የትራምፕ ድርጅቶች በወንጀል ተጠርጥረው እየተመረመሩ ነው

ታትሟል

የኒውዮርክ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የቀድሞውን የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕን ድርጅቶች በወንጀል ጠርጥሮ እየመረመረ እንደሆነ አስታወቀ፡፡የዋና ዓቃቤ ሕጓ ሌቴሺያ ጄምስ ቃል አቀባይ በድርጅቶቹ ላይ የሚደረገው ምርመራ ‹‹ሙሉ በሙሉ የፍትሃ ብሔር አይደለም›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ አቃቤ ሕጓ ጄምስ ወደ ኃላፊነቱ ከመምጣታቸው በፊትም የሪፐብሊካኑን ፕሬዘዳንት ትራምፕ የፋይናንስ ዝርዝር በመተቸት ይታወቃሉ፡፡

የትራምፕ ድርጅቶች በበኩሉ ምንም አይነት ጥሰት አልፈፀምንም ሲል መልስ የሰጠ ሲሆን ከዲሞክራቱ ፓርቲ በመጡ ዓቃቤ ሕግ የሚደረግ ምርመራ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ነው ሲልም አክሏል፡፡ ‹‹ለትራምፕ ተቋማት ምርመራችን ሙሉ በሙሉ የፍትሃ ብሔር እንዳልሆነ አሳውቀናቸዋል›› ሲሉ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ቃል አቀባይ ፋቢየን ሌቪ ማሰኞ ዕለት ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡‹‹በአሁኑ ሰአት ከማንሃተን ዲስትሪክት ዓቃቤ ሕግ ጋር በመሆን የትራምፕ ተቋማትን የወንጀል ኃላፊነት በተመለከተ በሙሉ ኃይላችን እየመረመርን ነው›› ሲሉም አክለዋል፡፡ ነገር ግን የፍትሃ ብሔር ምርመራውን ወደ ወንጀል እንዲቀየር ያደረገው ምክንያት ምን እደሆነ ብሎም ድርጊቱ ትራምፕን በግል ተጠያቂ ያደርግ እንደሆነ ቃል አቀባዩ ያሉት ነገር የለም፡፡ከሦስት አመታት በፊት በትራምፕ ላይ ፍትሃ ብሔር ምርመራ የጀመሩት ጄምስ የትራምፕ ድርጅቶች ከባንኮች ብድር ለማግኘት ያላቸውን የሃብት መጠን በማግዘፍ ብሎም ግብር ለመሰወር ደግሞ ንብረት በማሸሽ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ በሎስአንጀለስ፣ ማንሃተን፣ ኒው ዮርክ ብሎም ቺካጎ ያሉ የትራምፕ ድርጅቶች ሰነድ እንዲያቀርቡ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕጓ መጠየቃቸውም ይታወሳል፡፡ የማንሃተኑ ዓቃቤ ሕግ ሳይረስ ቫንስ ጁኒየር በበኩላቸው ባለፈው አመት ነሃሴ ወር ‹‹በሌላ ሰው እንዲፈፀም በተደረገ የወንጀል ድርጊት›› ምክንያት የትራምፕን ተቋማት በመጠርጠር ምርመራ እያደረጉ እንደነበር ገልጸዋል፡፡የቫንስ ምርመራ መነሻ የሆነውም በአንድ ጋዜጣ ላይ ድርጅቶቹ ፈፀሙት ተብሎ የተጠቀሱ የኢንሹራስ እና የባንክ ማጭበርበሮች ናቸው፡፡ እንዲሁም እኤአ በ2016 ከትራምፕ ጋር ግንኙነት ነበረን ላሉ ሁለት ሴቶች የተከፈሉ ክፍያዎችን ለመሸፈን ሲባል የድርጅቱ የፋይናንስ ሰነዶች ተቀይረው ከሆነ በሚልም የማን ሃተን ዓቃቤ ሕግ ሲመረምር ቆይቷል፡፡እንዲሁም የትራምፕን የግብር ተመላሽ ሰነዶች መያዙን እና ይህም የምርመራው አንድ አካል እንደሆነ አስታውቆ ነበር፡፡