ፕሬዝዳንት ፑቲን በዩክሬን ለሩሲያ ታማኝ የሆነ መሪ ለማስቀመጥ እያሴሩ ነው ተባለ

የዩክሬን ወታደር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ፕሬዝዳንት ፑቲን በዩክሬን ለሩሲያ ታማኝ የሆነ መሪ ለማስቀመጥ እያሴሩ እንደሆነ ብሪታኒያ ደርሼበታለሁ አለች።

ዩናይትድ ኪንግደም ፕሬዝዳንት ፑቲን የሩሲያ ደጋፊ የሆነ ፖለቲከኛ የዩክሬንን መንግስት እንዲመራ ለማድረግ አሲረዋል ስትል ከሳለች።

የቀድሞ የዩክሬን ፓርላማ አባል የነበሩት ፖለቲከኛ ኢቭሄን ሙሬዬቭን የሩሲያ ምርጫ እንደሆኑ የዩኬ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ ስም ጠቅሶ ገልጿል።

ሩሲያ 100 ሺህ ወታደሮቿን ዩክሬን ድንበር አቅራቢያ ያሰፈረች ቢሆንም ወረራ የማድረግ እቅድ የለኝም ስትል በተደጋጋሚ ገልጻለች።

የዩናይትድ ኪንግደም ሚኒስትሮች የሩስያ መንግስት ዩክሬን ላይ ወረራ የሚፈጽም ከሆነ ከባድ መዘዝ ይጠብቀዋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሊዝ ትረስ በጽሁፍ በሰጡት መግለጫ "በዛሬው የወጣው መረጃ ዩክሬንን ለመናድ ሩስያ እያደረገች ያለችውን እንቅስቃሴ ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ሲሆን የሩሲያ መንግስትንም እሳቤ የሚያንጸባርቅ ነው" ብለዋል።

ሩሲያ ጉዳዩን እንድታረግብ፣ የወረራ ዘመቻዋን እንድታቆም ሀሰተኛ መረጃ ከማሰራጨት እንድትቆጠብ እና የዲፕሎማሲ መንገድን እንድትከተል ሲሉም አሳስበዋል።

"ዩኬ እና አጋሮቻችን ደጋግመው እንደተናገሩት በዩክሬን ላይ የሚፈጸም ማንኛውም የሩሲያ ወታደራዊ ወረራ ከባድ ኪሳራን የሚያስከትል ትልቅ ስትራቴጂካዊ ስህተት ነው" ሲሉም አክለዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 ሩሲያ የዩክሬንን ግዛት ከመያዟ ቀደም ብሎ በሀገሪቱ ለሩስያ የታመኑ ፕሬዝዳንቷን ከስልጣን ተወግደው ነበር።

የምዕራባውያን እና የዩክሬን የስለላ አገልግሎቶች በተያዘው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መጀመሪያ በድንበር ላይ የሰፈረው የሩሲያ ጦር ሌላ ወረራ ሊፈጽም እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ምንም አይነት ጥቃት ዩክሬን ላይ ለማድረስ እቅድ የለኝም የምትለው ሩሲያ ደግሞ ዩክሬን ወደ ኔቶ ወታደራዊ ጥምረት መግባት የለባትም የሚል አቋም ግን አላት።

ፕሬዝዳንት ፑቲን በአከባቢው ኔቶ እያደረገ ያለው ወታደራዊ ልምምድን የሚልከው የጦር መሳሪያ መላኩን ለሩሲያ ደህንነት ቀጥተኛ ስጋት እንደሆነ ጠቅሰው ይህ እንዲቆም ጠይቀዋል።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በትዊተር ገፁ እንዳስታወቀው የብሪታኒያ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሀሰት መረጃዎችን እያሰራጨ ነው ያለሲሆን "ይህን መሰል ቀስቃሽ ተግባር እንዲያቆም" እና "እርባና ቢስ ወሬውን እንዲተው" አሳስቧል።