ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በትግራይ የሚካሄደው የግዳጅ ምልመላ፡ ከክልሉ የሚሸሹ እና ለመደበቅ የተገደዱ ወጣቶች
በትግራይ እየተካሄደ ያለው የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ በፈጠረው ስጋት ምክንያት በርካታ ወጣቶች ከክልሉ እየወጡ ወደ ቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል እየሸሹ ሲሆን ሌሎች ደግሞ እዚያው ተደብቀው እንደሚገኙ ተናገሩ።
በክልሉ ውስጥ በስፋት እየተካሄደ ባለው የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ የተነሳ እንቅስቃሴዎች እየተስተጓጎሉ መሆናቸውን የሚናገሩት ነዋሪዎች ፍርሃት መንገሱን ገልጸዋል።
ይህ አፈሳ ከነዋሪዎች እና ከመብት ድርጅት ውግዘት እየገጠመው ቢሆንም ምልመላው በፈቃደኝነት የሚካሄድ ነው በማለት ህወሓት ማስተባበሉን የፈረንሳይ ዜና ወኪል (ኤኤፍፒ) ዘግቧል።
ኤኤፍፒ አፈሳው በክልሉ ኃይሎች በቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ በተገኙ ወጣቶች ላይ ሳይቀር እንደሚፈጸም እና የተያዙትም በኃይል ወደ ማሠልጠኛ ካምፖች እንሚወሰዱ ጠቅሷል።
በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው አቤል የተባለ ወጣትን የጠቀሰው ዜና ወኪሉ "በድንገት ተከብበን ተወሰድን" በማለት በአፈሳው ተይዞ እንደነበረ እና ለጠባቂዎች ገንዘብ ከፍሎ ከተለቀቀ በኋላ ተደብቆ እንደሚገኝ ገልጿል።
በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን በማፍረስ ከጦርነቱ በፊት የነበረው ምክር ቤት ወደ ሥልጣን ከተመለሰ እና የህወሓት ሊቀመንበር የክልሉን መሪነት ከያዙ በኋላ ከፌደራል መንግሥት ጋር ያለው ውጥረት ተባብሷል።
ይህንንም ተከትሎ በምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ዕውቅናቸው የተሰረዘው የህወሓት መሪዎች መጠነ ሰፊ የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ እያከሄዱ መሆናቸውን የሚያመለክቱ ዘገባዎች በተደጋጋሚ ሲወጡ ቆይተዋል።
በዚህም የተነሳ ዳግም ግጭት ይቀሰቀሳል የሚል ስጋት በክልሉ ውስጥ የተፈጠረ ሲሆን፣ አገራት እና ተቋማት ሁለቱም ወገኖች ውጥረቱን ከሚያባብስ እርምጃ እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል።
ቅድሚያ ለሰብአዊ መብት-ኢትዮጵያ የተባለው የመብት ተቆርቋሪ ድርጅት "በአብዛኞቹ የትግራይ አካባቢዎች በሙሉ የግዳጅ ወደታራዊ ምልመላ" እየተካሄደ መሆኑን የሚሳዩ ምልክቶች እንዳሉ ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል ገልጿል።
የሰብአዊ መብት ድርጅቱ በሰሜናዊ ትግራይ ውስጥ የሚገኘውን ሱቁን ሲከፍት ባለፈው መጋቢት ወር የተያዘውን ገብሬን ጨምሮ እየተካሄደ ስላለው አፈሳ 27 የዐይን እማኞችን ቃለ መጠይቅ አድርጓል።
ገብሬ እንዴት ተይዞ ከነበረበት ስፍራ በመስኮት በመዝለል እንዳመለጠ በገለጸበት ጊዜ "ወደ ሠራዊቱ እንደገባን ሲነግሩን ነበር" በማለት በአሁኑ ወቅት ከአምስት ዓመት ልጁ ተለይቶ ተደብቆ እንደሚገኝ ተናግሯል።
ወደ አዲስ አበባ ሸሽቶ የሄደው የ36 ዓመቱ ክንፈ ደግሞ በትግራይ ውስጥ የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ አዲስ ነገር ሳይሆን ቀድሞም የነበረ መሆኑን ገልጿል።
በቅርቡ በተካሄደው ጦርነት ወቅት የህወሓት አባላት ቤት ለቤት በመሄድ እያንዳንዱ ቤተሰብ ቢያንስ አንድ ልጅ ለውትድርና መስጠት አለመስጠቱን እንደሚያጣሩ እና ካልሆነ ግን ቤተሰቦች እንዲሰለፉ እንደሚገደዱ አስታውሷል።
በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ባለው አፈሳ የህወሓት ኃይሎች መንገዶችን በመዝጋት ወጣቶችን መውጫ አሳጥተው በመያዝ ወደ አንድ ቦታ አሰባስበው ወደ ማሰልጠኛ ካምፕ እንደሚወስዷቸው ምሥክሮች ይናገራሉ።
