'ከኳስ እና ከትምህርት አንዱን ምረጥ!' ተብሎ ያደገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የፊት መስመር ተጫዋች

ዳዋ ሁጤሳ በመጀመሪያው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎው ጎል ማስቆጠር ችሏል።

የፎቶው ባለመብት, KENZO TRIBOUILLARD/Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዳዋ ሆጤሳ በመጀመሪያው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎው ጎል ማስቆጠር ችሏል።
ታትሟል

በልጅነቱ እረኛ ነበር። የወላጆቹን ከብቶች ያግዳል። ተማሪም ነበር። ይሁን እንጂ ፍቅሩ ከኳስ ጋር ነበር። በሰፈራቸው በሚገኘው ሜዳ፣ አልያም በወላጆቹ ሰፊ ግቢ ውስጥ ከኳስ ጋር ስሯሯጥ ነው ያደጉት ይላል፤ የዛሬው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የፊት መስመር ተጫዋች ዳዋ ሆጤሳ።

ወላጆቹ እግር ኳስ አብዝቶ መጫወቱን አልወደዱትም ነበር። የወላጆቹ ፍላጎት ልጃቸው ትኩረቱ ትምህርት ላይ እንዲሆን ነበር። የኳስ ፍቅሩ ከልክ ያለፈባቸው ወላጆች ልጃቸው በብዙ መንገድ ቀጥተዋል። ቅጣቶቹ ግን ዳዋን ኳስ ይዞ ከመሯሯጥ አላገዱትም።

በመጨረሻም 'ከትምህርት እና ከኳስ አንዱን ምረጥ!' ተባለ። ዳዋ ሳያቅማማ ምርጫውን አስታወቀ። ኳስን መረጠ።

እግር ኳስ እየተጫወት የፍቅር አጋሩን አገኘ። በኳስም ሕይወቱ ሰምሯል። ለአገር ተሰልፏል። በአፍሪካ ዋንጫ መድረክ አገሩን ወክሎ ግብ አስቆጠረ።

ዳዋ ስለልጅነት ጊዜው፣ እድገቱ እና ስለ የእግር ኳስ ሕይወቱ ለቢቢሲ ተናግሯል።

Presentational grey line

ተወልጄ ያደኩት በምዕራብ ጉጂ ዞን ቃርጫ ከተማ ነው። የከተማ ልጅ ነኝ። የ01 ቀበሌ።

ተወልጄ ካደግኩባት ከተማ እግር ኳስ ተጫዋች ሆኖ የወጣ ያለ አይመስለኝም። አላውቅም።

ቀርጫ በቡና ምርት በጣም ታዋቂ ነች። ወርቅም ይወጣል። አትክልትን እና ፍራፍሬ፤ የተለያዩ የእህል አይነቶችም ይመረታሉ።

ቡና እወዳለሁ፤ በቀን ግን ከአንድ ሲኒ በላይ አልጠጣም። ከብት በጣም እወዳለሁ፤ ወተትም እንደዛው። በልጅነቴ የጠጣሁት ወተት አጠንክሮኛል ብዬ አስባለሁ።

ከልጅነቴ ጀምሮ ኳስ ተጫዋች መሆን በጣም እፈልግ ነበር። ከኛ ቤት ፊት ለፊት ትልቅ ሜዳ ነበር፤ እዛ ኳስ እጫወት ነበር።

ከዲኤስቲቪ (እግር ኳስ ለመከታተል ከሳተላይት ቴሌቪዥን) አልርቅም ነበር። ኳስ ለማሳየት ገንዘብ ይጠይቁ ነበር። በልጅነት ጊዜ ደግሞ ገንዘብ ማግኘት ቀላል አልነበረም።

ቤተሰቦቼ በጣም ብዙ ከብቶች ነበሯቸው። እኛም እረኞች ነበረን። ክብት እንጠብቃለን፤ ከዛ ወደ ትምህርት ቤት መሄድ ነው።

እኔ እግር ኳስ ብወድም ቤተሰቦቼ ግን ኳስ እንድጫወት አይፈቅዱልኝም ነበር። በኳስ ምክንያት ብዙ ቅጣት ደርሶብኛል። ከብቶቹን ትቼ ወደ ኳስ ሜዳ ሄጄ ኳስ እጫወት ነበር። በዚህም ምክንያት በተለይ አባቴ በተኛሁበት ይመታኝ ነበር።

አባቴ የዛን ጊዜ የቡሌ ወረዳ አስተዳዳሪ ነበር። ከሥራ በኋላ ደግሞ አርሶ አደር ሆኗል።

ወላጆቼ ኳስ አትጫወትም ብለው ሲከለክሉኝ ምግብ አልበላም እያልኩ አስቸግር ነበር። 9ኛ ክፍል እስክደርስ በዚህ ሁኔታ ቆይቻለሁ።

ከዛ አባቴ 'ምንድነው የምትፈልገው' 'በማለት ከኳስ ወይም ከትምህርት አንዱን እንድመርጥ ጠየቀኝ። እኔም በኳስ መቀጠል ነው የምፈልገው ብዬ ነገርኩት። በዛው ትምህርት አቋረጥኩ።

