አይኤስ በሶሪያ ታራሚዎችን ለማስመለጥ እስር ቤት ሰብሮ መግባቱን ተከትሎ ግጭት ተቀሰቀሰ

በሃሳካ ግዛት የተቀሰቀሰው ግጭት

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

የእስላማዊ መንግሥት ቡድን (አይ ኤስ) ተዋጊዎች በኩርድ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ከሚገኝ እስር ቤት ታራሚዎችን ለማስመለጥ ሰብረው መግባታቸውን ተከትሎ በሰሜን ምስራቅ ሶሪያ ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ነው።

በአሜሪካ የአየር ጥቃት የሚደገፈው በኩርድ የሚመሩ ሃይሎች በሃሳካ ከተማ ከያዝነው ሳምንት ሃሙስ ጀምሮ ታጣቂዎችን እየተዋጉ ነው።

ቡድኑ ከሶስት አመት በፊት ከሶሪያ ከተሸነፈ በኋላ በግዋይራን እስር ቤት ያደረሰው ይህ ጥቃት በጣም ከፍተኛው ነው።

በከፍተኛ ሁኔታ የተጨናነቀው ይህ እስር ቤት አንዳንድ የአይኤስ አመራሮችን ጨምሮ 3 ሺህ 500 የሚሆኑ ተጠርጣሪ የአይኤስ አባላት እንደሚገኙበት አንድ የክትትል ቡድን ገልጿል።

እስር ቤቱን ሰብረው ከገቡ በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጂሃዲስቶች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን አንዳንዶቹም አሁንም በሽሽት ላይ መሆናቸውን የሶሪያ የሰብዓዊ መብት ታዛቢ ተቋም አስታውቋል።

የኩርድ የጸጥታ ኃይሎች እስር ቤቱን ከበው በአቅራቢያው ያሉትን ሰፈሮችንም ለመቆጣጠር እየተዋጉ ሲሆን ነዋሪዎች ቤታቸውን ጥለው እየሸሹ ነው።

የሶሪያው ታዛቢ ተቋም ቢያንስ 28 የኩርድ የጸጥታ ሃይሎች፣ አምስት ሲቪሎች እና 58 የአይኤስ አባላት መገደላቸውን አስታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አይ ኤስ በትናንትናው ዕለት በለቀቀው ቪዲዮ እስር ቤቱን ሰብረው በመግባት ባደረሱት ጥቃት በርካታ አባላቱ መፈታታቸውን ገልጿል።

በተጨማሪም ቪዲዮው ታጣቂዎቹ በርካታ ግለሰቦችን እንዳገቱ የሚያሳይም ይመስላል።

አይ ኤስ በአውሮፓውያኑ 2012 "ግንቡን ማፈራረስ " የሚል ዘመቻ በኢራቅ ከፍቶ ነበር። ይህም ዘመቻ ለቡድኑ ከፍተኛ ለውጥን ማምጣት የቻለ መሰረትም ተደርጎ ይቆጠራል።

ነገር ግን በሃሳካ ግዛት እስር ቤት ሰብሮ መግባት ተመሳሳይ ውጤት ይኖረዋል ተብሎ አይታሰብም ምክንያቱም አይኤስ የሚቆጣጠራቸው ቦታዎች በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።

ሆኖም የቅርብ ጊዜው ሙከራ ቡድኑ አሁንም ስጋት እንደጋረጠና ጥቃቶችን ለመፈጸም ከፍተኛ አቅም እንዳለው ማሳያ ነው ተብሏል።