አፈሳውን በመሸሽ አዲስ አበባ ውስጥ በችግር የሚኖረው ዓለም እንደሚለው እሱ ይኖርበት በነበረው አካባቢ አፈሳው የተጀመረው ከአንድ ወር በፊት ገደማ ጀምሮ ነው።
"መጀመሪያ ላይ የተወሰኑ ሰዎች ላይ በማተኮር የሚካሄድ ይመስል ነበር፤ ቀስ በቀስ ግን ሁሉንም ወጣቶች የሚመለከት ሆነ" በማለት ዓለም ተናግሯል።
በትግራይ በስፋት እየተካሄደ ያለው ወደታራዊ ምልመላ በአብዛኛው "በፈቃደኝነት ላይ ብቻ ተመሥርቶ" የሚካሄድ መሆኑን የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ አማኑኤል አሰፋ ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።
ነገር ግን ሁሉም የትግራይ ተወላጅ "ግዛቱን ከኅልውና ስጋት መከላከል ስላለበት ልዩ ሁኔታዎች አሉ" በማለት የግዳጅ ምልመላው እንዳለ በተዘዋዋሪ ገልጸዋል።
ላለፉት ወራት በትግራይ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላን በተመለከተ የፌደራል መንግሥቱ እስካሁን በይፋ ያለው ነገር የለም።
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የዘፈቀደ እስር እና የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላን የሚከለክል ቢሆንም በህወሓት የሚመራው የትግራይ ክልል የግዳጅ ወታደራዊ ምልመልላን የሚመለከት ሕግ አርቅቋል።
የክልሉ አስተደዳር በቅርቡ ይፋ ያደረገው ረቂቅ ሕግ ዕድሜያቸው እና የጤና ሁኔታቸው የሚፈቅድላቸው ማንኛውም የትግራይ ተወላጆች የክልሉ መንግሥት የሚያቀርበውን "የክተት ጥሪ ተቀብሎ የመሳተፍ ብሔራዊ ግዴታ" እንዳለባቸው ይደነግጋል።
ይህ ረቂቅ ሕግም የሚጸድቅ እና ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ በክልሉ እየተካሄደ ያለውን የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላን የበለጠ እንደያባብሰው ስጋት ፈጥሯል።
ለሁለት ዓመት ከተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ገና ባላገገመው ትግራይ ክልል ውስጥ አሁንም ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት በነዋዎች ዘንድ ከፍተኛ ጭንቀትን መፍጠሩን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚጋሩ መልዕክቶች ያሳያሉ።
የፈረንሳይ ዜና ወኪል እንዳለው በርካታ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች የክልሉ መሪዎች በሚያደርጉት ነገር ላይ ከፍተኛ ምሬት ተፈጥሯል።
ከትግራይ ሸሽቶ አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኘው ክንፈ የክልሉ መሪዎች "ሰማዕታቱን ችላ ብለው ምቾታቸውን ብቻ ነው የሚጠብቁት" በማለት በጦርነት የሚጠቀሙት ከላይ ያሉት "ጥቂቶች" ብቻ መሆናቸውን ብዙዎች እንሚያምኑ ተናግሯል።
"ጦርነት መነሳት የለበትም፣ በፖለቲካዊ መንገድ መፍትሄ መፈለግ አለበት። ጥይት መተኮስ ለምንም ነገር መፍትሄ አይሆንም" ብሏል።
የህወሓት መሪዎች የክልሉን አስተዳደር ከተቆጣጠሩ በኋላ ከፌደራል መንግሥት ጋር ያላቸው ግንኙነት የተቋረጠ ሲሆን፣ የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት አንዳቸው ሌላኛቸውን ጦርነት ለመክፈት እየተዘጋጀ ነው በሚል እየተካሰሱ ነው።
ውጥረቱ ስጋት የፈጠረበት የአፍሪካ ኅብረትም ከሦስት ዓመት በፊት በትግራይ የተካሄደውን ጦርነት ያስቆመውን ስምምነት የሸመገሉትን መልዕክተኛውን ኦሉሴጎን ኦባሳንጆን ወደ መቀለ ልኮ ከህወሓት መሪዎች ጋር ተወያይቷል።
በዚህ ሳምንትም የአሜሪካ መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ውጥረት እንዳይፈታ እንቅፋት ፈጥረዋል ባላቸው አክራሪ የህወሓት መሪዎች እና ቤተሰቦቻቻው ላይ የቪዛ ክልከላ መጣሉን ተጨማሪ እርምጃም እንደሚወስድ አስታውቋል።