እስራኤል አዲሱ የኢራን ፕሬዚዳንት 'ፅንፈኛ' ናቸው ስትል አስጠነቀቀች

የፎቶው ባለመብት, EPA
እስራኤል አለም አቀፉ ማህበረሰብ በአዲሱ የኢራን ተመራጭ ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ሬይሲ ላይ ስጋት ሊያድርበት ይገባል ብላለች።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ ሊዮር ሃያት እንዳሉት ኢብራሂም ሬይሲ በኢራን "ፅንፈኛው ፕሬዚዳንት" ናቸው ብለዋል።
ቃለ አቀባዩ አዲሱ ፕሬዚዳንት የኢራንን የኒውክሊየር እንቅስቃሴም በሰፊው እንደሚጨምሩትም አስጠንቅቀዋል።
ኢራን በባለፈው ሳምንት እሁድ በነበረው ምርጫ ኢብራሂም ሬይሲን አዲስ ፕሬዚዳንት አድርጋ መርጣለች።
በነሐሴ ወር ስልጣናቸውን የሚረከቡት አዲሱ ፕሬዚዳንት በኢራን ውስጥ ስመ ጥር ዳኛ ሲሆን ወግ አጥባቂ ምልከታም እንዳላቸው ይነገርላቸዋል።
አሜሪካ ማዕቀብ ከጣለችባቸው ኢራንያን መካከል አንዱ ሲሆን ከዚህ ቀደምም በነበሩ የፖለቲካ እስረኞች ግድያ ላይ እጃቸው አለበት በሚልም ስማቸው ይነሳል።
ተመራጩ ፕሬዚዳንት ማሸነፋቸውን ተከትሎ ባወጡት መግለጫ በመንግሥት ላይ ያለውን ህዝባዊ አመኔታ እንደሚያጠናክሩና ለመላው አገሪቱም ጥሩ መሪ እንደሚሆኑ አስታውቀዋል።
"ጠንካራ ሰራተኛ፣ አብዮተኛና ሙስናን የሚጠየፍ መንግሥት እመሰርታለሁ" በማለት መናገራቸውን የአገሪቱ ሚዲያ ዘግቧል።
ነገር ግን የእስራኤሉ ሊዮር ሃያት በትዊተር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት ፅንፈኛ ብለው የጠሯቸው ሲሆን የኢራንን የወታደራዊ ኒውክሊየር ፕሮግራምም በከፍተኛ ፍጥነት ማሳለጥ ይፈልጋሉ በማለትም ወንጅለዋቸዋል።
ለዘመናት በፍጥጫ ላይ ያሉት ኢራንና እስራኤል አነስ ባሉ ግጭቶች ቢሰነዛዘሩም ጦርነት ውስጥ አልገቡም። ነገር ግን በቅርቡ ያለው መጋጋል ወደ ከፍተኛ ፍጥጫ ከቷቸዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ችግር የተወሳሰበ ቢሆንም በዋነኝነት የፍጥጫቸው ምክንያት የኢራን የኒውክሊየር እንቅስቃሴ ነው።
ኢራን ታዋቂውን የኒውክሊየር ሳይንቲስት እስራኤል ገድላብኛለች እንዲሁም የኒውክሊየር ማብላላያውም ላይ ጥቃት ፈፅማለች ትላለች።
በተቃራኒው እስራኤል የኢራን የኒውክሊየር ፕሮግራም ሰላማዊ አይደለም ሽፋን ነው እንጂ ለጦር መሳሪያነት ልትጠቀምበት ነው በማለት ትወነጅላታለች።












