እግር ኳስ፡ የአውሮፓ ዋንጫ እሑድ ምሽት ፍጻሜውን ያገኛል፤ ማን ያሸንፋል?

የአውሮፓ ዋንጫ እሑድ ምሽት ፍጻሜውን ያገኛል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የበርካታ እግር ኳስ አፍቃሪያንን ልብ ሰቅዞ ይዞ የከረመው የአውሮፓ ዋንጫ ነገ እሑድ ምሽት አራት ሰዓት ላይ ፍጻሜውን ያገኛል።

በፍጻሜ ጨዋታው ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ በአውሮፓ ዋንጫ ለፍጻሜ የደረሰችው እንግሊዝ እና ምንም ሳትጠበቅ እዚህ የደረሰችው ጣልያን ይፋለማሉ።

ጣልያኖች ገና ከምድብ ጨዋታዎች ጀምሮ በርካታ ጎሎችን እያስቆጠሩና እስካሁንም ድረስ ምንም አይነት ሽንፈትም ሆነ አቻ ውጤት ሳያስተናግዱ ነው ለፍጻሜው ጨዋታ የደረሱት።

እንግሊዝ ደግሞ በምድብ ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር ተስኗት ነበር። ቀስ በቀስ ግን እነ ሀሪ ኬንን የያዘው ቡድን ወደ ግብ ማግባት መመለስ ችሏል።

በግማሽ ፍጻሜው ጨዋታ ጣልያን ስፔንን በፍጹም ቅጣት ምት በማሸነፍ ለፍጻሜ መድረሷን አረጋግጣለች። በእንግሊዙ ዌምብሌይ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ዘጠና ደቂቃው እና ተጨማሪ ደቂቃ አንድ አቻ በመጠናቀቁ ሁለቱ ቡድኖች በፍጽም ቅጣት ምት እንዲለያዩ ሆኗል።

የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በፈጣን እንቅስቃሴና በስፔን የተበላይነት የተሞላ ቢሆንም ግብ ግን ሳይቆጠር ነበር የተጠናቀቀው። ሁለተኛው አጋማሽ ላይ የጣልያኑ ፌደሪኮ ኪዬዛ አስገራሚ ግብ አስቆጥሮ ጣልያንን መሪ ማድረግ ችሏል።

ነገር ግን ጨዋታው ሊጠናቀቅ እየተቃረበ በነረበት ሰዓት የስፔን ተጫዋቾች በጥሩ ጨዋታ ጣልያን የግብ ክልል ውስጥ የተቀባበሏትን ኳስ ተቀይሮ የገባው አልቫሮ ሞራታ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብነት በመቀየር አገሩን አቻ ማድረግ ችሎ ነበር።

የጣልያኑ አሰልጣኝ ሮቤርቶ ማንቺኒ ያዋቀሩት ቡድን እስካሁን ድረስ ብዙም ሳይቸገር ነበር ለግማሽ ፍጻሜው መድረስ የቻለው። ነገር ግን ከስፔን ጋር የተደረገው ጨዋታ ጣልያኖችን የፈተነ ነበር።

ጣልያን ከምድብ ድልድል ጀምሮ ባልተለመደ መልኩ ማጥቃት ላይ መሠረት ያደረገና ብዙ ግቦችን ማስቆጠር የሚያስችል አጨዋወት ነበር ይዛ የመጣችው።

አሰልጣኝ ሮቤርቶ ማንቺኒ ብሔራዊ ቡድኑን ከተረከቡ ወዲህ ለ2018ቱ የዓለም ዋንጫ እንኳን ጣልያንን ማሳለፍ አቅቷቸው የነበረ ቢሆንም በዘንድሮው የአውሮፓ ዋንጫ ግን በደንብ የተደራጀና ውጤታማ ቡድን ሠርተው ለፍጻሜ መድረስ ችለዋል።

እንግሊዝ ደግሞ በግማሽ ፍጻሜው ዴንማርክን በመርታት ከ55 ዓመት በኋላ ለአንድ ትልቅ የእግር ኳስ ውድድር ፍጻሜ ደርሳለች። በርካታ ተመልካች በሚይዘው የለንደኑ ዌምብሊ ስታዲየም የተካሄደው ጨዋታ ፈጣንና በግብ ሙከራዎች የታጀበ ነበር።

እንግሊዝ በፈረንጆቹ 1966 ምዕራብ ጀርመንን በመርታት ካነሳችው የዓለም ዋንጫ ውጭ ሌላ ውድድር አሸንፋም ይሁን ለፍጻሜ ደርሳ አታውቅም። ረቡዕ ምሽት ዴንማርክን የገጠመችው እንግሊዝ አንድ ለባዶ ስትመራ ብትቆይም ከ120 ደቂቃዎች ፍልሚያ በኋላ 2-1 መርታት ችላለች።

ምንም እንኳ ዴንማርክ በወጣቱ ዳምስጋርድ ግሩም ቅጣት ምት አማካይነት ጨዋታውን ስትመራ ብትቆይም የኋላ ኋላ እጇን ሰጥታለች። የመጀመሪያው አጋማሽ ከመጠናቀቁ በፊት የእንግሊዙ ቡካዮ ሳካ ወደ ጎል የላካትን ኳስ የዴንማርኩ ሳይመን ኬር በራሱ መረብ ላይ በማሳረፉ ጨዋታው አቻ ሆነ።

የዴንማርኩ ግብ ጠባቂ ካስፐር ሽማይክል ከሃገሪ ማጓየርና ሃሪ ኬን የተቃጡበትን የጎል ሙከራዎች ማዳን ቢችልም 103ኛው ደቂቃ ላይ ራሂም ስተርሊንግ ፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ተጠልፎ ዳኛው ቅጣት ሰጥተዋል።

የእንግሊዙ ግብ አዳኝ ሃሪ ኬን ፍጹም ቅጣት ምቱን ሲመታ በረኛው ተወርውሮ ቢያድነውም ሃሪ ኬን ግን ተመልሶ ኳሷን ወደ መረብ በመጠለዝ እንግሊዝ ሁለት ለአንድ እንድታሸንፍ አስችሏል።

የጣልያኑ ተከላካይ ሊዮናርዶ ቦኑቺ የፍጻሜ ጨዋታው በእንግሊዙ ዌምብሌይ ስታዲየም መካሄዱ ምንም አይነት ፍርሀት እንደማይፈጥርባቸው ተናግሯል።

"ምንም እንኳን በስታዲየሙ ከሚገኙት ደጋፊዎች መካከል አብዛኛዎቹ እንግሊዛውያን እንደሚሆኑ ብናውቅም ምንም አይነት ስጋት ግን አይገባንም። እንደውም ይሄ ተጨማሪ መነሳሳትን ነው የሚፈጥርልን" ብሏል።

በለንደኑ ዌምብሌይ ስታዲየም የሚካሄደውን የፍጻሜ ጨዋታ እስከ 1 ሺህ የሚደርሱ ጣልያናውያን ደጋፊዎች ገብተው እንደሚከታተሉት ይጠበቃከል።

የዩቬንቱስ የመሀል ተካለካይ ቦኑቺ ከ36 ዓመቱ ጆርጂዮ ኪዬሊኒ ጋር በመጣመር እንግሊዝ ግብ እንዳታስቆጥር ከፍተኛ ሥራ ይጠበቅባቸዋል። ነገር ግን አማካይ እድሜው 25 የሆነው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አንጋፋዎቹን ተከላካዮች ሥራ እንዳያበዛባቸው ተሰግቷል።

''በጣም ፈጣን የፊት መስመር ተጫዋቾች አሏቸው። ሙሉ ቡድናቸውንና በተለይ አጥቂዎቹን በትልቅ ትኩረት ነው የምንጠብቃቸው። ምን አይነች ችግር ሊፈጥሩብን እንደሚችሉ እናውቃለን። ፍጥነታቸውን ከግምት ውስጥ አስገብተን ተጠንቅቀን እንጫወታለን'' ብሏል ቦኑቺ።

የእንግሊዙ አምበል ሃሪ ኬን በበኩሉ ''ይሄ በእግር ኳስ ሕይወቴ ትልቁ አጋጣሚ እንደሆነ ነው የሚሰማኝ። ምናልባት ይህ ለሁሉም የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች የሚሠራ ይመስለኛል''ብሏል።

''ልጅ ሆነን እንዲህ አይነት ህልሞችን እናልማለን። አገርን ወክሎ ተጫውቶ ዋንጫ ማሸነፍ። አሁን ይህንን ህልም የመኖር እድል አግኝተናል። ይሄን የመሰለ እድል በቀላሉ አሳልፈን አንሰጥም።''

እንግሊዞች የግማሽ ፍፃሜ እርግማን አለባቸው ይባል ነበር። በወጣት ተጫዋቾች የተሞላችው እንግሊዝ በ2018ቱ የዓለም ዋንጫ ለግማሽ ፍጻሜ ደርሳ በክሮሺያ መሸነፏ ይታወሳል።

ጣልያን በተካሄደው የ1990 ዓለም ዋንጫ ላይ እንዲሁ ለግማሽ ፍጻሜ ደርሰው ተሸንፈዋል። በድጋሚ ጣልያን ባስተናገደችው የ1996 አውሮፓ ዋንጫ ላይ ለግማሽ ፍጻሜ የደረሰችው እንግሊዝ ሽንፈት አስተናግዳ ነበር።

አሁን ግን ይህንን መጥፎ ጠባሳ ሽራ ለፍጻሜ ማለፍ ችላለች። አሁን ጥያቄው እንግሊዝ ከነዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ በዓለም መድረክ ትልቅ ዋንጫ ማንሳት ትችላለች ወይ የሚለው ነው።

እሑድ ምሽት 4 ሰዓት በለንደኑ ዌምብሊ ስታድየም በአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ እንግሊዝ ከጣልያን የውድድሩን የመጨረሻ ጨዋታ ያደርጋሉ።

ሁለቱም ቡድኖች ባሳዩት አቋም ምክንያት ይሄኛው ቡድን የተሻለ እድል አለው ለማለት እንኳን ከባድ አድርጎታል። ለማንኛውም ግን አሸናፊው ነገ ምሽት የሚታወቅ ይሆናል።