የኒውዚላንዷ ጠቅላይ ሚኒስትር በኮቪድ ምክንያት የሰርግ ፕርግራማቸውን ሰረዙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኒውዚላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደርን አዲስ ኮቪድን ለመቆጣጠር የወጡ ገደቦችን ይፋ ካደረጉ በኋላ የራሳቸውን የጋብቻ ፕርግራም መሰረዛቸውንም ገልጸዋል።
በሀገሪቱ የኮሮና ቫይረስ ኦሚክሮን ዘርያ መከሰቱን ተከትሎ በመላው ሀገሪቱ የኮቪድ ለመቆጣጠር ከፍተኛ ገደብ ይጣላል።
እገዳዎቹ በተለያዩ ፕርግራሞች ላይ ከ100 ያልበለጡ እና የተከተቡ ሰዎች ብቻ እንዲሳተፉ እንዲሁም በመገበያያ እና በሕዝብ ትራንስፓርት ላይ ማስክ መጠቀምን ጨምሮ የተለያዩ ክልከላዎችን ያጠቃልላል።
በነዚህ ክልከላዎች ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትር አርደርን ከቴሌቭዥን ፕርግራም አዘጋጁ ክላርክ ጌይፎርድ ጋር ሊያደርጉት ያሰቡት ሰርግ እንደማይካሄድ ለጋዜጠኞች አረጋግጠዋል።
"በወረርሽኙ አስከፊ ጉዳት ከደረሰባቸው በሺዎች የሚቆጠሩ የኒውዚላንድ ዜጎች በምንም የተለየሁ አይደለሁም" ብለዋል።
ኒውዚላንድ ወረርሽኙ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የሞት ምጣኔን ዝቅተኛ ለማድረግ በማለም ጥብቅ የኮቪድ መከላከያ ህጎች አውጥታ ስትተገብር ቆይታለች።
በወረርሽኙ ምክንያት ድንበሮቿን በመዝጋት እና የእንቅስቃሴ ገደብ ከጣሉ የመጀመሪያ ሀገራት አንዷ ነበረች።
ነገር ግን ዴልታ የተሰኘው የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ጠቅላይ ሚኒስትር አርደርን ኮሮናንን ሙሉ ለሙሉ ማስወገድ የሚለው ስትራቴጂያቸውን በፍተኛ ቁጥር የወርርሽኙን መጠን መቀነስ በሚል ተክተውታል።
በሀገሪቱ ዕድሜያቸው ከ12 ዓመት በላይ ከሚሆነው ህዝብ 94 በመቶው ሙሉ በሙሉ የተከተቡ ሲሆን 56 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ተጨማሪ ወይም የማጠናከሪያ ክትባት ወስደዋል።
ሀገሪቱ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ድንበቿን የመክፈት እና ተጓዞች ወደ ሀገራ እንዲገቡ የመፍቅድ እቅድ እንዳላት አስታውቃ ነበር።
የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን በኒውዝላንድ በቫይረሱ 15 ሺህ ሰው እንደተያዘ የተመዘገበ ሲሆን 52 ሰዎች ደግሞ መሞታቸው ተረጋግጧል።












