ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በቻይና ባለ 70 ፎቅ ህንፃ መንቀጥቀጡ ስጋት ጭሯል
በቻይናዋ ሸንዘን ከተማ የሚገኛው ሰማይ ጠቀስ ባለ 70 ወለል ህንፃ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እየተገበያዩ ባሉበት እስካሁን ባልታወቀ ምክንያት ተንቀጥቅጧል፡፡
የህንፃው መንቀጥቀጥ ምክንያት እስካሁን ድረስ ባይታወቅም በወቅቱ ምንም አይነት የመሬት መንቀጥቀጥ እንዳልነበረ ግን ተገልጿል፡፡ የመንቀጥቀጡን ምንጭ ለመለየት ምርመራዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡
ይህ ሰማይ ጠቀስ ህንፃ ከተገነባ 20 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን ቢሮዎችን ብሎም የኤሌክትሮኒክ መሳሪያዎችን የያዘ ነው፡፡ ባለ 12 ሚሊዮን ሕዝቧ ሸንዘን ከተማም እጅግ እያደገ ባለው የኤሌክትሮኒክ ኢንዱስትሪዋ እና የሸመታ ከተማነቷ ትታወቃለች፡፡
በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ተጠቃሚዎች ያጋሯቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎች እንደሚያሳዩት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከሰማይ ጠቀሱ ህንፃ ውስጥ እየሮጡ ሲወጡ ያሳያል፡፡
በአለም 212ኛ ብሎም በቻይና 140ኛ ረጅም ነው የተባለለት ይህ ህንፃ ከተንቀጠቀጠ በኋላ በዙሪያው በተደረገ ምርመራ ምንም አይነት ስንጥቅ አለመገኘቱን የቻይናው ግሎባል ታይምስ ዘግቧል፡፡
ከዚህ ቀደም በቻይና ሰማይ ጠቀስ ህንፃ መፍረስ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ባለፈው አመት የኮሮና ቫይረስ ለተያዙ ሰዎች ለይቶ ማቆያ ሲውል የነበረ ሆቴል ፈርሶ 29 ሰዎች መሞታቸው የሚታወስ ነው፡፡