የቱርኳ ታዋቂ ጋዜጠኛ ስለመሪዎች አባባል በመጥቀሷ ለእስር ተዳረገች

ሴዴፍ ካባስ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

የቱርክ ፍርድ ቤት ታዋቂዋን ጋዜጠኛ ሴዴፍ ካባስ ስለ መሪዎች የጠቀሰችው አባባል ለሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ስድብ ነው በሚል ክስ አስሯታል።

ካባስ ቅዳሜ ዕለት በዋናዋ መዲናዋ ኢስታንቡል ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋለች ሲሆን ችሎት ከመቅረቧም በፊት ፍርድ ቤቱ እንድትታሰር አዟል።

ጋዜጠኛዋ የፕሬዚዳንት ሬሴፕ ጣይብ ኤርዶጋን ተቃዋሚ በሆነው የቴሌቪዥን ጣቢያም በቀጥታ ፕሮግራም ቀርባም በጠቀሰችው አባባልም ተከሳለች። ጋዜጠኛዋ ክሱን ውድቅ አድርጋለች።

ክሱ ከአንድ አመት እስከ አራት አመት የሚያደርስ እስራትም ያስቀጣል ተብሏል።

"ዘውድ የተቀዳጀ ጭንቅላት ጠቢብ ይሆናል የሚል በጣም ዝነኛ አባባል አለ። ነገር ግን እሱ ትክክል እንዳልሆነ አይተናል" ስትል በቴሌ 1 ቻናል የተናገረች ሲሆን

"ኮርማ በሬ ቤተ መንግሥት ስለ ገባ ንጉስ ይሆናል ማለት አይደለም በተፃራሪው ቤተ መንግሥቱ በረት ይሆናል" ብላለች። ይህንንም አባባል በትዊተር ገጿ ላይ ለጥፋዋለች።

የፕሬዚዳንት ኤርዶጋን ዋና ቃል አቀባይ ፋህረቲን አልቱን የጋዜጠኛዋን አስተያየት "ኃላፊነት የጎደለው" ሲሉ ገልፀውታል።

"ጋዜጠኛ ተብዬዋ ፕሬዝዳንታችንን በቴሌቪዥን ጣቢያ በግልፅ መሳደቧ ጥላቻን ከማስፋፋት ውጭ አላማ የሌለው ነው" ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

ካባስ በፍርድ ቤት በሰጠችው መግለጫ ፕሬዚዳንቱን ለመስደብ አላሰብኩም ስትል አስተባብላለች።

የቴሌ 1 ቻናል አዘጋጅ መርዳን ያንዳግ የጋዜጠኛዋን መታሰር ተችቷል።

"በምሳሌያዊ አነጋገር ምክንያት ሌሊት 8 ሰአት ላይ መታሰሯ ተቀባይነት የለውም፤ ይህ አካሄድ ጋዜጠኞችን፣ ሚዲያዎችን እና ማህበረሰቡን ለማስፈራራት የሚደረግ ሙከራ ነው።" ብሏል።

ኤርዶጋን በአውሮፓውያኑ 2014 የመጀመርያው በቀጥታ የተመረጡ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ከመሆናቸው በፊት በጠቅላይ ሚኒስትርነት 11 አመታትን አገልግለዋል።

ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን ተቺዎቻቸውንና ተቃዋሚዎቻቸውን ዝም ለማሰኘት የሚወስዱት እርምጃ ድንጋጤን ፈጥሯል።

ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ያላቸው ግንኙነት ቀዝቀዝ እንዲል ምክንያት የሆነ ሲሆን ይህም ቱርክ ህብረቱን ለመቀላቀል የምታደርገው ጥረት ላይ እክል ፈጥሯል።

ኤርዶጋን የፕሬዝዳንትነቱን ስልጣን ከተቆጣጠሩበት ጊዜ ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ፕሬዚዳንቱን ተሳድበዋል በሚል ተከሰዋል።

በአውሮፓውያኑ 2020 ከስድብ ክስ ጋር በተያያዘ ከ31 ሺህ በላይ ምርመራዎች ተካሂደዋል ሲል ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል ።