እግር ኳስ፡ ሃሪ ኬን ቶተንሀምን ሊለቅ ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Football Insider
እንግሊዛዊው የቶተንሀም ግብ አዳኝ ሃሪ ኬንን ለማስፈረም ከቼልሲና ከማንቸስተር ሲቲ በተሻለ መልኩ ማንቸስተር ዩናይትዶች እድል እንዳላቸው ፉትቦል ኢንሳይደር አስነብቧል።
የ27 ዓመቱ ሃሪ ኬን በአሁኑ ሰዓት ከአገሩ እንግሊዝ ጋር በመሆን በአውሮፓ ዋንጫ እሑድ ለሚካሄደው የፍጻሜ ጨዋታ መድረስ የቻለ ሲሆን ቡድኑን በአምበልነት እየመራ እስካሁን በውድድሩ አራት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።
ፉትቦል ኢንሳይደር ከታማኝ ምንጮቼ አገኘሁት ብሎ ይዞት በወጣም መረጃ መሠረት፤ ቶተንሀሞች ለኮከብ ተጫዋቻቸው 100 ሚሊዮን ፓውንድ እና ሁለት የማንቸስተር ዩናይትድ ዋናው ቡድን ተጫዋቾችን በምትኩ እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል።
ማንቸስተር ዩናይትዶች በዘንድሮው የክረምት የዝውውር መስኮት እንግሊዛዊው የፊት መስመር ተጫዋች ጄዳን ሳንቾን በ70 ሚሊየን ፓውንድ ያስፈረሙ ሲሆን በመቀጠል ተከላካይና አጥቂ መግዛት እንደሚፈልጉ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ነበር።
በሌላ የዝውውር ጭምጭምታ ሌላኛው የማንቸስተር ክለብ ሲቲ ፈረንሳያዊው የባርሴሎና የፊት መስመር ተጫዋች አንትዋን ግሪዬዝማንን ለማስፈረም እንቅስቃሴ እንዳደረገ ተዘግቧል።
የ30 ዓመቱ ግሪዬዝማን ከአትሌቲኮ ማድሪድ ወደ ባርሴሎና ሲያቀና በርካቶች ስኬታማ ሊሆን እንደሚችል ገምተው የነበረ ቢሆንም፤ የባርሴሎና ቆይታው ግን ብዙም አስደሳች አልነበረም። ለዚህም ነው ተጫዋቹ አዲስ ክለብ እየፈለገ እንደሆነ የተገለጸው።
ሁለቱ ታላላቅ የጣልያን ክለቦች ኢንተርና ሚላን እንዲሁም የእንግሊዙ ሌስተር ሲቲ ብራዚላዊው የባርሴሎና የፊት መስመር ተጫዋች ፊሊፔ ኩቲንዮን ለማስፈረም ፍላጎት እንዳላቸው ተገልጿል።
የቀድሞው የሊቨርፑል ኳስ አቀጣጣይ ኩቲንዮ 29 ዓመቱ ሲሆን በጉልበት ቀዶ ሕክምና ምክንያት ያለፈውን የውድድር ዓመት ሁለተኛ ግማሽ ኳስ አልተጫወተም። ነገር ግን አሁን ላይ ወደ ድሮ አቋሙ እየተመለሰ መሆኑን ተከትሎ በርካታ ክለቦች ተጫዋቹን የግላቸው ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምረዋል።
ስለዚህም ክለቡ ባርሴሎና ለተጫዋቹ እስከ 20 ሚሊዮን ፓውንድ የሚከፍል ከመጣ ለመሸጥ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።












