ኮሮናቫይረስ፡ በብራዚል በኮሮና የሞቱ ሰዎች ቁጥር ግማሽ ሚሊዮንን ተሻገረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኮቪድ 19 ምክንያት በዓለም ከፍተኛ ሞት ከተመዘገበባቸው ሀገራት በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠችው ብራዚል የሟቾች ቁጥር 500 ሺህን ያለፈ ሲሆን የክትባት ስርጭት መዘግየቱና የክረምት መቃረብ የወረርሽኙን ሁኔታ ሊያባብሰው ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጄር ቦልሴናሮ እንደ አካላዊ ርቀትን ያሉ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የሚያግዙ እርምጃዎችን ለማስተግበር ዳተኛ መሆናቸውን ተከትሎ በብራዚል ቫይረሱ መስፋፋቱን ቀጥሏል ፡፡
በሀገሪቱ የሚገኝ ፊዮክሮስ የተሰኘ ጤና ላይ የሚያተኩር የምርምር ተቋም በብራዚል ከኮሮና ጋር በተገናኘ ያለውን ሁኔታ "አሳሳቢ" ነው ያለ ሲሆን ሙሉ ክትባት የወሰዱ ጎልማሶች 15 በመቶ ብቻ እንደሆኑ አስታውቋል።
የብራዚል ኮንግረንስ የሀገሪቱ መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመካከል እየሄደበት ያለውን መንገድ እየፈተሸው ይገኛል።
ፕሬዝዳንት ቦልሴናሮ ቫይረሱን ለመከላከል በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቀናጀ ተግባር ባለማከናወናቸው እና የኮሮናቫይረስ ክትባቶች ፣ የእንቅስቃሴ ገደቦች እንዲሁም ማስክ መጠቀምን በተመለከተ የሚያንጸባርቋቸው አቋሞች ሲያስተቻቸው ቆይቷል።
ተቃዋሚዎች ፕሬዚዳንቱ በተከታታይ ወረርሽኙን 'አቅልለው ነው' የተመለከቱት በሚልና ለፖለቲካዊ ትርፍ የክትባት ግዥን አዘግይተዋል ተብለው ይወቀሳሉ።
በሀገሪቱ በአማዞን ክልል ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘውን እና 'ጋማ' ተብሎ የሚጠራውን ጨምሮ ከፍተኛ ፍጥነት የሚዛመቱ የኮሮና ቫይረስ ዓይነቶች በባዛት መገኘታቸው ስርጭቱን አባብሰውታል፡፡
ባለፈው ሳምንት ውስጥ በየቀን በአማካይ 70 ሺህ ሰው በቫይረሱ ተይዞ እንደነበር ተመላክቷል።
በአብዛኞቹ የብራዚል ግዛቶች በሚገኙ የጤና ተቋማት የጽኑ ህሙማን ክፍል አልጋዎች 80 በመቶ ወይም ከዚያ በላይ በቫይረሱ በተያዙ ሰዎች የተሸፈኑ ሲሆን ባለሞያዎችም የክረምቱ መምጣት የቫይረሱን ስርጭት ከዚህም ከፍ እንደሚያደርገው አመላክተዋል።
የብራዚል ጤና ሚኒስትር ማርሴሎ ኮይሮጋ በትዊተር ገፃቸው ላይ ለሞቱት ሰዎች "አባቶች ፣ እናቶች ፣ ወዳጆችና ዘመዶች" አጋርነታቸውን በመግለጽ "በብራዚላችን እና በመላው ዓለም ላይ በተከሰተ ወረርሽኝ ምክንያት የ 500 ሺህ ሰዎች ህይወት አልፏል" ብለዋል፡፡
ከመጋቢት ወር ጀምሮ በብራዚል በሳምንት ውስጥ በእያንዳንዱ ቀን እስከ 1 ሺህ 500 ሰው በቫይረሱ ምክንያት እንደሚሞትም ተዘግቧል። ከብራዚል በመቀጠል በአለም ላይ በቫይረሱ ከፍተኛ ሰዎች የሞቱባት ሀገር አሜሪካ ናት።












