ በተሰደዱ ቢያንስ 59 ሱዳናውያን ስደተኞች ላይ ወሲባዊ ጥቃት በመፈጸም መከሰሳቸውን አምኗል።
ታዳጊ ሴቶችም ጭምር ለጥቃት የተዳረጉ ሲሆን፤ በምግብ ወይም በሥራ ዕድል ምትክ በተደጋጋሚ ወሲብ እንዲፈጽሙ ይጠየቁ ነበር።
ወሲባዊ ጥቃቶቹ የተፈጸሙት እስካሁን ድረስ የቀጠለው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ በምስራቅ ቻድ ውስጥ በአውሮፓውያኑ 2024 እንደነበረ ተገልጿል።
የህክምና ረድኤድ ድርጅቱ ኤምኤስኤፍ፣ በድርጊቱ ጥፋተኛ ናቸው ያላቸውን 18 ሰራተኞቹን ከሥራ ማሰናበቱን ቢገልጽም፤ ሌሎች በወንጀሉ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ማንነት ግን ማወቅ እንዳልቻለ ለአሶሼትድ ፕሬስ አስታውቋል።
የህክምና ረድኤድ ድርጅቱ፣ "ለወሲባዊ ድርጊት ሰዎችን ማዘዋወር" ተብለው ሊጠቀሱ የሚችሉ ተደጋጋሚ ድርጊቶችን ማግኘቱንም በሐምሌ ወር ባወጣው የውስጥ ሪፖርቱ ይጠቁማል።
ከተጎጂዎች መካከል አንዳንዶቹ፣ አስፈላጊው ድጋፍ እንዳይቋረጥባቸው በመስጋት፣ ስለተፈጸመባቸው ጥቃት ከመናገር መቆጠብ እንደሚመርጡ ዘገባው ጠቅሷል።
ጥቃቱን ሪፖርት ያደረጉትም ቢሆኑ አንዳንዴ ምንም ዓይነት ምላሽም ሆነ ድጋፍ እንዳላገኙም ኤምኤስኤፍ በራሱ ሪፖርት ላይ ያመነ ሲሆን፤ የቅሬታ ማቅረቢያ ሥርዓቱም በአብዛኛው ውጤታማ አልነበረም።
ኤምኤስኤፍ የወሲባዊ ጥቃት ድርጊቱን ለመረመሩ የአሶሼትድ ፕሬስ ጋዜጠኞች በሰጠው ምላሽ፥ "ይህ የሥነ-ምግባር ጉድለት የኤምኤስኤፍ እሴቶችንና ኃላፊነቶችን በከፍተኛ ሁኔታ የጣሰ ነው፤ በደረሰው ጉዳትም ክፉኛ አዝነናል" ብሏል።
ሱዳን፣ በሀገሪቱ ወታደራዊ ኃይል እና ፈጥኖ ደራሽ ደጋፊ ኃይሎች (አርኤስኤፍ) መካከል በተፈጠረ የሥልጣን ሽኩቻ ምክንያት ከሦስት ዓመታት በፊት ነበር ወደ እርስ በርስ ጦርነት የገባችው።
ከ11 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቀዬአቸው የተፈናቀሉበት እና 28 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ለከፋ ርሃብ የተጋለጡበት ይህ ጦርነት፥ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ አስከፊውን ሰብአዊ ቀውስ ያስከተለ የእርስ በርስ ጦርነት መሆኑ ይገለጻል።
ምንም እንኳን ትክክለኛው የሟቾች ቁጥር ባይታወቅም፤ ጦርነቱ ቢያንስ የ150,000 ሰዎችን ህይወት እንደቀጠፈ እና ሟቾቹ እስከ 400,000 ሊደርሱ እንደሚችሉ ይታመናል።
በዚህ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ መጠነ-ሰፊ የወሲብ ጥቃት እንደ ጦርነት መሣሪያነት በሰፊው ጥቅም ላይ መዋሉ የተመዘገበ ሲሆን፤ ህጻናትን ጨምሮ ወንዶች እና ሴቶች የጥቃት ሰለባ ሆነዋል።