ዳዋ በፕሪሚየር ሊጉ ባለፉት 7 ዓመታት ተጫውቷል።

የፎቶው ባለመብት, Dawa Hotessa

የምስሉ መግለጫ, ዳዋ በፕሪሚየር ሊጉ ባለፉት 7 ዓመታት ተጫውቷል።

ቀስ በቀስ ለትምህርት ቤት መጫወት ጀመርኩ። 'ልምድ ያግኝ' እያሉኝ ወደ ነገሌ ቦረና ይዘውኝ ይሄዱ ነበር።

በወቅቱ ነገሌ ክለቡ በኦሮሚያ ሊግ ውስጥ ይጫወት ነበር። ለነገሌ ስጨዋት የመጀመሪያው ክፍያዬ 300 ብር ነበር።

Presentational grey line
  • ቁመት: 1.87 ሴንቲ ሜትር
  • እድሜ፡ 26 (የትውልድ ዘመን 1988 ዓ.ም.)
  • የሚጫወትበት ቦታ፡ የፊት መስመር
  • ክፍያ፡ 150ሺህ ብር (ከዚህ ቀደም በአዳማ ሲጫወት ይከፈለው የነበረው )
Presentational grey line

የልጆች አባት

የሕይወት አጋሬ ኳስ እና አትሌቲክስ ትወዳለች። ግን እሷ በትምህርት ገፍታበታለች። በልጅነት ነው የተጋባነው። ብዙ ዓመት በፍቅር ቆይተናል። ከስድስት ዓመት በፊት ነው የተጋባነው። አሁን ሁለት ልጆች አሉን።

ኑሮዬ በአዳማ ከተማ ነው። አዳማ ላይ ቤት ገዝቻለሁ።

ዳዋ ማለት ሰው መንካት የማይችለው ትልቅ ደን ማለት ነው። ሁጤሳ ማለት ደግሞ እኩለ ለሊት ላይ የተወለደ ሰው ማለት ነው።

ወደ ትውልድ ከተማዬ ስሄድ በተለያዩ ፕሮጀክቶች መካከል ውድድር በማካሄድ ታዳጊዎች እንዲበረታቱ ጥረት አደርጋለሁ። በቅርቡ ግን በአካባቢው የጸጥታ ችግር ስላለ ሄጄ አላውቅም።

Presentational grey line

ፕሪሚዬር ሊጉን ከተቀላቅልኩ 7ኛ ዓመቴ ነው። በእነዚህ ዓመታት፤

  • ናሽናል ሲሚንት (ድሬ ዳዋ)
  • ቅዱስ ጊዮርጊስ - ለሁለት ዓመት
  • አዳማ- ለአራት ዓመት
  • ሃዲያ ሆሳዕና - አንድ ዓመት
  • አዳማ - አሁን ዳግም ተመልሼ እየተጫወትኩ ነው።

በጣም ተደስቻለሁ

የአፍሪካ ዋንጫ ማለት ትልቅ ውድድር ነው። በትልቅ ውድድር ላይ ተሰልፌ ጎል ማስቆጠሬ በጣም ነው ያስደሰተኝ።

በሁለት ጨዋታዎች ላይ ተሰልፌ ተጫውቻለሁ። በዚህ ውድድር ላይ የሴኔጋሉን ሳዲዮ ማኔን እና ለአርሰናል የሚጫወተውን ጋናዊውን ቶማስ ፓርቴን አግኝቻለሁ።

ዳዋ ከሊቨርፑሉ የፊት መስመር ተጫዋች ሳዲዮ ማኔ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Dawa Hotessa

የምስሉ መግለጫ, ዳዋ ከሊቨርፑሉ የፊት መስመር ተጫዋች ሳዲዮ ማኔ ጋር

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የሚጎለው ነገር የለም። ግን እንደ ተጫዋች ብዙ መስራት ያለብን ነገር አለ። ለምሳሌ በቴክኒክ እንጂ በሰውነት ብቃት ከእነሱ ጋር አንወዳደርም።

እንደ አትሌቶቻችን ብዙ የስኬት ደረጃ ላይ መድረስ አለመቻላችን ያበሳጨኛል። እንደ አንድ ግለሰብ ያሳዝነኛል። ለዚህ አገር ብዙ ማድረግ እፈልጋለሁ።

ከአፍሪካ ዋንጫ በኋላ በአካል ቀርቦ ያነጋገረኝ ክለብ የለም። ግን የተለያዩ ወኪሎች በኢንስታግራም አነጋግረውኛል።

ከ2007 ጀምሮ በብሔራዊ ቡድን ስሳተፍ ቆይቻለሁ። በሴካፋ ውድድር ላይም ተሳትፌያለሁ።