የእስራኤል ኃይሎች የመብት ተሟጋቾች ላይ ፈጽመዋል የተባለውን ጥቃት አውስትራሊያ መመርመር ጀመረች

ወደ ጋዛ በመርከብ የተጓዙት የዓለም አቀፍ ንቅናቄው 'ግሎባል ሳሙድ ፍሎቲላ' አባላት የሆኑ አራት ሴት የመብት ተሟጋቾች

የፎቶው ባለመብት, Global Sumud Flotilla

የምስሉ መግለጫ, ወደ ጋዛ በመርከብ የተጓዙት የዓለም አቀፍ ንቅናቄው 'ግሎባል ሳሙድ ፍሎቲላ' አባላት የሆኑ የመብት ተሟጋቾች
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ወደ ጋዛ የተጓዙት የመብት ተሟጋቾች በእስራኤል ኃይሎች መደፈራቸውን እና መሰቃየታቸውን መግለጻቸውን ተከትሎ የአውስትራሊያ ፖሊስ ምርመራ ከፈተ።

ወደ ጋዛ በመርከብ የተጓዙት የዓለም አቀፍ ንቅናቄው 'ግሎባል ሳሙድ ፍሎቲላ' አባላት የሆኑ አራት ሴት የመብት ተሟጋቾች ከአውስትራሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔኒ ዎንግ እና ከሌሎችም የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ከተገናኙ በኋላ ምርመራው እንደሚካሄድ ይፋ ተደርጓል።

የእስራኤል ኤምባሲ ቃል አቀባይ በክሱ ላይ "ምንም ተዓማኒ ማስረጃ የለም" ያሉ ሲሆን፤ ይፋዊ ቅሬታ እንዳልቀረበላቸውም አስታውቀዋል።

ወደ ጋዛ ከተጓዙት በመቶዎች የሚቆጠሩ የመብት ተሟጋቾች መካከል 11 አውስትራሊያውያን ይገኙበታል።

ከሁለት ወራት በፊት ሰብአዊ እርዳታ ይዘው ወደ ጋዛ የተጓዙት የመብት ተሟጋቾች በእስራኤል ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ውለው እንደነበር ይታወሳል።

ከመብት ተሟጋቾቹ አንደኛዋ ጁልየት ላሞንት እንዳለችው፤ በእስራኤል ኃይሎች ላይ ያቀረቡትን ክስ በተመለከተ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት የአውስትራሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ያምናሉ።

"እገታ፣ ብዝበዛ፣ መደፈር እና ስቅይትን በተመለከተ ገለልተኛ ምርመራ ለማድረግ ተስማምተዋል" ብላለች።

የአውስትራሊያ ፌደራል ፖሊስ "ክሶቹ ላይ ምርመራ ማድረግ እንደተጀመረ" እና "ተጎጂዎችን እና የደረሰባቸውን እንግልት ያማከለ መንገድ" እንደሚከተል አስታውቋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ከመብት ተሟጋቾቹ ጋር የተገናኙት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን "በቀጥታ ስለ ተሞክሯቸው የመስማት" ዕድል እንዳገኙ ጠቅሰዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ቃል አቀባይ እንደተናገሩት፤ በእስራኤል ኃይሎች ተፈጽመዋል የተባሉትን ጥቃቶች በተመለከተ በተደጋጋሚ ለእስራኤል እና ለባለሙያዎች ገልጸዋል። "ገለልተኛ እና ግልጽ ምርመራ" እንደሚደረግም አክለዋል።

"ሚኒስትሯ የእስራኤል ባለሥልጣናትን ድርጊት ኮንነዋል። የእስራኤሉ ሚኒስትር ቤን-ግቪር ላይም ማዕቀብ ተጥሏል" ብለዋል።

እጃቸውን የታሰሩ የጋዛ የመብት ተሟጋቾች ላይ ያፌዙት ቀኝ አክራሪው የእስራኤል ሚኒስትር ከፍተኛ ውግዘት ደርሶባቸው እንደነበር አይዘነጋም።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የሚኒስትሩ ድርጊት "የእስራኤልን እሴቶች አይወክልም" ብለዋል።

በአውስትራሊያ የሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ ወደ ጋዛ የተጓዙት የመብት ተሟጋቾች "ተንኳሽ" እንደሆኑ እና ክሳቸው "የውሸት መሆኑ እንደተረጋገጠ" ገልጿል።

"አካላዊ እና ወሲባዊ ጥቃት ደርሶብናል ላሉት ክስ እስካሁን ተዓማኒ ማስረጃ አልቀረበም። ይፋዊ ቅሬታም አልደረሰንም" ሲልም አቋሙን አስታውቋል።