የሄይቲው ጠቅላይ ሚኒስትር ከግድያ ሙከራ አመለጡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሄይቲው ጠቅላይ ሚኒስትር ኤርዬል ሄንሪ ባለፈው ቅዳሜ የሃገራቸውን የነፃነት ቀን እያከበሩ ሳለ በታጣቂዎች የግድያ ሙከራ እንደተረገባቸው ባለሥልጣናት ገለጡ።
በሃገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በምትገኘው ጎናይቭስ ከተማ ባለ አንድ ቤተ እምነት ውስጥ ሥነ ሥርዓቱን እየታደሙ ባሉበት ወቅት ነው ሙከራው የተደረገባቸው።
ማሕበራዊ ድር አምባዎች ላይ የተለጠፉ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እንደሚያሳዩት ጠቅላይ ሚኒስትሩና አጃቢዎቻቸው ከነበረው የተኩስ እሩምታ በመሸሽ ወደመኪናቸው ሲሮጡ ነበር።
ሄይቲ፤ ፕሬዝደንቷ ከተገደሉባት በኋላ የደህንነት መዋቅሯ የተፈረካከሰ መስሏል። ፕሬዝደንት ጆቬኔል ሞይዝ ባለፈው ሐምሌ ነበር የተገደሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃገሪቱ ውስጥ የሚታየውን አፈና ለማስቀረት አደገኛ የወንጀለኞች ቡድንን መረብ እበጣጥሳለሁ ብለው ቃል ገብተው እንደነበር ይታወሳል።
እኒህ በቡድን የተደራጁ ወንጀለኞች ወደተለያዩ ሥፍራዎች የሚሠራጩ ነዳጆችን በመዝረፍ በሄይቲ የነዳጅ እጥረት አስከተሏል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ እንዳለው "ባንዳዎችና አሸባሪዎች" ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ግድያ ጀርባ አሉበት። አልፎም በቁጥጥር ሥር ውለው ለፍርድ እንዲቀርቡ ማዘዣ ወጥቷል።
ኦሶሺዬትድ ፕሬስ የተሰኘው የዜና ወኪል እንደዘገባው ታጣቂው ቡድን ጳጰሱን በማስፈራራት የቤተ ክርስትያኒቱን አጥር ከበው የጠቅላይ ሚኒስትር ሄንሪን መኪና ለማጥቃት ሲጠብቁ ነበር።
በነበረው የተኩስ ልውውጥ አንድ ሰው ሲገደል ሁለት ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል ሲሉ የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ይህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የተሰነዘረው ጥቃት ባለፈው ሐምሌ ፕሬዝደንቷን ላጣችው ሃገር ከባድ ፈተና ነው ተብሏል።
ጠቅላይ ሚንስትር ሄንሪ የፕሬዝደንት ሞይዝን ግድያ ተከትሎ የሃገሪቱ ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።
ፕሬዝደንት ሞይዝ የተገደሉት በቀድሞ የአሜሪካ ሠራዊት አባላት ትብብር ነው ተብሎ የተነገረው እስካሁን አልተጣራም።
አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመምረጥ እስካሁን ቀን አልተቆረጠም።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሄይቲን ደጋግሞ የጎበኛት የተፈጥሮ አደጋ እንዲሁም እያደገ የመጣው አመፀኝነት ከምጣኔ ሃብት ሁኔታው ጋር ተዳምሮ የሃገሪቱ ዜጎች ስደትን እንደሚርጡ አስገድዷቸዋል።












