ኳታር ለትራምፕ ያበረከተችው ባለ 400 ሚሊዮን ዶላር ቅንጡ አውሮፕላን

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኳታር መንግሥት ባለፈው ዓመት ለአሜሪካ "ያለምንም ቅድመ ሁኔታ" ያበረከተውን በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች የሚያወጣውን አዲስ የቦይንግ 747-8 ቅንጡ ፕሬዝዳንታዊ አውሮፕላን የተለያዩ ለውጦች ከተደረገበት በኋላ ይፋ አደረጉ።

የአሜሪካ ጦር ሠራዊት እንዳለው 400 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያወጣ የተገመተው የቅንጦት ጃምቦ ጄት ላይ ሲያደርግ የነበረውን ማሻሻያዎችን አጠናቋል።

ትራምፕ አርብ ዕለት አንድሩስ በተባለው የአየር ኃይል ሰፈር ውስጥ አውሮፕላኑ ይፋ ሲደረግ ባደረጉት ንግግር "ይህ አውሮፕላን ማንም ሰው ከዚህ በፊት አይቶት በማያውቅ የቅንጦት ደረጃ የሚበር ሆኖ ተለውጧል" ብለዋል።

የአሜሪካ የአየር ኃይል ባሠራጨው ጋዜጣዊ መግለጫ አውሮፕላኑ ለፕሬዝዳንቱ ጉዞ ከመዋሉ በፊት የተደረጉበትን ማሻሻያዎች ለመፈተሽ "የመጨረሻ ፈተና" እንደሚያከናውን አስታውቋል።

የአየር ኃይሉ እንዳመለከተው፣ በአውሮፕላኑ ላይ የተደረጉት ማሻሻያዎች የደኅንነት፣ የተልዕኮ ግንኙነት፣ የሎጂስቲክስ ድጋፍ እና የላቀ የቴክኖሎጂ መገልገያዎችን ያካትታል። አውሮፕላኑ ሲመጣ ከነበረው ይዘት ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ ከሚችሉ ስጋቶች ሙሉ ለሙሉ ነጻ መሆኑም ተገልጿል።

የአውሮፕላኑ ውስጣዊ ክፍል ላይ ውስን ለውጦች ብቻ የተደረጉ ሲሆን፣ በውጫዊው ክፍሉ ላይ ደግሞ አዲስ ቀይ፣ ነጭ፣ ሰማያዊ እና ወርቃማ ቀለም ተቀብቷል።

ይህ የቅንጦት ቦይንግ 747-8 አውሮፕላን ለፕሬዝዳንት ትራምፕ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ከሚሰጡት ኤር ፎርስ ዋን ከሚባሉት አውሮፕላኖች አንዱ እንዲሆን በኳታር ንጉሣዊ ቤተሰብ ለአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር የተሰጠው ባለፈው ዓመት ግንቦት ነበር።

የአውሮፕላኑ ስጦታ ዜና ባለፈው ዓመት ሲገለጽ፣ የትራምፕ አጋሮችን ጨምሮ ከሌሎችም ተቃውሞ አስነስቶ ነበር። ተቺዎች እንዲህ ዓይነቱን ከፍተኛ ዋጋ ያለውን ልገሳ መቀበል የጥቅም ግጭት እንደሚፈጥር እና ሕገ መንግሥታዊ እንዳልሆነ ተከራክረዋል።

የአሜሪካ ፌዴራል ሕግ ባለሥልጣናት ስጦታዎችን መቀበል የሚችሉት ከ480 ዶላር በታች ብቻ መሆኑን ቢያመለክትም፣ ዋይት ሐውስ ግን አውሮፕላኑን መቀበል ሕጋዊ እንደሆነ አጥብቆ ተናግሯል፣ ጨምሮም ትራምፕ ሥልጣን ሲለቁ ለፕሬዝዳንታዊው ቤተ መጽሐፍት እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል።

ትራምፕ በንግግራቸው ላይ "የዚህ አውሮፕላን አሠራር ፈጽሞ የሚታመን አይደለም" በማለት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

"በእውነቱ የእንጨቶቹ ጥራት፣ የውስጥ ቁሳቁሶቹ ጥራት፣ የሞተሮቹ ጥራት የተለየ ነው። እነዚህ ሞተሮች እጅግ በጣም ምርጥ የሚባሉ ናቸው፣ በዓለም ላይ እጅግ በጣም ጥሩ ናቸው፣ እንደሱ ዓይነት ነገር የለም" በማለት የኳታሩን አሚር አመስግነዋል።

የኳታር ስጦታ የሆነው አውሮፕላን ከመጨመሩ በፊት፣ ኤር ፎርስ ዋን የተባለው የፕሬዝዳንቱ መጓጓዣ የሆኑ እና ከአውሮፓውኑ 1990 ጀምሮ አገልግሎት ላይ ያሉ ሁለት 747-200ቢ ጄቶች አሉ። ከእነዚህ መካከል አሮጌ ሞዴል ከአገልግሎት እንደሚወጣ የዋይት ሐውስ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ስቲቨን ቼዋን ተናግረዋል።

የአሜሪካ አየር ኃይል ከቦይንግ የታዘዙ ሁለት ግዙፍ ጄቶች ተጠናቀው እስከሚቀርቡ ድረስ አዲሱ ጄት በጊዜያዊነት ለፕሬዝዳንቱ አገልግሎት እንደሚሰጥ አስታውቋል።