የቀድሞ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት በአንድ ጉባኤ ላይ 'ከሃዲ' ተባሉ

ማይክ ፔንስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የቀድሞው የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት በአንድ ሃይማኖታዊ ጉባኤ ላይ በሚናገሩበት ወቅት ከተሳታፊዎች ስድብ ተወርውሮባቸዋል።

አንዳንዶች "ከሃዲ" በሚል የሰደቧቸው ሲሆን "ነፃነት" የሚሉ ቃሎችም ተሰምተዋል።

ፖለቲከኛው በያዝነው ሳምንት አርብ በኦርላንዶ ግዛት በነበረው የፌይዝ ኤንድ ፍሪደም ኮሊሸን ንግግር እያደረጉ በነበረ ወቅት ነው ይሄ የደረሰባቸው ተብሏል።

የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት ለአሸናፊው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ዕውቅና መስጠታቸውንም ተከትሎ ነው ይህንን ያስተናገዱት ተብሏል።

በተሳዳቢዎቹ ምክንያት ፖለቲከኛው ንግግራቸውን እንዳላቆሙና ለ28 ደቂቃም የቆየ ንግግርም አድርገዋል።

ተሳዳቢዎቹም መሃል ላይ በፖሊስ እንዲወጡ ተደርገዋል።

በዚህ ንግግግራቸው ወቅት የዲሞከራቱን ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ፖሊሲዎች በመተቸት የተሰናባቹን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን አወድሰዋል።

በጥር ወር ላይ ፕሬዚዳንት ትራምፕን ጨምሮ በርካታ ደጋፊዎቻቸው በወቅቱ የምክር ቤቱ የበላይ የነበሩትን ማይክ ፔንስን ፕሬዚዳንት ባይደን ያሸነፉበትን ሰርቲፊኬት በኮንግረሱ እውቅና እንዳይሰጡት ጠይቀዋቸው ነበር።

ማይክ ፔንስ ይህንን ለማድረግ ስልጣኑ የለኝም ቢሉም በርካታ የትራምፕ ደጋፊዎች ተናደውባቸዋል።

በምርጫው ውጤት የተናደዱ የትራምፕ ነውጠኛ ደጋፊዎች በጥር ወር ላይ በካፒቶል ህንፃ ሰብረው በመግባት ከፍተኛ ሁከት ማስከተላቸው ይታወሳል።

ጥር 6፣ በተለምዶ "የካፒቶል ሒል ነውጥ" ተብሎ የሚጠራው የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች የሁለቱ ምክር ቤቶች መሰብሰብያና በርካታ የመንግሥት አስተዳደር ቢሮዎችን ሰብረው በመግባት የዲሞክራሲ ተምሳሌት ተደርጎ የሚታየውን ስፍራ እንዲሁም የአገሪቱን ስምና ክብር የሚያጎድፍ ተግባር የፈጸሙበት ዕለት ነው።

በካፒቶል የደረሰውንም ጥቃት ተከትሎ ማይክ ፔንስ ከትራምፕ ራሳቸውን አግልለዋል። የካፒቶሉን ጥቃት ተከትሎ ትራምፕ በምክር ቤቱ ያለመከሰሰስ መብታቸው እንደተገፈፈ ይታወሳል።

በአሜሪካ ታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ በመከሰስ የመጀመርያ ሆነው የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ አመጽን ቀስቅሶ ከመምራት ክስ ነጻ መደረጋቸው ይታወሳል።

ማይክ ፔንስ ነውጠኞቹን የተቃወሙ ሲሆን የፕሬዚዳንት ጆ ባይደንን በዓለ ሲመት ላይ ተገኝተዋል። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዓለ ሲመቱ ላይ አልተገኙም።

ነገር ግን አርብ እለት በነበረው ንግግራቸው ማይክ ፔንስ የቀድሞ አለቃውን በስልጣን ላይ ያሳኩዋቸውን ነገሮች ተናግረዋል።