ያልተከተቡ ሰዎችን ከህዝብ አገልግሎት የሚያግድ ህግ የደገፉ የፈረንሳይ የፓርላማ አባላት የግድያ ዛቻ ደረሰባቸው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በርካታ የፈረንሳይ የፓርላማ አባላት ያልተከተቡትን ሰዎች በሀገሪቱ ከበርካታ ህዝባዊ አገልግሎት እንዲታገዱ የሚያዘውን ረቂቅ መደገፋቸውን ተከትሎ የግድያ ዛቻ እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።
የፈረንሳይ መንግሥት ሰዎች ወደ የጋራ ስፍራዎች ላይ ለመገልገል እና በትራንስፖርት ለማጓጓዝ መከተባቸውን የሚያረጋገጥ ሰነድ እንዲያሳዩ የሚያስገድድ ሕግ በማውጣት ላይ ይገኛል።
ህጉ በዚህ ሳምንት በድምጽ ይፀድቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ክትባትን አንፈልግም የሚሉትን አስቆጥቷል።
ፈረንሳይ በአውሮፓ ህብረት በከፍተኛ ምጣኔ የኮቪድ19 ክትባትን አዳርሳለች። የሀገሪቱ መንግሥት እንደገለጸው በፈረንሳይ ቢያንስ 91 በመቶው የሚሆኑት አዋቂዎች ሙሉ በሙሉ ተከትቧል።
ባለፈው እሁድ የፓርላማ አባል የሆኑት አጀንስ ፊርሚን ክትባት በአንዳንድ ስፍራዎች አስገዳጅ እንዲሆን ደግፈው በመከራከራቸው ሊገደሉ እንዲችሉ የሚያሳይ ስዕላዊ ማስፈራሪያ የያዘ እና በኢሜል የተላከላቸውን በትዊተር ገጻቸው አስፍረው ነበር።
የፋርማሲ ባለሙያ የሆኑት እና የኮቪድ 19 ክትባትንም የሚሰጡት እኚሁ የፓርላማ አባል "ዲሞክራሲያችን አደጋ ላይ ነው" ሲሉም ጽፈዋል።
ቢኤፍኤም ቲቪ ከተሰኘ መገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ዛቻውን ለፖሊስ ሪፖርት እንዳደረጉ እና ክትባቱን አስገዳጅ ለማድረግ ከመደገፍ እንደማይገታቸው አብራርተዋል።
ሌላዋ የፓርላማ አባል የሆኑት ናኢማ ሙችቹ በኢሜል የተላከላቸውን ማስፈራሪያ የሚያሳይ ከስክሪን የተወሰደ ምስል በትዊተር አማካኝነት አሰራጭተዋል።
ትላንት በፓርላማ የተገኙት የጤና ሚኒስትሩ ኦሊቪየር ቬራን የክትባት ተቃዋሚዎችን እያደረሱ ያሉትን የሞት ዛቻ እና "ራስ ወዳድነት" አውግዘዋል።
ባለፈው ሳምንት የፈረንሳይ ሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ጄራልድ ዳርማኒን ክትባትን የተመለከተው ህግ ላይ ድምጽ ከመሰጠቱ በፊት ፖሊስ ለተመረጡት ባለስልጣናት ጥበቃውን እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።
የገዢው ፓርቲ እና የፓርላማው አባል የሆኑት ባርባራ ቤሶት "ነጻነታችንን በማጥቃት" የፓርላማ አባላት እንደሚገደሉ የሚያስፈራራ መልዕክቶች እንደደረሳቸው ፓርቲው ገልጿል።
በትዊተር ገጻቸው ላይ ደግሞ "እነዚያ የግድያ ዛቻዎች ተቀባይነት የላቸውም" ሲሉ ጽፈዋል።
በፈረንሳይ ወረርሽኙ በተስፋፋበት ጊዜ ተቺዎች የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የሚመሩት መንግስት ኮቪድ ለመቆጣጠር ህጎችን በመጣል ነፃነቶችን ጥሷል ሲሉ ከሰዋል። በዚህም ምክንያት እነዚህን ህግጋት የሚቃወሙ ሰልፎች በየጊዜው ተካሂደዋል።
በፈርንሳይ በበርካታ የጋራ ቦታዎች ለመገልገል ሰዎች የክትባት ማረጋገጫ ወይም ከኮቪድ ነጻ መሆንን የሚያረጋግጭ ሰነድ እንዲያሳዩ ለወራት ስትጠይቅ ቆይታለች።
ሆኖም የፈረንሣይ መንግሥት በከፍተኛ ፍጥነት የሚዛመቱት የኦሚክሮን እና ዴልታ ዝርያዎች ተከስተው በቫይረሱ የሚያዙሰዎችን መጨመር ተከትሎ ከቫይረሱ ነጻ መሆንን የሚያሳይ ሰነድ ማቅረብን ከምርጫ ውጪ አድርጋዋለች።
የፈረንሳይ መንግሥት ክትባቱን አስገዳጅ የሚያደርገው ህግ በፓርላማ ከፀደቀ ከተያዘው ወር አጋማሽ ጅምሮ ተግባራዊ ለማድረግ እቅድ ይዟል።
ነገ በሀገሪቱ ሴኔት ውስጥ በጉዳይ ላይ ውይይት የሚደረግ ሲሆን ከዚህ በፊት አብዛኛዎቹ የፓርላማ አባላት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በታችኛው ምክር ቤት ባደረጉት ምክክር በህዝብ አገልግሎት ለመጠቀም አስገዳጅ መሆኑን ይደግፋሉ።












