በኢራን ተመትቶ በወደቀው አውሮፕላን ተጎጂ የሆኑ ካናዳውያን ቤተሰቦች ካሳ አሸነፉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የካናዳ ፍርድ ቤት በባለፈው ዓመት በቴህራን አቅራቢያ በኢራን ተመትቶ በወደቀው አውሮፕላን ውስጥ ህይወታቸውን ላጡ ስድስት ቤተሰቦች 62 ሚሊዮን ዶላር ከነወለዱ ካሳ እንዲከፈላቸው ውሳኔ አስተላልፏል።
በኦንታርዮ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ካሳ እንዲሰጣቸው የተወሰነላቸው ተጎጂ ቤተሰቦች የትዳር ጓደኞቻቸው፣ እህትና ወንድም፣ ልጆች፣ የእህት ልጅና የወንድም ልጆቻቸውን ያጡ እንደሆነም ተገልጿል።
የዩክሬን አለም አቀፍ አየር መንገድ በረራ ቁጥር ፒኤስ 752 ለበረራ ከተነሳ በጥቂት ጊዜ ነው በሁለት ሚሳይሎች የተመታው። ኢራን አውሮፕላኑን በአሜሪካ ሚሳይልነት እንዳሳሳተችው አስታውቃለች።
በአውሮፕላኑ ውስጥ ተሳፍረው የነበሩ 176 መንገደኞች በሙሉ ህይወታቸውን አጥተዋል።
ከነዚህም ውስጥ 55 ካናዳውያን እና 35 በካናዳ ቋሚ ነዋሪነታቸውን ያደረጉ መንገደኞች ነበሩበት።
ቤተሰብ፣ ወዳጅ፣ ዘመዶቻቸውን ያጡት መንገደኞች ለአደጋው ተጠያቂ ናቸው ባሏቸው የኢራን አና ሌሎች ባለስልጣናት ላይ የፍትሐ ብሔር ክስ አቅርበዋል።
ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት ካሳ እንዲከፈላቸው ቢበየንላቸውም ገንዘቡ ከኢራን እንዴት እንደሚሰበሰብ ለጊዜው አልተገለጸም።
የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ቤተሰቦች ጠበቃ ማርክ አርኖልድ በበኩላቸው ቡድናቸው በካናዳ እና በውጪ የሚገኙ የኢራን ንብረቶችን ለመያዝ ምልከታ እያደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል። ከእነዚህም ውስጥ የነዳጅ ማጠራቀሚያዎች ሊካተቱ እንደሚችሉም ተጠቁሟል።
በዚህ አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ተጎጂ ቤተሰቦች ካሳ ሲከፈል ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ሲቢሲ ዘግቧል። በዚሁ ዘገባ ኢራን በፍርድ ቤት ራሷን እንዳልተከላከለችም ተገልጿል።
ባለፈው አመት የካናዳ መንግሥት ባወጣው ዘገባ ኢራንን ለአውሮፕላኑ መውደቅ ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ ያደረጋት ሲሆን ይህ ደግሞ "የአቅም ማነስ" እና "ግዴለሽነት" ውጤት ነው ብሏል።
የኢራን ባለስልጣናት በአውሮፓውያኑ ጥር 8 ቀን 2020 ተመትቶ ለወደቀው አውሮፕላን በመጀመሪያው ሰሞን አካባቢ ሃላፊነቱን አልወሰዱም እንዲሁም አልተፈጠረም ሲሉ ክደው ነበር።
ነገር ግን መረጃዎች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመራቸውን ተከትሎ የአብዮታዎዊ ጠባቂዎች ኤሮስፔስ ኃይል የአየር መከላከያ ክፍሉ ቦይንግ 737-800ን በአሜሪካ ሚሳኤልነት አሳሳቶታል ብሏል።
በወቅቱ የኢራን አየር መከላከያ በተጠንቀቅ ላይ ነበር የተባለ ሲሆን ለዚህም እንደ ምክንያትነት የተጠቀሰው ሀገሪቱ የአሜሪካ ወታደሮችን በሚያስተናግዱ ሁለት የኢራቅ ወታደራዊ ካምፖች ላይ የባሊስቲክ ሚሳኤሎችን በመተኮሷ ነው።
ይህም የሆነው ከአምስት ቀናት በፊት የአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን ባግዳድ ላይ የኢራኑ ከፍተኛ ጄኔራል ቃሲም ሱሌይማኒን መግደሏን ተከትሎ ሚሳይሎቹ ለዚህ ግድያ የአጸፋ ምላሽ እንደሆነም ተነግሯል።












