ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኦባማዎች በፕሬዝዳንታዊ ማዕከል ምርቃት ላይ ከትራምፕ ውጪ ሦስት የቀድሞ መሪዎችን ጋበዙ
ባራክ እና ሚሼል ኦባማ በፕሬዝዳንታዊው ማዕከል ምርቃት ላይ ከዶናልድ ትራምፕ ውጪ ሦስት የቀድሞ የአገሪቱን መሪዎች እና ባለቤቶቻቸው ሲገኙ ፕሬዝዳንት ትራምፕ አለመጋበዛቸው አነጋጋሪ ሆኗል።
'ኦባማ ፕሬዝደንሻል ሴንተር' የተባለው ማዕከል ሲመረቅ ጆርጅ ቡሽ፣ ቢል ክሊንተን እና ጆ ባይደን ተገኝተዋል።
ቢቢሲ ስለ ጉዳዩ ከዋይት ሐውስ ምላሽ ጠይቋል።
ባራክ እና ሚሼል ኦባማ የከፈቱት ማዕከል ሙዚየም፣ ቤተ መጻሕፍት እና የትምህርት ተቋም የያዘ ነው። ጥንዶቹ በዋይት ሐውስ ላሳለፉት ስምንት ዓመታት መታሰቢያ እንደሆነም ተገልጿል።
ጥንዶቹ ለረዥም ጊዜ ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ ቆይተዋል።
ማዕከሉን ያስገነቡት ዋይት ሐውስ ከመግባታቸው በፊት ይኖሩበት በነበረው አካባቢ ነው።
የምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ሲከናወን የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ "ማዕከሉ ደማቅ እና ማኅበረሰባችንን የሚዘክር እንዲሆን እንፈልጋለን። ጥበብ፣ ሙዚቃ እና ስፖርት የምንጋራበት እንዲሁም የምንማማርበት ይሆናል" ብለዋል።
ሚሼል ኦባማ በጥልቅ ስሜት ውስጥ ሆነው ስለ ባለቤታቸው ንግግር አድርገዋል። ባራክ ኦባማም በዚህ ስሜታዊ ሆነው ታይተዋል።
ጥንዶቹ ዶናልድ ትራምፕን በስም ባይጠቅሱም የአሁኑን አስተዳደር ወርፈዋል።
የቀድሞዋ የጀርመን መራሔተ መንግሥት አንግላ ሜርክል እና የቀድሞው የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ በማዕሉ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ታድመዋል።
ጄኔፈር ሀድሰን፣ ክርስቲና አጉሌራ፣ ጆን ሌጀንድ፣ ኮመን እና ሌሎችም ዝነኛ ድምጻዊያን በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ሙዚቃ አቅርበዋል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ከሥልጣን ሲወርዱ ቤተ መጻሕፍት የመክፈት ልማድ አላቸው።
ኦባማዎች የከፈቱት ማዕከል ቅርጫት ኳስ መጫወቻ፣ የሙዚቃ ስቱዲዮ እና ሌሎችም መዝናኛዎችን የያዘ ነው።
ማዕከሉ ለሕዝብ ፓርክነት በተመደበ ቦታ ላይ መሠራቱ ተቃውሞ እንዲሁም የፍርድ ቤት ክርክር አስነስቷል።
ቱሪስቶችን ወደ ቺካጎ ሊስብ ይችላል በሚል በአወንታዊ መንገድ ማዕከሉን የተመለከቱም አሉ።
ማዕከሉ ወደ 850 ሚሊዮን ዶላር እንደወጣበት ተነግሯል።