እንግሊዝ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአውሮፓ ዋንጫ ፍፃሜ ደረሰች

የእንግሊዝ እግር ኳስ ክለብ

የፎቶው ባለመብት, Frank Augstein - Pool

ታትሟል

እንግሊዝ በዩሮ 2020 ፍልሚያ ዴንማርክን በመርታት ከ55 ዓመት በኋላ ለአንድ ትልቅ የእግር ኳስ ውድድር ፍፃሜ ደርሳለች።

በርካታ ተመልካች በተሰበሰበበት በለንደኑ ዌምብሊ የተካሄደው ጨዋታው ልብን ሰቅዞ የሚይዝ ነበር።

እንግሊዝ በፈረንጆቹ 1966 ምዕራብ ጀርመንን በመርታት ካነሳችው የዓለም ዋንጫ ውጭ ውድድር አሸንፋም ይሁን ለፍፃሜ በቅታ አታውቅም።

ረቡዕ ምሽት ዴናማርክን የገጠመችው እንግሊዝ አንድ ለምንም ስትመራ ብትቆይም ከ120 ደቂቃዎች ፍልሚያ በኋላ 2-1 መርታት ችላለች።

66 ሺህ ሰዎች በታጩቀበት የተፋለሙት ሶስቱ አናብስት የተሰኘ ቅጥያ ያላቸው እንግሊዞች ይህን ጨዋታ በማሸነፋቸው በፍፃሜው ከጣልያን ጋር ይገናኛሉ።

እንግሊዝ እሁድ ምሽት ጣልያን የምትገጥመው በገዛ ሜዳዋና ሕዝቧ ፊት ነው።

ምንም እንኳ ዴንማርክ በወጣቱ ዳምስጋርድ ግሩም ቅጣት ምት አማካይነት ጨዋታውን ስትመራ ብትቆይም የኋላ ኋላ እጇን ሰጥታለች።

ነገር ግን የመጀመሪያ አጋማሽ ከመጠናቀቁ በፊት የእንግሊዙ ቡካዮ ሳካ ወደ ጎል የላካትን ኳስ ሳይመን ኬር በራሱ መረብ ላይ በማሳረፉ ጨዋታው አቻ ሆነ።

የዴንማርኩ ግብ ጠባቂ ካስፐር ሽማይክል የዳኒሾች ጎል ደጀን ሆኖ ቢያመሽም ከሽንፈት አልታደጋቸውም።

ሽማይክል ከሃገሪ ማክጓዬርና ሃሪ ኬን የተቃጡበትን የጎል ሙከራዎች እያዳነ ቢያመሽም ጨዋታው ተጨማሪ 30 ደቂቃዎች ከታከሉበት በኋላ የተሰጥውት ፍፁም ቅጣት ምት ግን ማዳን አልቻለም።

103ኛው ደቂቃ ላይ ራሂም ስተርሊን ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ተጠልፎ ወድቋል ሲሉ ዳኛው ቅጣት ምት ይሰጣሉ።

በሺዎች የሚቆጠሩ የስታድየሙ ታዳሚያን በሁለት ተከፍለው ቅጣት ምቱን በጉጉት ይጠባበቃሉ።

ሃሪ ኬን ኳሷን ወደ መረቡ ሲሰዳት ሽማይክል ያገኛታል። ነገር ግን ሲተፋት ተመልሳ የሃሪ ኬን እግር ላይ ታርፋለች። ይህን ወርቃማ ዕድል ያገኘው ኬን ኳሷን ከመረብ ያዋህዳል።

ዴንማርክ የዳኛው ውሳኔ ትክክል አይደለም ብለው አቤቱታ ቢያቀርቡም ሰሚ አላገኙም።

እንግሊዞች የግማሽ ፍፃሜ እርግማን አለባቸው ይባላል። ምክንያቱ ወዲህ ነው።

በወጣት ተጫዋቾች የተሞላችው እንግሊዝ ባለፈው የዓለም ዋንጫ [2018] ለግማሽ ፍፃሜ ደርሳ መሸነፏ ይታወሳል።

ጣልያን በተካሄደው የ1990 ዓለም ዋንጫ ላይ እንዲሁ ለግማሽ ፍፃሜ ደርሰው ተሸንፈዋል።

በድጋሚ ጣልያን ባስተናገደችው የ1996 አውሮፓ ዋንጫ ላይ ለግማሽ ፍፃሜ የደረሰችው እንግሊዝ ሽንፈት ተከናንባ ነበር።

ዘንድሮ ግን ይህንን ሽራ ለፍፃሜ ማለፍ ችላለች። የፍፃሜው ጨዋታ እሁድ ምሽት ይከናወናል።

እንግሊዝ ከጣልያን እሁድ ምሽት 4 ሰዓት በለንደኑ ዌምብሊ ስታድዬም የአውሮፓ ዋንጫን ለማንሳት የሚያደርጉት ፍልሚያ ይጠበቃል።